​የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት – የቅዳሜ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት  በሳምንቱ መጨረሻ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይቀጥላል። ከነዚህ መሀከል ነገ አዲስ አበባ ላይ መከላከያ አዳማ ከተማን የሚያስተናግድበትን እና ድሬደዋ ላይ ድሬደዋ ከተማ ከደደቢት የሚገናኙባቸውን ጨዋታዎችን ተመልክተናቸዋል።

መከላከያ ከ አዳማ ከተማ
መከላከያ እስካሁን ደካማውን አጀማመሩን ማስተካከል አልቻለም። አመቱን በአቻ ውጤት የጀመረው ክለቡ በወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ሽንፈት ደርሶበታል። ለአራተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታድየም የሚያደርገውን የነገውን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥም የገባ ይመስላል። ተጋጣሚው አዳማን ስንመለከት በውጤት ደረጃ መሻሻል እያሳየ የመጣ ቡድን መሆኑን እንረዳለን። በሽንፈት አመቱን የጀመሩት አዳማዎች ሁለተኛ ሳምንት ላይ ከደደቢት አቻ ተለያይተው ሶስተኛው ሳምንት ላይ ወላይታ ድቻን በመርታት የመጀመሪያ ሶስት ነጥባባቸውን አሳክተዋል።


ቴዎድሮስ ታፈሰ በኢትዮ ኤሌክትሪክ መረብ ላይ ካሳረፋት የቅጣት ምት ውጪ ሌላ ጎል ማግኘት ያልቻለው መከላከያ ነገ ከሜዳው ውጪ በመከላከሉ ከማይታማው አዳማ ከተማ ጋር መግጠሙ ጨዋታውን እንደሚያከብድበት ይታመናል። ቡድኑ ለሚፈጥራቸው ዕድሎች ወሳኝ ሚና የነበራቸው የመስመር ተከላካዮቹ ማጥቃት ተሳትፎ የተዳከመበት መከላከያ የግብ ዕድል በመፍጠሩም በኩል እጅግ ቀንሷል። ከፊት ምንይሉ ወንድሙ እና ተመስገን ገ/ፃዲቅ በግላቸው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መጥፎ የሚባል ባይሆንም ከአማካይ ክፍሉ በቂ እገዛ ሲያገኙ አይስተዋልም። በተለይ የቡድኑ የማጥቃት ሂደት መነሻ የሆኑት የመስመር አማካዮች የቦታ አያያዝ እንደአምናው ሁሉ ዘንድሮም ጥያቄ የሚነሳበት ነው። ይህ ችግር ደግሞ የተሻለ የአማካይ ስብስብ ላለው አዳማ ከተማ ዕድል የሚሰጥ ይመስላል። አዳማ ከተማ ጨዋታውን አጥቅቶ በመጫወት ግቦችን ለማግኘት እና ለማሸነፍ አስቦ ከገባ በነከንአን ማርክነህ የሚመራው የቡድኑ የአማካይ ክፍል የመከላከያን ድክመት ለመጠቀም የሚያስችለው ጥራት አለው። ሆኖም ስህተቶችን ሲሰራ የሚታየው የአዳማ የኋላ ክፍል ምንአልባትም በነምንይሉ ወንድሙ ሊቀጣ የሚችልበት አጋጣሚም ሊፈጠር ይችላል።

አምና 29ኛው ሳምንት ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ተገናኝተው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች ያለግብ አቻ ሲለያዩ እንደነበረው ብዙ ክፍት ያልሆነ ጨዋታ ነገም ሊደገም የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው። የአሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬ ቡድን በተከታታይ በሜዳው ውጤት ማግኘት ባለመቻሉ ሙሉ ለሙሉ ይህን ጨዋታ ማሸነፍን አስቦ ለነገው ጨዋታ እንደሚቀርብ እርግጥ ቢሆንም ደህና የሚባል ደረጃ ላይ ያሉት አዳማዎች ዕቅድ የጨዋታውን መልክ የሚወስነው ይሆናል።

