የፍርድ ቤት ጉዳይ አለኝ በሚል ምክንያት ወደ ሀገሩ ያቀናው የጅማ አባጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጄ እስካሁን አለመመለሱ ሲታወቅ በቀጣይ የመምጣቱ ሁኔታም አጠራጣሪ ሆኗል።
የቀድሞው የጋና ኢንተርናሽናል እና ሲምባ ግብ ጠባቂ ጅማ አበጅፋርን ማገልገል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ መልካም የሚባል እንቅስቃሴ እያደረገ ባለበት ወቅት ነበር ባሳለፍነው ሳምንት ክለቡን የፍርድ ቤት ጉዳይ እንዳለበት በመግለፅ ወደ ሀገሩ ጋና ያቀናው። ሆኖም አሁን የሚገኘው ከሆላዳዊ የትዳር አጋሩ ጋር አምስተርዳም እንደሆነ ሰምተናል። የጅማ አባጅፋር የክለብ አመራሮች ወደ ክለቡ እንዲመለስ የተለያዩ ግኑኝነቶች እያደረጉ እንደሚገኙ እና ለኤምባሲዎች እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት እንዳሳወቁም ታውቋል።
አጄይ ከሄደበት የሚመለስበት የመጨረሻ ቀን ታህሳስ 1 እንደሆነና ክለቡም እስከዚህ ቀን ድረስ ይመለሳል ብሎ እየጠበቀ ቢገኝም ሶከር ኢትዮዽያ እንዳገኘችው መረጃ የመመለሱ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። ይህ የሚሆን ከሆነ በአምስት ጨዋታ አራት ነጥብ በመያዝ ጥሩ ጉዞ እያደረገ ለማይገኘው ጅማ አባጅፋር ሌላ ራስ ምታት የሚፈጥር ይሆናል። ክለቡ ዳንኤል አጄይ ወደ ቡድኑ እንደሚመለስ ተስፋ ከማድረግ ጎን ለጎን በሁለተኛው ዙር ሌላ ግብ ጠባቂ ከውጭ ለማምጣት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ሰምተናል።