የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሣምንት ሦስት ጨዋታዎች ነገ ይደረጋሉ። አዳማ እና አዲስ አበባ ላይ የሚደረጉትን ሁለት ጨዋታዎችም እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።
ጅማ አባ ጅፋር ከ ሲዳማ ቡና
እንደሊጉ የመጀመሪያ መርሀ ግብር ቢሆን ኖሮ ጅማ ላይ ይካሄድ የነበረው ይህ ጨዋታ ፌዴሬሽኑ ክለቡ በመጀመሪያ ሳምንት ሀዋሳን በረታበት ጨዋታ ላይ በተከሰተው ረብሻ ምክንያት ከሜዳው ከ 150 ኪ.ሜ በላይ በሆነ ርቀት ላይ እንዲጫወት በመወሰኑ የጨዋታው ቦታ ወደ አዳማ ተቀይሮ ነገ ዘጠኝ ሰዐት ላይ የሚደረግ ይሆናል።
ቅጣቱን ካስከተለው የሀዋሳው ድል በኋላ አባ ጅፋሮች ያሉበት ሁኔታ ጥሩ የሚባል አይደለም። ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች አንድም ድል ሳያስመዘግቡ እና ግብም ሳያስቆጥሩ በሊጉ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በተመሳሳይ ሦስት ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡናም ያለበት ሁኔታ ከተጋጣሚው የተለየ አይደለም። ልዩነቱ ሲዳማ ሶስቱን ነጥቦች ያሳካው በሶስት የአቻ ውጤቶች መሆኑ ነው።
የአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌው አባ ጅፋር በ 1 ጎል ልዩነት ከተሸነፈባቸው ሶስቱ ጨዋታዎች መሀከል በፋሲል ከተማ እና መቐለ ከተማ በተረታበት ጨዋታዎች የተቆጠሩበት ግቦች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ የተገኙ መሆናቸው የቡድኑን የትኩረት ችግር የሚያሳዩ ናቸው። በድሬደዋ ከተማ ጨዋታ ላይም የኩዋሜ አትራም ጎል ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ 6ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘች መሆኗ ይህን ሀሳብ ያጠናክራል። ቡድኑ አንድ ግብ በየጨዋታው ቢያስተናግድም ግብ አለማስቆጠሩ ደግሞ በአዲስ አበባ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ የታየው የቡድኑ የወገብ በላይ ድክመት አለመቀረፍ የሚናገር ነው። ኦኪኪ አፎላቢም ቡድኑን ከተቀላቀለ በኃላ በመጀመሪያ ጨዋታው ሁለት ግቦችን ቢያስቆጥርም ከዛ በኃላ ግን በአጀማመሩ አልዘለቀም። ሲዳማ ቡናም እስካሁን ያስቆጠራቸውን ሁለት ግቦች ያስቆጠረለት አዲስ ግደይ አለመኖር ደካማ የነበረውን የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ይበልጥ ሊያዳክመው እንደሚችል የሚታሰብ ነው። በርግጥ ከሌሎቹ ጨዋታዎች በላይ በጊዮርጊሱ ጨዋታ ሲዳማዎች በርካታ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ግብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። ቡድኑ ጨዋታው በገለልተኛ ሜዳ ላይ መደረጉን በመጠቀም ከጥንቃቄ ይልቅ ወደፊት ገፍቶ ለመጫወት እንደሚሞክር የሚታሰብ ቢሆንም በአበበ ጥላሁን አለመኖር ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን የኃላ መስመር መሳሳት በአግባቡ መድፈን ይጠበቅበታል።
በጥቅሉ ሁለቱ ተጋጣሚዎች ካሉበት ሁኔታ አንፃር በጨዋታው ቀዳሚ ግብ የሚያገኘው ክለብ የማሸነፍ ዕድሉ ሰፊ እንደሚሆን መናገር ይቻላል። የጅማ አባጅፋሮቹ እንዳለ ደባልቄ ፣ ኦካካ አፉላቢ እና ሳምሶን ቆልቻ እንዲሁም የሲዳማዎቹ ባዬ ገዛሀኝ ፣ አብዱለጢፍ መሀመድ እና ፍፁም ተፈሪ በጨዋታው ልዩነት ይፈጥራሉ ተብለው የሚጠበቁ ተጨዋቾች ናቸው።
የጅማ የቀኝ መስመር ተከላካይ ኄኖክ አዱኛ እንዲሁም የሲዳማዎቹ አበበ ጥላሁን እና አዲስ ግደይ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስብስብ ውስጥ በመካተታቸው ጨዋታው ያልፋቸዋል። መሀመድ ኮናቴ እና ፈቱዲን ጀማል በሲዳማ ቡና በኩል ስማቸው በጉዳት ዝርዝር ውስጥ ሲካተት የጅማ አባ ጅፋሮቹ ዝናቡ ባፋአ ፣ አሸናፊ ሽብሩ እና ጌቱ ረፌራም በተመሳሳይ በጉዳት ከጨዋታ ውጪ የሆኑ ተጨዋቾች ናቸው። ከዚህ ውጪ የጅማ አባ ጅፋሩ ጋናዊ ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጃዬ በፍርድ ቤት ጉዳይ ወደ ሀገሩ ካቀና በኃላ ባለመመለሱ እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ ከጨዋታ ውጪ ሆኗል።
ጨዋታውን ፌ/ዳ ተካልኝ ለማ በመሀል ዳኝነት እንዲሁም ፌ/ዳ ካሳሁን ፍፁም እና ፌ/ዳ ሰለሞን ተስፋዬ በረዳት ዳኝነት ይመሩታል።
ደደቢት ከ ፋሲል ከተማ
ጥሩ ግምት ከተሰጣቸው ጨዋታዎች መሀል አንዱ የሆነው የደደቢት እና የፋሲል ከተማ ፍልሚያ ነገ 11፡30 ላይ የሚደረግ የአምስተኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ይሆናል። ሁለቱ ቡድኖች አምና በሊጉ 27ኛ ሳምንት ላይ በአዲስ አበባ ሲገናኙ ደደቢት 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል። ተመሳሳይነት በሚታይበት በቡድኖቹ የእስካሁኑ የዘንድሮ ጉዞ ደግሞ በመሀከላቸው የአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ ያለ ሲሆን ሁለቱም አንድ አንድ ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል። አንድ ቀሪ ጨዋታ ያለው ፋሲል ከተማ ከሜዳው ውጪ ያለው ሪከርድ መልካም የሚባል ነው። ጅማ አባጅፋርን አሸንፎ ከወልዋሎ አቻ ተለያይቶ ያገኛቸው አራት ነጥቦች የተገኙት ቡድኑ ከሜዳው ውጪ በወጣባቸው አጋጣሚዎች ነው። ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሁለቱን ሜዳው ላይ ያከናወነው ደደቢትም በተመሳሳይ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ከወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ አራት ነጥቦችን አሳክቷል ።
ከሜዳቸው ውጪ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ደፈር ብለው ከሚጫወቱ ጥቂት ቡድኖች መሀል ፋሲል ከተማ ይጠቀሳል። አምና በሊጉ የመጀመሪያ ተሳትፎ ከሜዳ ውጪ የሰበሰባቸው በርካታ ነጥቦች እና የዘንድሮው ጉዞውም ለዚህ ምስክር ነው። ፈጠን ባለ የማጥቃት ሽግግር ወደ ተጋጣሚያቸው ሜዳ በመግባት ዕድሎችን ሲፈጥሩ የሚስተዋሉት አፄዎቹ በነገው የደደቢት ጨዋታ ላይም ተመሳሳይ አቀራረብ እንደሚኖራቸው ይገመታል። በተለይም ከመስመር የሚነሱት ኤርሚያስ ሀይሉ እና ራምኬል ሎክ እምብዛም ከግብ ክልላቸው ከማይርቁት የደደቢት የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚገናኙባቸው ሁለቱ መስመሮች ላይ የሚኖራቸው ውጤታማነት ለቡድኑ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ወሳኝ እንደሚሆኑ ይታመናል። የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታው ደደቢት ደከም ብሎ የሚታየውን የአማካይ ክፍሉን ቅርፅ በመቀያየር መፍትሄ እየፈለገ ያለ ይመስላል። በጨዋታው የአቤል ያለው አለመኖር ቡድኑ ጌታነህ ከበደን ብቸኛ አጥቂ በማድረግ መሀል ላይ አምስት አማካዮችን ወደሚጠቀምበት ዕቅዱ እንዲያደላ ሚያበረታታ ይመስላል። በመሆኑም መሀል ላይ በሚኖረው የቁጥር ብልጫ በመጠቀም ሁለት አማካዮች ለተከላካይ ክፍሉ ሽፋን እየሰጡ የፋሲልን የመልሶ ማጥቃት በማርገብ ከሁለቱ መስመሮች በሚነሱት ሽመልስ ጉግሳ እና ኤፍሬም አሻሞ እንቅስቃሴ ላይ በመመርኮዝ ግቦችን ለማግኘት እንደሚሞክር መናገር ይቻላል። በዚህም መሰረት ጥሩ የማጥቃት ፍሰት የሚታይበት እና በፈጣን እንቅስቃሴ የታጀበ ጨዋታ ከሁለቱ ቡድኖች የሚጠበቅ ይሆናል።
አቤል ያለው እና ታሪክ ጌትነት ከደደቢት እንዲሁም አብዱርሀማን ሙባረክ እና አምሳሉ ጥላሁን ከፋሲል ከተማ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ወደ ኬንያ በማምራታቸው በዚህ ጨዋታ ላይ አይኖሩም። በተጨማሪም የፋሲል ከተማው አማካይ ዳዊት እስጢፋኖስ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሲሆን በድሬደዋው ጨዋታ ተጎድቶ የወጣው የደደቢቱ የግራ መስመር ተከላካይ ብርሀኑ ቦጋለም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።
ኢ/ዳ ብሩክ የማነብርሀን ጨዋታውን በዋና ዳኝነት የሚመራ ሲሆን ፌ/ዳ አስቻለው ወርቁ እና ፌ/ዳ ወጋየው ድንቁ በረዳት ዳኝነት ተመድበዋል።