ማራኪ ወርቁ ፣ አቅሌሲያስ ግርማ እና አዲሱ ተስፋዬ ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ከመከላከያ ስብስብ ውጪ የሆኑ ተጨዋቾች ናቸው። ዳዋ ሁቴሳ እና ሱሌማን አህመድን በቅጣት የማይጠቀመው አዳማ ከተማ ጉዳት ላይ የሚገኙት የሲሳይ ቶሊን እና ቡልቻ ሹራን አገልግሎት ማግኘቱም የሚያጠራጥር ነው። ሆኖም አንጋፋው አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬ ከጉዳት እንደተመለሰ ተሰምቷል።

ፌዴራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ሲመራ ኢንተርናሽናል ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ፌዴራል ዳኛ ዳዊት ገብሬ ደግሞ በረዳት ዳኝነት ተመድበዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ደደቢት

ድሬዳዋ ከተማ ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን አሳክቶ ደደቢትን ያስተናግዳል። በመጀመሪያ ጨዋታው በሜዳው ጅማ አባጅፋርን ማሸነፍ የቻለው ድሬዳዋ ሳምንት ከሜዳው ውጪ ከወልድያ ጋር ያለግብ ተለያይቷል።  በሊጉ አናት የተቀመጡት ደደቢቶች በተከታታይ ያለግብ ካጠናቀቁዋቸው ጨዋታዎች በኃላ በሳለፍነው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን በጌታነህ ከበደ እና አቤል ያለው ግቦች ማሸነፍ ችለዋል።


በ2009 የውድድር አመት 10ኛ ሳምንት ላይ በድሬዳዋ ተገናኝተው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች 1-1 በሆነ ውጤት መለያየታቸው የሚታወስ ነው። ነገም በርካታ ግቦች ይቆጠራሉ ተብሎ ባይጠበቅም ሁለቱም እስካሁን ሽንፈት አለማስተናገዳቸው በጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ሊደረግ እንደሚችል የሚጠቁም ነው። የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ቡድን እንደሁልጊዜው ሁሉ ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን ተጋጣሚውን በመቆጣጠር  እና በሱራፌል ዳንኤል የመስመር እንቅስቃሴ ላይ በመመርኮዝ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሞክር ይገመታል።  ሆኖም የማጥቃት ተሳትፏቸው እምብዛም የሆነው የደደቢት የመስመር ተከላካዮች ለድሬዳዋ የመስመር መልሶ ማጥቃት ምን ያህል ክፍተት ይሰጣሉ የሚለው አጠያያቂ ነው።

በጨዋታው የደደቢት የአማካይ ክፍል የሚፈተንበት ይሆናል። አራት እና አምስት አማካዮችን ከፊት እንደሚጠቀሙባቸው አጥቂዎች ብዛት በማቀያየር ሲጠቀሙ የተስተዋሉት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በነገው ጨዋታ የድሬዳዋን የአማካይ እና ተከላካይ ክፍል ለማስከፈት በምን መልኩ ጨዋታውን እንደሚጀምሩ የሚጠበቅ ነው። በሀዋሳው ጨዋታ ጥሩ ቅንጅት የታየበት የጌታነህ ከበደ እና አቤል ያለው ጥምረትም ነገ ከጠንካራው የድሬዳዋ የተከላካይ ክፍል ጋር የሚገናኝ ይሆናል። በጨዋታው ሰፊ ቦታ አካሎ የሚጫወተው ፈጣኑ አቤል ያለው እና በአጨራረስ ብቃቱ የማይታማው ጌታነህ ከበደ ከአንተነህ ተስፋዬ እና ያሬድ ዘውድነህ የመሀል ተካላካይ ጥምረት ጋር የሚፋለሙ ይሆናል።

የድሬዳዋ ከተማው ወሰኑ ማዜ እና የደደቢቱ ኩዌኪ አንዶህ ከነበረባቸው ጉዳት ባለማገገማቸው በነገው ጨዋታ የማይሰለፉ ይሆናል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በፌዴራል ዳኛ ወልዴ ንዳው የመሀል ዳኛነት እንዲሁም  በፌዴራል ዳኛ ዳንኤል ግርማ እና በፌዴራል ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት ረዳት ዳኝነት የሚመራ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *