የአሰልጣኝ ሹም ሽር በደራበት በዚህ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ሌላው ከአሰልጣኙ ጋር የተለያየ ክለብ ሆኗል።
በ2009 የውድድር አመት ቡድኑን የተረከቡትና ዘንድሮ ከ7 ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ በማስመዝገብ በደረጃ ሰንጠረዡ 13ኛ ላይ እንዲቀመጥ ያደረጉት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝነት ያቀረቡት የልቀቁኝ ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ በይፋ ከቡድኑ ጋር መለያየታቸውን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው ደብዳቤ ለማወቅ ችለናል። ረዳት አሰልጣኙ ስምዖን አባይም ክለቡን በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት የሚመራ ይሆናል።
አሰልጣኙ ትላንት በነበረው የልምምድ ፕሮግራም ላይ እንዳልተገኙ የታወቀ ሲሆን በዛሬው እለት በማለዳው በረራ ከድሬዳዋ ለቀው እንደወጡ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የቀድሞው የሲዳማ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ አሰልጣኝ በክረምቱ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት በሊጉ ደረጃ ምርጥ የሚባሉ ተጫዋቾችን ቢሰበስቡም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ባለማስመዝገባቸው እና ደጋፊዎች የሚፈልጉትን ማጥቃት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ባለማሳየታቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ሲነሳባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡
አሰልጣኝ ዘላለም በቀጣይ የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ እንደሚሆኑ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል።