የመጽሐፍ ምርቃት
በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ማኀበር ስራ አስኪያጅ በሆኑት በአቶ ሰለሞን በቀለ ፀሐፊነት ተዘጋጅቶ ለንባብ የቀረበው ” ስፖርታዊ ስነ ምግባር ” የተሰኘው መጽሐፍ ዛሬ የቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ገ/መስቀል ፣ የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል አዳራሽ የመጸሐፏ ምርቃት ተከናውኗል።
በምርቃት ስነ ስርአቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት እንግዶች ስርአት አልበኝነት በየሜዳዎቹ እየተስፋፉ መምጣታቸውን በመልክቶቻቸው ያንፀባረቁ ሲሆን በዋናነት ሁሉም መልዕክት ተናጋሪዎች አፅኖት ሰጥተው የተናገሩት በእግርኳሱ ውስጥ ጎጠኝነት ፣ ዘረኝነት እየተፀባረቁ መምጣታቸው አሳሳቢ እንደሆነ እና በምንም መንገድ ደጋፊዎች ይህን ኋላ ቀር እርባና የሌለውን ነገር ወደ ሜዳ ይዘው መምጣት እንደሌለባቸው ነው። እንደነዚህ ያሉ መፅሐፍቶች መዘጋጀታቸው ብቻ በቂ እንዳልሆኑ እና ሁሉም የሚመለከተው አካል የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ይህን ችግር ለማስወገድ መታገል አለበት ብለዋል።
መፅሐፉን ለንባብ ያበቁት አቶ ሰለሞን በቀለ መፅሐፉን ለመፃፍ ያነሳሳቸው በቅርበት የኢትዮጵያ እግርኳስን እንደማወቃቸው እና አሁን እየተባባሰ ከመጣው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር አኳያ ለሁሉም ግንዛቤ ለመፍጠር በማሰብ መሆኑን ገልፀዋል።
መጽሐፉ 65 ገፅ ሲኖረው አንዱን መፅሐፍ ለመግዛት 50 ብር እንደሚያወጣ ተነግሯል።
ኢትዮዽያ ቡና
አሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒችን ከክለቡ እውቅና ውጪ ያጣው ኢትዮዽያ ቡና አሰልጣኝ ፓፒች የሄዱበትን ህገወጥ መንገድ ለፌዴሬሽኑ እንዳሳወቀ እና በቀጣይ ጉዳዩን በመከታተል ለክለቡ ደጋፊዎች ይፋ እንደሚያደርጉ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በክለቡ የሬድዮ ፕሮግራም ላይ ተናግረዋል። በቀጣይ ክለቡን እንዲያሰለጥኑ በአፍሪካ የማሰልጠን ልምድ እንዳላቸው የተነገርላቸው ፈረንሳዊው ዲዲዬ ጎሜዝ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ለማምጣት በቅድመ ሁኔታ ደረጃ እንደተስማሙና ዛሬ እኩለ ሌሊት አአ እንደሚገቡ ተናግረው ነገ ይካሄዳል ተብሎ የታሰበውን የሸገር ደርቢ ጨዋታ እንደሚከታተሉ የተገለፀ ቢሆንም ጨዋታው ወደ ማክሰኞ በመተላለፉ በጨዋታ ላይ ቡድኑን እየመሩ ወደ ሜዳ ሊገቡ እንደሚችል ተገምቷል ።
አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ በአፍሪካ አሰልጣኝነታቸው በካሜሩን ፣ ታዛንያ ክለቦች እንደሰሩ ሲነገር በአልጄርያ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚገኘው ጀኤስ ኤም ስኪክዳ ክለብ የአሁኑ ክለባቸው እንደሆነ ተገልጿል።
የአስመራጭ ኮሚቴው ቅሬታ ሰሚ
ዛሬ ከረፋድ ጀምሮ በቀረቡለት የቅሬታ ጉዳዮች ዙርያ ረጅም ሰአት የፈጀ ስብሰባ ያደረጉት ሦስት አባላት የሚገኙበት ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ያሳለፉትን የውሳኔ ሀሳቦች ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ለማድረግ ብንሞክርም ሳይሳካ ቀርቷል። ሆኖም ከሦስት ድምፅ ሁለቱ የቀረቡትን ቅሬታዎች ሁሉ ውድቅ የሚያደርግ ውሳኔ በድምፅ ብልጫ እንደወሰኑ እየተሰማ ይገኛል።
1ኛ ሊግ ውድድር
የኢትዮዽያ 1ኛ ሊግ ውድድር ዛሬ በአንድ ጨዋታ አአ ተጀመረ። ውድድሩም ነገ በሚደረጉ 8 ጨዋታዎች የሚቀጥል ሲሆን የተቀሩት ጨዋታዎች የምዝገባ እና የዳኞች እና የታዛቢዎች ክፍያ ባለማጠናቀቃቸው ምክንያት የማይጀመር ቢሆንም የሚቀጥለው ሳምንት ሁሉም ውድድሮች እንደሚጀምሩ ፌዴሬሽኑ አሳውቋል። በዚህም መሰረት የዛሬው ጨዋታ ውጤት እና የነገ ፕሮግራሞች የሚከተሉት ናቸው።
የዛሬ ውጤት
ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ 2 – 0 ቂርቆስ ክ/ከተማ
ነገ የሚደረጉ ጨዋታዎች
አማራ ፖሊስ ከ መርሳ
ወሊሶ ከተማ ከ ቱሉቦሎ
ልደታ ክ/ከ ከ አዲስ ከተማ ክ/ከ
ቦሌ ክ/ከ ከ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ
ቡሌሆራ ከ ወላይታ ሶዶ
ኮንሶ ከ ጎፋ ባሬንቺ
ሺንቺቾ ከ ጅንካ ከተማ
አራዳ ክ/ከ ከ ሆለታ ከተማ
የፌዴሬሽኑ የስብሰባ ጥሪ
ዘንድሮ ገና ከጅምሩ እየተበራከቱ የመጡት የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ያሳሰበው የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፊታችን ዕሮብ ታኀሳስ 4 አሁን ለጊዜው ባልተገለፀ ቦታ የኢትዮዽያ ስፖርት ኮሚሽን ተወካይ ፣ የክለብ አመራሮች ፣ የፀጥታ አካላት ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የምክክር ጉባኤ ማዘጋጀቱን ሰምተናል።
ሀዋሳ ከተማ
የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ጨዋታ ዛሬ 09:00 ላይ ከመከላከያ ሊጫወት መርሐግብር የወጣለት ቢሆን ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ሜዳ ቢሄዱም የፀጥታ አካላት ጨዋታው እንደቀረ በመስማታቸው መመለሳቸው ይታወቃል። ታዲያ ፌዴሬሽኑ ጨዋታው ወደ ሰኞ 09:00 ላይ መዞሩ መነገሩ በብዙ ምክንያት ጨዋታውን ላለማድረግ እንደሚገደዱ እየገለፁ ሲሆን ምን አልባት ይህን ዜና ካቀረብንበት ጊዜ በኋላ የተቀየረ ነገር ከሌለ በስተቀር ሰኞ እንዲጫወቱ ፌዴሬሽኑ የወሰነውን ውሳኔ እንደማይቀበሉ እየተናገሩ ይገኛል ።
አቶ አብነት ገ/መስቀል
ስፖርታዊ ስነ ምግባር በተሰኘው መፅሐፍ ምርቃት ላይ ንግግር ያደረጉት የቅዱስ ጊዮርጊስ እግርኳስ ማህበር ፕሬዝደንት ባስተላለፉት መልዕክት ዘረኝነት ፣ ጎጠኝነት በየሜዳዎቹ እየተስፋፉ መሄዳቸው እያሳሰባቸው በመሆኑ በቅርቡ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት አንድ ሲፖዚየም ሊያዘጋጁ እንደሚችሉ ጥቆማ ሰጥተው አልፈዋል።