​አዳማ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሜዳቸው ውጪ ጣፋጭ ድል አስመዝግበዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት 5 ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ከሜዳቸው ውጪ ለተጫወቱ ክለቦች አስደሳች ቀን ሆኖ አልፏል፡፡ ወደ አርባምንጭ የተጓዘው ኤሌክትሪክ እና የወደ ሶዶ ያቀናው አዳማ ከተማ የውድድር አመቱን የመጀመርያ ድል አስመዝግበዋል፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በተገኙበት ጨዋታ አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ አትዮ ኤሌክትሪክን አስተናግዶ 2-1 ተሸንፏል፡፡ 14ኛው ደቂቃ ላይ ከጉዳት ተመልሶ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ የተካተተው ኃይሌ እሸቱ በግል ጥረቱ በቀኝ ጠርዝ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ጋናዊው ካሉሻ አልሀሰን በአግባቡ ተጠቅሞ ኤሌክትሪክን ቀዳሚ ሲያደርግ 44ኛው ደቂቃ ላይ በኤሌክትሪክ የግብ ክልል ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት ወንድሜነህ ዘሪሁን በቀጥታ ወደ ግብ ሲመታ የኤሌክትሪክ ተከላካዮች በእጅ በመንካታቸው የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ላኪ ሳኒ አስቆጥሮ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡ ኤሌክትሪኮች ወደ እረፍት ከማምራታቸው በፊት ፍፁም ቅጣት ምቱ አግባብ አልነበረም በኒል ክስ አስመዝግበዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ 52ኛ ደቂቃ ላይ ዲዲዬ ለብሪ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ በድጋሚ ኤሌክትሪክን መሪ ማድረግ የቻለ ሲሆን በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል የግብ ሙከራዎች ቢስተናገዱም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በኤሌክትሪክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ባለፉት አመታት መጥፎ አጀማመር ሲያደርግ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ2 ጨዋታ 4 ነጥቦችን በመሰብሰብ ጥሩ አጀማመር ሲያደርግ ካለፈው አመት ሁለተኛ ዙር የጀመረው የአርባምንጭ ከተማ ውጤት አልባ ጉዞ ዘንድሮም የቀጠለ ይመስላል፡፡ በ3 ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 9 ነጥብም 2 ብቻ አሳክቷል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

ፀጋዬ ኪ/ማርያም – አርባምንጭ ከተማ

‹‹ዛሬ በአጠቃላይ ጥሩ አልነበርንም፡፡ ጨዋታው ለኔ ተበልጠን የተሸነፍንበት ነው፡፡ ተከላካዮቼ እጅግ ተዳክመውብኛል፡፡ ውድድሩ ገና ሶስተኛ ሳምንቱ በመሆኑ ደጋፊው ሊታገሰን ይገባል፡፡ ተቃውሞውም ተገቢ አይመስለኝም፡፡››

ብርሀኑ ባዩ – ኤሌክትሪክ

‹‹እኛ ያገኘነው የልፋታችንን ውጤት ነው በተለይ አርባምንጭን በሜዳው ማሸነፍ ከባድ ቢሆንም ያን ተቋቁመን ማሸነፍ ችለናል፡፡ በዛሬው የተሰጠብን ፍፁም ቅጣት ምትም ተገቢ አልነበረም›

ወደ ሶዶ ያቀናው አዳማ ከተማ እንደ ኤሌክትሪክ ሁሉ ወላይታ ድቻን 2-1 በማሸነፍ የውድድር አመቱን የመጀመርያ ሶስት ነጥብ ማግኘት ችሏል፡፡ በ23ኛው ደቂቃ ከነአን ማርክነህ ከርቀት አክርሮ የመታት ኳስ በወላይታ ድቻ ተከላካዮች ተጨርፋ ኢማኑኤል ፌቮ መረብ ላይ በማረፍ አዳማ ቀዳሚ መሆን ችሏል፡፡ በ27ኛው ደቂቃ ላይ ምኞት ደበበ ከግራ ጠርዝ የሰጠውን ኳስ ከነዐን ማርክነህ በድጋሚ ወደ ግብነት ቀይሮ የአዳማ ከተማን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች በጃኮ አራፋት የ52ኛው ደቂቃ ግብ መነሳሳት ቢችሉም ተጨማሪ ተከላካዮችን ወደ ሜዳ ያስገቡት አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ ተሳክቶላቸው ጨዋታው በአዳማ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው 88ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማው አጥቂ ዳዋ ሁቴሳ ከዳኛ ጋር በፈጠረው ግብግብ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሲወጣ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ሱሌይማን መሀመድ በሰራው ጥፋት በተመሳሳ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ በጨዋታውም በአጠቃላይ 5 ቢጫ እና 2 ቀይ ካርዶች ተመዘዋል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

መሳይ ተፈሪ – ወላይታ ድቻ
“በጨዋታው እጅግ ጥሩ ነበርን፡፡ ተጋጣሚያችን ባገኙት ሁለት እድሎች ብቻ አስቆጥረውብን አሸንፈውናል፡፡ ማግባት የምንችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎችን ፈጥረናል፡፡”

ተገኔ ነጋሽ – አዳማ ከተማ
‹‹ በማሸነፋችን ደስተኛ ነኝ፡፡ ውጤቱን አስጠብቀን በአሸናፊነት መውጣታችን ለቡድኔ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ያገኘነውን እድል በአግባቡ ተጠቅመናል፡፡ ጨዋታው ኃይል የተቀላቀለበት ነበር። ጥፋት የበዛበትም ነበር። ሆኖም ለኛ ብቻ ተለይቶ የተሰጠብን ውሳኔ አግባብነት የለውም።በዳኝኘቱ አዝኛለው። ››
ዛሬ ከተካሄዱት 5 ጨዋታዎች ደደቢት ብቻ በሜዳው ማሸነፍ የቻለ ሲሆን አዳማ ከተማ ፣ ፋሲል ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሜዳቸው ውጪ አሸንፈዋል፡፡ መቐለ ደግሞ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን ነጥብ ማስጣል ችሏል፡፡

____________________

ተጨማሪ መረጃዎች በስፍራው ከነበሩ ጋዜጠኞች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *