በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከ ፋሲል ከተማ። ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ከዋና አሰልጣኛቸው ዘላለም ሽፈራው ተለያይተው በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ እየሀመሩ ወደ ሜዳ የገቡት ድሬዳዋዎች በ22ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም ኢሳያስ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል።
በ51ኛው ደቂቃ ጀማል ጣሰው በኤርሚያስ ኃይሉ ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራምኬል ሎክ አስቆጥሮ ፋሲል አቻ አድርጓል ። በ71ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዎች የፍጹም ቅጣት ምት ቢያገኙም ሱራፌል ዳንኤል መቷት የግቡን ቋሚ ነክታ ወጥታለች፡፡
የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች በጨዋታው ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ምንተስኖት ጌጡ – ፋሲል ከተማ
” ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። እንደተጀመረ እስከ 20 ደቂቃ እኛ የተሻልን ነበርን። የጎል እድሎችን ፈጥረን ነበር። ከዛ እነሱ ካገቡ በኃላ ደሞ እነሱም ጥሩ መሆን ቻሉ። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ተመጣጣኝ የነበረ ሲሆን የመጨረሻ 10 ደቂቃ ላይ ግን ጫና አብዝተውብን ነበር። እኛም ውጤቱን ለማስጠበቅ ተከላክለን ተጫውተናል። በውጤቱ አልተከፋሁም። ”
ስምዖን ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ
“ውጤት ይዘን ለመውጣት ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። ዛሬ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ አዳዲስ ወጣት ተጫዋቾችን ምክረናል። ያም ደግሞ ትንሽ ክፍተት ነበረው። ሆኖም ግን ከሁለት ተከታታይ ነጥብ መጣል በኃላ የተሻለ ውጤት ለመያዝ ጥረት አድርገናል። አቻ ውጤቱ ግን የሚያስከፋ አደለም ብዬ ነው የማስበው፡፡ “