የአሰልጣኞች ገፅ | ኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች በእድሉ ደረጄ እይታ

በአዲስ መልክ በጀመርነው ‹‹የአሰልጣኞች ገፅ›› የዛሬው መሰናዷችን ከቀደሙት እስከ ዘመኑ ድረስ ያሉ ኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች ያላቸው የአጨዋወት እና የአሰለጣጠን መንገድ፣ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንዲሁም የተጫወች አያየዝ ስርዓታቸውን በተመለከተ ከቀድሞው ተጫዋች እና የአሁኑ አሰልጣኝ እድሉ ደረጄ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ እድሉ ደረጄ በተጫዋችነት ዘመኑ ለኢትዮ-ኤሌክትሪክ፣ አየር መንገድ፣ ኢትዮጵያ ባንኮች፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን በኢትዮጵያ ቡና የተስፋ ቡድን አሰልጣኝ ፣ የዋናው ቡድን ረዳት አሰልጣኝ እና ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ሰርቷል፡፡ በዘንድሮው የውድድር አመት ደግሞ የአንደኛ ሊጉ ክለብ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃንን ተረክቦ ቡድኑን ለውድድር እያዘጋጀ ይገኛል፡፡ እድሉ በተጫዋችነት ባሳለፈባቸው ጊዜያት ያሰለጠኑትን አሰልጣኞች፣ እንደ ስፖርት ቤተሰብ የታዘባቸውን እና በአሰልጣኝነት በሰራባቸው አጭር ጊዜያት ካገኛቸው ልምዶች በመነሳት ስለ ኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች አብርሃም ገብረማርያም እና ሚልኪያስ አበራ ጋር ባደረገው ቆይታ ሰፊ ማብራርያን ሰጥቷል፡፡  


ቀደምት አሰልጣኞች በተጫዋቾች ዘንድ የነበራቸው ተፈሪነት እና መከበር ከአሁኑ ዘመን ጋር ስናነጻፅረው በብዙ ርቀት የበለጠ ነው፡፡ ይህ ከምን የመጣ ይመስልሃል?

ሶስት ነገሮች ማንሳት ይቻላል፡፡ የመጀመርያው ተጫዋቾቹ የሚያልፉበት የእድገት ደረጃ ነው፡፡ ይህም ማለት የባህል እና የማሀበረሰባዊ መስተጋብር የፈጠረው አክብሮታዊ ልማድ ነው፡፡ ማንኛውም ግለሰብ ለታላላቆቹ የነበረው አክብሮት በተለያዩ የስራ ዘርፎች ይገለፅ ነበር፡፡ በእግርኳሱ ደግሞ አሰልጣኞች የእግርኳስ እድገትህን የሚወስኑ አካላት በመሆናቸው ከፍተኛ ክብር ያገኙ ነበር፡፡

ሁለተኛው የአሰልጣኞቹ አቀራረብ በተለይ ደግሞ በተጫዋቾች ኣያያዝ ላይ የነበራቸው አባታዊ አቀራረብ መሰረታዊ ነበር፡፡ የቀደመው ዘመን አሰልጣኞች ከመለሳለስ ይልቅ በከፍተኛ ቁጣ ፤ ተጫዋቾች በራሳቸው መንገድ እዲሄዱ ከመተው ይልቅ በጥብቅ ክትትል ተጫዋቾቻቸውን የመቅረፅ ባህል ነበራቸው፡፡ ቁጥጥሩ በሜዳ ብቻ ሳይወሰን ከሜዳ ውጪ ባላቸው ሕይወት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ይፈጥሩ ነበር፡፡ ተጫዋቾች ትዳር መስርተው የተረጋጋ ህይወት ኖሯቸው እና ከአጓጉል ባህርያት ርቀው ስኬታማ እና ረጅም የእግርኳስ ህይወት እንዲኖራቸው ይጥሩ ነበር፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ከዴሞክራቲክ አቀራረብ ይልቅ አውቶክራቲክ (ሁሉም ነገሮች ላይ የመወሰን ዝንባሌ የሚያሳዩ) መሆንን መምረጣቸው የተፈሪነት እና የመከበር ስብዕናን እንዲላበሱ አድርጓቸዋል፡፡

ሶስተኛው የዘመኑ አሰልጣኞች ከቀደሙት የወረሷቸው ባህርያት በእነሱም ላይ ያሳደረረው ተፅእኖ ይታያል፡፡ እንደነ ስዩም አባተ ፣ ካሳሁን ተካ እና አስራት ኃይሌ ያሉ አሰልጣኞች በተጫዋችነት ዘመናቸው ያሰለጠኗቸው ሉቺያኖ ቫሳሎ እና ይድነቃቸው ተሰማን የመሳሰሉ አሰልጣኞችን ባህርይ ማለትም ከአሰልጣኝ ወደ ተጫዋች የሚሄዱ ትዕዛዛት ላይ ማዕከል ያደረገ (Coach Centered) አቀራረብ መከተላቸው ይመስለኛል፡፡


ከ1970ዎቹ አጋማሽ እስከ 90ዎቹ መጀመርያ ከነበሩት አሰልጣኞች በኋላ የመጡትን ከየትኛው ወገን መመደብ እንችላለን?

የመካከለኛው ዘመን አሰልጣኞች (ከ1990ዎቹ መጀመርያ እስከ ምዕተ አመቱ መባቻ) በተጫዋችነት ካሰለጠኗቸው አሰልጣኞች የወረሷቸው ባህርያት እንዳሉ ሆነው ከትውልዱ እና ምዕራባዊያን አስተሳሰብ ተፅእኖ ጋር በማዳቀል ቅይጥ የሆኑ አሰልጣኞች የሚታዩበት ዘመን ነበር፡፡ አዲሱ ትውልድ ከቀደመው ትውልድ በተለየ ዴሞክራሲን የሚያይበት የተንሸዋረረ አተያይ ከቀደሙት ይልቅ ለታላላቆቹ ያለው አክብሮት ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህ የፈጠረው ተጽዕኖም ከቀደሙት አሰልጣኞች የወረሱትን አካሄድ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር እንዲያዋዱ አስገድዷቸዋል፡፡ አብርሃም ተክለኃይማኖት ፣ አብርሃም መብራቱ ፣ ክፍሌ ቦልተና ፣ ገብረመድህን ኃይሌ እና የመሳሰሉ አሰልጣኞች በዚህኛው የአሰልጣኝነት ዘመን የተፈተኑ አሰልጣኞ ነበሩ፡፡

ከአዲሱ ሚሌንየም ወዲህ ያለው የአሰልጣኞች ዘመን ስንመለከት አሰልጣኝነት ከባድ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከእድሜ ጋር የተያያዙ ምክንያችን ስንመለከት ከተጫዋችነት ዘመን መገለል በኋላ በፍጥነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስራ መምጣታቸው ከተጫዋቾቹ ጋር በእድሜ ተቀራራቢ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ በአዎንታዊ ጎኑ ወጣት አሰልጣኞች ከአንጋፋዎቹ በተሻለ የተጫዋቾቻቸውን ስሜት እና ፍላጎት እንዲረዱ ያደርጋል ፤ አዳዲስ እግርኳሳዊ አስተሳሰቦችን ተጫዋቾች በሚረዱበት መንገድ ለማስረፅ ይረዳል፡፡ በአሉታዊ ጎኑ ስንመለከተው ደግሞ የእድሜ መመጣጠን የስራ መስመርን የመለየት ችግርን ያመጣል ፤ የመከባበር ሒደትን ይቀንሳል፡፡ አሰልጣኞቹም በተጫዋቾቻቸው ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት እና ከበሬታ እንዲያገኙ የሚያደርጋቸውን ስራ ሲሰሩና ራሳቸውን ለማሻሻል ሲተጉ አናስተውልም፡፡ የትምህርት እድሎችን መፈለግ ፣ በንባብ ራስን ማበልፀግ እና የጨበጡትን እውቀት በተግባር የማሳየት ችግር መኖሩ በተጫዋቾች ዘንድ ከበሬታ እንዳያገኙ እና በተጫዋቾቻቸው ላይ የሚፈልጉትን ተጽእኖ መፍጠር እንዳይችሉ ገድቧቸዋል፡፡


አሰልጣኞቻችን በተለይም ቀደምቶቹ የጨዋታ አቀራረባቸው ተመሳሳይ ይዘት የነበረው ነው፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነበር?

ይህ የተጠናቀቀ መረጃ የተሰበሰበበት ባለመሆኑ ጥልቅ ጥናት ይፈልጋል፡፡ እንደኔ አመለካከት የስልጠናዎችም ሆነ የጨዋታዎች አቀራረብ መንገዶች በኛ ልክ የተሰፉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ አገራዊ መልክ ቢይዙም መልካም ነው፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ እግርኳስ ያሉት ፋሲሊቲዎች (የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ሜዳዎች ፣ የተሟሉ የልምምድ ቁሳቁሶች ፣ በየጊዜው የሚሻሻሉ የስልጠና ማንዋሎች እና በእግርኳሱ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል…) እንዲሁም የተጫዋቾቹ ተፈጥሮ (ክህሎት ፣ አካል ብቃት ፣ የእእምሮ ብቃት ፣ ተክለ ሰውነት….) ላይ የማሻሻያ ምርምሮች አይደረጉም፡፡ በአጠቃላይ በእግርኳሱ ዘላቂ የጥናት እና ምርምር እድገት (research development) የለንም፡፡ ስለዚህ በዘርፉ ላይ የሚሰሩ የትምህርት እና ጥናት ተቋማት ሊኖሩን ይገባል፡፡

ወደ ጥያቄው ስመጣ የአቀራረብ መንገዱም ሆነ የስልጠና ስርአቱ ተመሳሳይ መሆኑ አዳዲስ ሀሳባችን ለማፍለቅ የሚያግዝ ሲስተም ካለመኖሩ ጋር ይያያዛል፡፡ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አሰልጣኞች እና በስፖርት ሳይንስ ዘርፍ ያሉ ምሁራን ተቀራርበው የሚሰሩበት መንገድ አለመመቻቸቱ አሰልጣኞች ልምዳቸውን በእውቀት ለማዳበር እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የትምህርት እድሎች እምብዛም አልተፈጠረላቸውም ፣ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችም በግል ጥረታቸው ራሳቸውን ለማሻሻል የሚያገኙት ዕድልም አናሳ የሚባል ነበር፡፡ በእርግጥ እንደ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ያሉ በአመት በብዛት የስልጠና ትምህርቶችን የሚከታተሉ አሰልጣኞች እንዳሉ ሆነው፡፡


አሰልጣኞቻችን ውጤታማ ባይሆኑ እንኳ ለረጅም ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ የማሰልጠን እድል የሚኖራቸው ለምንድነው?

ማሰልጠንን እንዳያቆሙ የሚያደርጓቸው ምክንያች አሏቸው፡፡ ከነዚህም መካካል ዋንኛው አዲሱ የአሰልጣኞች ትውልድ የሚታይ ስኬት እያሳየ አለመሆኑ ‹‹እኔም ስራው ላይ ብቆይ ተመሳሳዩን መስራት እችላለሁ›› የሚል እምነት ማሳደራቸው ነው፡፡ ከዘመኑ እግርኳሳዊ እውቀት ጋር ለመራመድ የሚኖራቸው ጉጉት ፣ አሰልጣኞችን የሚመዘኑበት መስፈርት አለመኖር ፣ አመራሮች ለቡድኖቻቸው አሰልጣኝ የሚመርጡበት መንገድ ልምድ ላይ ማመዘን እና የመሳሰሉት በምክንያትነት መጥቀስ እንችላለን፡፡ ይህ ጉዳይ በአሰልጣኞች ላይ ብቻ ሳይሆን በተጫዋቾችም ላይ እንመለከታለን፡፡ ተጫዋቾች ለረጅም ጊዜ ሲጫወቱ እና ካቆሙ በኋላ በድጋሚ ወደ ሜዳ ሲመለሱም እናያለን፡፡

ውጤት ተኮርነት ላይ ያመዘኑ የአጨዋወት ስልቶች እንዲበዙ ያደረጋቸው ምክንያት እና የነበራቸው አሉታዊ ጎን ምንድን ነበር?

ዋንኛው ምክንያት ውጤት ማምጣት ትልቁ መመዘኛ መሆኑ ነው፡፡ ይህም የመመዘኛ መስፈርቶቻችን አናሳ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ አሰልጣኙም በረጅም ጊዜ የአሰልጣኝነት ልምዱ ይዞት የመጣው ነገር ላይ በተለይም ውጤት አምጥቶበት ከሆነ በስራው ላይ ያለው እምነት የፀና እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ Coach Instinct (ውጤት አምጥቼበታለሁ በሚለው መስመር ሁልጊዜም መጓዝ) የምንለው ነው፡፡

ሌላው የአሰልጣኝን ስህተት በሙያዊ መንገድ አርሞ የሚያሻሽል የግምገማ እና የመመዘኛ መስፈርት የሚከተል የእግርኳስ ስርዓት አለመኖሩ ነው፡፡ በእግርኳሱ አስተዳደር ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ቴክኒካል የሆነ እውቀት ያላቸው ሳይሆኑ ሹመኞች መሆናቸው ከውጤት በዘለለ የውጤታማነቱን መንገድ የመመልከት ፣ በቡድኑ ላይ የሚታየውን እድገት የመገንዘብ እና የአሰልጣኞችን ክፍተት የሚሞላ አቅም ባለቤቶች አይደሉም፡፡ እንደውም በዚህ የእግርኳስ ስርአት ላይ እያሰለጠኑ ያሉ አሰልጣኞች ላስመዘገቧቸው ውጤቶች ከፍተኛ አድናቆት እና አክብሮት አለኝ፡፡ ነገር ግን በዚህ ሁነታ ውስጥ መቀጠል የለብንም፡፡


አሰልጣኞቻችን ትምህርት በወሰዱበት ሀገር የነበረው የእግርኳስ አስተሳሰብ አሻራ አርፎባቸዋል ማለት እንችላለን? በእግርኳስ የላቁት ሀገራት የፈጠሩባቸው ተጽእኖስ በስራዎቻቸው ላይ ይታይ ነበር?  

አሰልጣኞቻችን የተማሩት ትምህርት እና የአሰለጣጠን መንገድ የተቀራረበ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ ትምህርት የመማር እድል ያገኙት በምስራቅ አውሮፓ ሀገራት (ቡልጋርያ ፣ ሀንጋሪ እና ዩጎዝላቪያ) እና ምስራቅ ጀርመን እንደመሆኑ የምስራቆቹ የተጫዋች አያያዝ ዘይቤ እና አካል ብቃት ላይ ያመዘነ አቀራረባቸው ላይ ይንፃባረቃል፡፡ ለዚ እንደ ጥሩ ምሳሌ የምናነሳው አንጋፋው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌን ነው፡፡ በእርግጥ አስራት የአሰልጣኝነት ትምህርት የወሰደው በዩጋንዳ በተዘጋጀ ስልጠና በሰር ቦቢ ቻርልተን አማካኝነት ነው፡፡ ይህም የእንግሊዛውያን በአካል ብቃት እና ፍጥነት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ እንዲከተል አድርጎት ይሆናል፡፡ አስራት በተጫዋቾቹ ላይ የአሸናፊነት ስነልቦና የማስረጽ ፣ ከፍተኛ የሆነ አካላዊ እና አዕምሯዊ ጫና እንዲቋቋሙ የማድረግ እንዲሁም ጥብቅ የተጫዋቾች አያያዝ ስርአት መከተሉ ደግሞ ለምስራቅ አውሮፓው የእግርኳስ አስተሳሰብ የቀረበ ያደርገዋል፡፡

የምስራቅ አውሮፓ የእግርኳስ አስተሳሰብ በሀገራችን እግርኳስ ላይ የአምበሳውን ድርሻ ቢወስድም አንዳንድ አሰልጣኞችም የምዕራብ አውሮፓዎቹን መንገድ ለመከተል ሲጥሩ ይታይ ነበር፡፡ ለምሳሌ ሀጎስ ደስታ በ1980ዎቹ መጨረሻ ይጠቀምበት የነበረው የልምምድ ፕሮግራም (Drill) በ1994 የአለም ዋንጫ ዝግጅት ወቅት ዝነኛው አሪጎ ሳኪ ከተከተሉት ጋር ተቀራራቢነት ያለው ነበር፡፡ በወቅቱ ወጣት እንደመሆኔ ነገሮችን የመረዳት ችሎታዬ አሁን ያለው ደረጃ ላይ ባይገኝም በጭላንጭል ትውስታዬ አሰልጣኝ ሀጎስ ምዕራባዊውን የስልጠና መንገድ ይከተል እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ሌላው ምሳሌ ደግሞ ካሳሁን ተካ ነው፡፡ የምዕራቡ አለም ሀሳባዊያን አሰልጣኞች ተፅዕኖ ያረፈበት ይመስለኛል፡፡ አሁን ብዙ የሚወራለት ተጋጣሚን በራሱ የሜዳ አጋማሽ ተጭኖ የመጫወት ዘይቤ (Pressing football)ን ይተገብር የነበረ አሰልጣኝ ነው፡፡ ለትግበራው የሚጠቀምባቸውን መፅሀፍቶችም ለመመልከት ችያለው፡፡ ስዩም አባተም መጠቀስ ያለበት አሰልጣኝ ነው፡፡ ዘመናዊ የልምምድ ትግበራዎችን የሚያዘወትር እና ተጋጣሚን በኳስ ቁጥጥር በልጦ ለመቅረብ የሚተጋ አሰልጣኝ ነበር፡፡ በልምምድ ወቅት የሚሰጠው በትንሽ የሜዳ ክፍል እና በአናሳ የተጫዋቾች ቁጥር በሚደረጉ የእርስ በእርስ ልምምድ ጨዋታዎች (Small Sided Games) በሚሰጠው ትንተና እና አተገባበርሩ ላይ በነበረው አቀራረብ የጊዜው ማስተር ነበር፡፡ ይህ የልምምድ ፕሮግራም ተጫዋቾቹ አመቱን ሙሉ ያለ ድካም እንዲዘልቁ አግዟቸዋል፡፡ ሰውነት ቢሻው ደግሞ ከምዕራባዊያን የተጫዋቾች አያያዝ እና የቡድን አመራር ጋር የሚቀራረብ ባህርይ ያለው አሰልጣኝ ነበር፡፡ እንደውም በ1998 የሴካፋ ዋንጫን አሸንፈን ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ አውሮፕላን ውስጥ ከጎኔ ተቀምጦ ከነበረው አንተነህ ፈለቀ ጋር ስናወጋ ያነሳልኝ ሀሳብ ለዚህ ማጠናከርያ ይሆንልኛል፡፡ ‹‹ እድሉ ፤ ስዩም አባተ እያሰለጠነን ሰውነት ቢሻው የቡድን መምራት ስራውን ቢይዝ ለአለም ዋንጫ ማለፍ እንችል ነበር፡፡ ››

በአጠቃላይ ሁሉም አሰልጣኞች የየራሳቸው የሆነ በስልጠናው አለም አስፈላጊ የሆኑ ችሎታዎች አሏቸው፡፡ ጥልቅ ጥናት ቢደረግባቸውም ብዙ የሚነገር ጠንካራ ጎን እናገኝባቸዋለን፡፡


በዚሁ አያይዘን አንተ ወደ አሰልጣኝነት እንድትመጣ ተፅእኖ ያሳረፉብህ አሰልጣኞችን እንመልከት..

በተጫዋችነት ዘመኔ ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞች እና የእኔ ምርጫ የሆነው የግራ ዘመም እግርኳሳዊ አቀራረብን የሚከተሉ እንደ ስዩም አባተ ፣ ክፍሌ ቦልተና እና ውበቱ አባተ መሰል አሰልጣኞችን ልጠቅስ እችላለሁ፡፡ ከውጭው አለም ደግሞ በስፓኒሽ እና ደች የእግርኳስ ሲስተም ውስጥ ያለፉት ሉዊ ቫንሃል እና ፔፕ ጓርዲዮላ ይመቹኛል፡፡ የአነሱን ፍልስፍናን መከተልም እፈልጋለሁ፡፡ በቡድን እና ተጫዋቾች አስተዳደር ጥበብ ደግሞ ከካርሎ አንቼሎቲ እና ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ብዙ ነገሮች መቅሰም እፈልጋለሁ፡፡ እነዚህ አሰልጣኞች በቡድን አመራር እና ታክቲካል ጉዳዮች ላይ ያሳተሟቸውን መጽሀፎችንም እጠቀማለሁ፡፡


ከተጫዋቾች አያያዝ ፣ ሀሳባቸውን ከማስተላለፍ እና ሽንፈትን ከመቀበል ጋር በተገናኘ አሰልጣኞቻችን ያላቸው ሁኔታ ምን ይመስላል?

በሁለት አይነት መንገድ አየዋለሁ፡፡ የመጀመርያው ሽንፈትን በፀጋ ተቀብለው ወደ ስኬታማነት መመለስ እንደሚችሉ የሚያምኑ አሰልጣኞች አሉ፡፡ እነዚህ አሰልጣኞች በመሸነፍም ሆነ በማሸነፍ ወቅት ኃላፊነትን የሚወስዱ ናቸው፡፡ በሽንፈት ወቅት ተጫዋቾቻቸውን ሰበብ የማያደርጉ እና ለቀጣዩ ጨዋታ ትኩረት የሚሰጡ አሰልጣኞች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተደጋጋሚ ሽንፈት በሚያመጣባቸው ጫና ኃላፊነቱን ወደ ተጫዋቾቹ በማምጣት ከተጠያቂነት ለመሸሽ ሲጥሩ የሚታዩ አሰልጣኞችም አሉ፡፡

አንጋፋዎቹ አሰልጣኞች በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያየ ባህርይ አላቸው፡፡ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ከሽንፈት በኋላ ረዘም ላለ ጊዜ ንግግር የሚያደርግ እና ቀጣዩን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ የሚከትህ አሰልጣኝ ነው፡፡ አንድ ጨዋታ ከተሸነፈክ ‹‹ ቀጣዩን ጨዋታ እናሸነፍና ከአስራት ቁጣ እንገላገል ›› የሚባልለት አሰልጣኝ ነበር፡፡ ይህም ለቀጣዩ ጨዋታ በከፍተኛ ትኩረት እንድንዘጋጅ የማድረግ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ አስራት ስንሸነፍ የሚቆጣውን ያህል ስናሸንፍም ተጫዋቾቹን የማመስገን ባህርይ አለው፡፡

ስዩም አባተን ስትመለከት በማሸነፍም ሆነ በመሸነፍ ወቅት በተጫዋቾቹ የመደሰትም ሆነ የመበሳጨት ፊት/ስሜት አያሳይም፡፡ ስዩም ይበልጥ ትኩረት የሚሰጠው ለቀጣዩ ጨዋታ በሚደረገው ዝግጅት ላይ ነው፡፡ ስዩም ላይ አንደ ችግር የሚነሳው ነገር ለቋሚ 11 እና ለተቀሩት የቡድን አባላት የሚሰጠው ሚዛናዊ ያልሆነ ትኩረት ነው፡፡ በቋሚ 11 ላይ ያለው እንክብካቤ እና በሌሎቹ መካከል ያለው ልዩነት ከፍተኛ ነበር፡፡ ምናልባት ይህንን የምመለከተው ከቋሚ 11 ውጪ ያሉ ተጫዋቾች በቋሚዎቹ ደረጃ ላይ ለመገኘት እንዲጥሩ ለማነሳሳት ይመስለኛል፡፡

ወደ ሰውነት ቢሻው ስንመጣ ከላይ የጠቀስናቸውን አሰልጣኞች ቅይጥ ባህርይ የያዘ ነው፡፡ ተጫዋቾቹ ላይ ተዝናኖት የመፍጠር ችሎታ ያለው እንደመሆኑ ተጫዋቾቹም ሜዳ ላይ ያላቸውን ሁሉ እንዲሰጡ የማድረግ ስነልቦናዊ ስራ ይሰራል፡፡ ተጫዋቾች ለሰውነት ሙቱ ቢባሉ የሚሞቱለት አይነት አሰልጣኝ ነው፡፡

የቅርብ አመታቶቹን ስንመለከት ውበቱ አባተ ፣ ክፍሌ ቦልተና እና ገብረመድህን ኃይሌ በእረፍት ሰአት ላይ ባላቸው እርጋታ ይታወቃሉ፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነው ነገሮችን ቀለል አድርገው መግለፅ ፣ ለተጫዋቾች መተላለፍ የሚገባቸው መሰረታዊ ነገሮች ላይ ብቻ የማተኮር ዝንባሌ አላቸው፡፡


በጨዋታ ወቅት የአሰልጣኞች ምክርን በተመለከተ ይዘቱ ላይ የስፖርት ቤተሰቦች ጥርጣሬ አላቸው፡፡ ተጫዋቾች ተገቢውን ምክር አያገኙም የሚል ነገርም ይነሳል…

እዚህ ጋር የተጫዋቾችን ድክመት ነው የምትመለከተው፡፡ ምክሮችን ለመቀበል ያለው ፍለጎትም አናሳ ነው፡፡ ‹‹ ባክህ ዝም በለው ፣ እገሌን ያዘው ሊልህ ነው ›› የሚሉ አሉ፡፡ አሰልጣኞቹ የሚሰጡት ምክር ግን እኛ በእንቅስቃሴ ውስጥ ሆነን የማናስተውላቸውን ጉዳዮች ነው፡፡ ከመስመርህ ወጥተሃል ፣ የተጋጣሚ ተጫዋችን ያዝ ፣ ለእገሌ እንዲህ ብለህ ንገረው የመሳሰሉትን ይመክራሉ፡፡


አሁን አሁን ሁለት ረዳት አሰልጣኞችን መቅጠር እየተለመደ መጥቷል፡፡ በጨዋታ ወቅት እና በልምምድ ሜዳ ያላቸው አስፈላጊነት ምንያህል ነው? በጨዋታ ወቅት ረዳቶቹ በየፊናቸው ለተጫዋቾች ትዕዛዝ ሲያስተላለፉ መመልከት ግርታን አይፈጥርም? 

እኔ ይህንን በአዎንታዊ ጎኑ ነው የምመለተው፡፡ በተለይ በልምምድ ወቅት የሰው ኃይል ማነስ የሚፈጥረው ክፍተትን ይደፍናል፡፡ የተለያዩ የልምምድ ስራዎችን በተለያየ ዲፓርትመንት ከፋፍሎ ለማሰራት ይጠቅማል፡፡ ዋናው ነገር ተግባብቶ የመስራት እና ምክትሎቹን በአግባቡ የመጠቀም ጉዳይ ነው፡፡ በጨዋታ ወቅትም ቢሆን ምክትል አሰልጣኞቹ ለዋናው አሰልጣኝ በጨዋታው ሒደት የሚፈጠሩ ስህተቶችን እና የመፍትሄ ሀሳባችን ለመንገር ይረዳል፡፡


ከውጪ ስለሚመጡ አሰልጣኞች ያለህ ምልከታ ምን ይመስላል?

የውጪ አሰልጣኞችም ሆነ ተጫዋቾች መምጣትን እንደበጎ አሳቢ ሳየው በግሎባላይዜሽን ዘመን ላይ እንደመገኘታችንም መምጣታቸውን ላልቃወም እችላለሁ፡፡ ነገር ግን አሁን ባለን የእግርኳስ ስርአት ላይ የውጪ ተጫዋቾችም ሆኑ አሰልጣኞች መምጣታቸው የሚፈጥረው ለውጥ አይኖርም፡፡ ምናልባት ክለቦቻችን ወደ ውጪ ያማተሩት ከኛ ሀገር አሰልጣኞች የሚፈልጉትን ስላላገኙ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ፌዴሬሽኑ የሚፈጥረው ሲስተም ወሳኝ ነው፡፡ ኮታ እና ገደብ ሊኖር ይገባል፡፡ ከፕሪምየር ሊጉ ውጪ ያሉ ክለቦች ምንም የውጪ ዜጋ እንዳይቀጥሩ የማድረግ ገደብ እንዲሁም የፐሪምየር ሊጉ ክለቦች የሚያስፈርሟቸው ተጫዋቾች ላይ ኮታ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ እንደኔ ግን ጥራት ያለው እግርኳስ አስክናዳብር ድረስ ክልከላ ቢኖር እመርጣለሁ፡፡ የእግርኳስ የጥራት ደረጃችን ከፍ ካለ እና አመቺ ሲስተም ከተዘረጋ በኋላ የውጪ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ቢመጡ እግርኳሱ ላይ አዎንታዊ ነገሮችን መጨመር ይችላሉ፡፡ ለዚህ ተግባራዊነት ደግሞ የፌዴሬሽኑ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡


ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የመነጋገርያ ርዕስ ከሆኑ አብይ ጉዳዮች አንዱ የጂኬ ሀሳብ ነበር፡፡ ስለስልጠናው ያለህ ግንዛቤ እና  አስተያየት ምን ይመስላል?

በግንዛቤ ደረጃ ከእኔ ይልቅ በስሩ ያለፉ እና አሁን በማሰልጠን ስራ ውስጥ የገቡት ደብሮም ሀጎስ እና ካሊድ መሐመድ የተሻለ ኣረዳድ ያላቸው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ ተጫዋቾች በካሳዬ ቡድን ውስጥ የInverted role (ከተፈጥሮአዊ መስመራቸው በተቃራኒ መስመር የሚሰለፉ ተጫዋቾች ሚና) በመስጠት የቡድኑ ዋንኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማዕከል የነበሩ በመሆናቸው ከሌላው የተሻለ እውቀቱ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ስላልሰለጠንኩበት ጋዜጣ ላይ ባነበብኩት እና በምሰማው ብቻ ላስረዳ ብል ቁንፅል ሀሳብ ይሆንብኛል፡፡ ነገር ግን ጂኬ ለእግርኳሱ መፍትሄ ይሆናል ከተባለ በሳይንሱ ዘርፍ እንዳለው የችግር አፈታት ዘዴ ሊታይ ይገባዋል፡፡ ከሁሉም በፊት ችግሩን የመለየት ስራ መስራት ፣ ለችግሩ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ አማራጭ ሀሳቦችን ማፍለቅ ፣ በቀረቡት አማራጮች ላይ ግምገማ ማድረግ ፣ ከቀረቡት አማራጮች የተሻለውን መምረጥ ፣ በመጨረሻም መፍትሄውን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማነቱን አይቶ ድምዳሜ መድረስ በሚለው የሳይንስ ሒደት ሊታይ ይገባዋል፡፡ ሀሳብ ካለ መሬት ላይ ወርዶ መታየት አለበት፡፡ በተግባራዊነት ሒደቱ ላይ የሚገጥሙትን ችግሮች እና ጫናዎች ተቋቁመህ መውጣትም አለብህ፡፡


ስለ ወቅታዊ ጉዳዮች…


በሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን አሰልጣኝ ሆነህ እየሰራህ ትገኛለህ፡፡ አምና በኢትዮጵያ ቡና ከመስራትህ አንጻር ወደ አንደኛ ሊግ ያደረግከውን ሽግግር እንዴት አገኘኸው?

ወደ ዝቅተኛ ሊግ ወርዶ መስራት ብዙ ነገሮችን ከስር መሰረቱ እንድረዳ ያግዘኛል፡፡ ከታች ወደ ላይ በሚኖረው እድገት ውስጥ እግርኳሱን በጥልቀት ለማወቅ ጥሩ አጋጣሚንም ይፈጥራል፡፡ ብዙ ክለቦች ተሳታፊ የሚሆኑበት ውድድር በመሆኑ ሰፊ ልምድ አገኝበታለው፡፡

አምና ቡናን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት በተረከብክባቸው የመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ላይ የነበረው ጫና ለዚህ አስተዋፅኦ አድርጓል ማለት እንችላለን?

እንደ ቡና ባለ ክለብ ውስጥ ስታሸንፍም ሆነ ስትሸነፍ ጫና መኖሩ አይቀርም፡፡ ይህን ደግሞ በተጫዋችነትም ጭምር ስለለመድኩት ጫና የመቋቋም ልምድ ሰጥቶኛል፡፡ በቡና ጊዜያዊ አሰልጣኝነት ያሳለፍኩት አጭር ጊዜ ውሳኔዎችን በአግባቡ የማሳለፍ ችግር እንዳይኖርብኝ አድርጎኛል፡፡ ለምሳሌ ከኤሌክትሪክ ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይ ሀሪሰን ኳሱን መስርቶ በመጫወት እንዲጀምር ትዕዛዝ አስተላልፌ ነበር፡፡ ተጫዋቹ ትዕዛዜን ያለመቀበል ምልክት ቢያሳይም ማለት ነው፡፡ በወቅቱ ለዚህ አጨዋወት የሚሆን ግብ ጠባቂ ቢኖር ኖሮ ቅድሚያ እሰጠው ነበር፡፡ አሰልጣኝ የቡድን ወሳኝ ሰው ነው፡፡ ስለዚህም ተጫዋቾችን የመምራት እና ውሳኔ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ በጨዋታው የተከሰተውም ይኸው ነበር፡፡

ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃንን እንደተረከብክ የሰራሃቸው ስራዎች ምንድን ነበሩ?

ክለቡን ከተረከብኩ 16 ቀናት ሆኖኛል፡፡ (ቃለ መጠይቁን በሰጠበት ወቅት) እነዚህ ቀናትንም በምልመላ በተለይ ሰሜን ሸዋን ማዕከል ካደረጉ አካባቢዎች ባደረግነው ምርጫ 30 የሚሆኑትን በመለየት ወደ ዝግጅት ገብተናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለማስፈረም የምፈልጋቸውን ተጫዋቾች በበጀት እጥረት እና ዘግይቼ ቡድኑን በመያዜ ምክንያት ያሰብነውን ያህል ቡድናችንን ማጠናከር አልቻልንም፡፡

ቡድኑን ስትረከብ የነበሩ ችግሮች ሁኔታዎችን አስቸጋሪ አላደረገብህም?

የመጀመርያው ቡድኑ በመፍረስ እና መቀጠል አጣብቂኝ ውስጥ የነበረ መሆኑ የዝግጅት መዘግየት እና አሉታዊ የስነ ልቦና ተጽእኖ አሳድሯል፡፡ የምንፈልጋቸውን ተጫዋቾችም በገበያው ላይ እንዳናገኝ የሚያደርግ የበጀት እጥረት ሌላኛው ችግር ነበር፡፡ በጀት ቢኖርም ዘግይተን ወደ ገበያው በመግባታችን ብቁ ተጫዋቾችን ማግኘት አንችልም በነር፡፡ ሌላው በቡድኑ መውረድ ምክንያት በርካታ ነባር ተጫዋቾች ለቀው ነበር፡፡

እንዲህ አይነት ቡድን ስትረከብ በእቅድ ደረጃ ያስቀመጥከው ግብ ምንድን ነበር?

እቅዴ ቡድኑን በብሔራዊ ሊግ ማቆየት ሲሆን ለወጣቶች እድል በመስጠት ልምድ እና እንዲያገኙ በማድረግ መሰረት ያለው ቡድን በመስራት በሒደት ወደ ከፍተኛው ሊግ መመለስ ነው፡፡ ይህም ክለቡ ካስቀመጠው እቅድ ጋር ተቀራራቢ መሆኑ አመቺ ሁኔታን ይፈጥርልኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *