የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ ጊዜያዊ ዋና ፀሃፊ መሾሙ ሲታወቅ የውድድር እና የማዘውተሪያ ስፍራዎች ዳይሬክቶሬት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ በጊዜያዊ ዋና ፀሃፊነት ተሹመዋል፡፡ አቶ ሰለሞን በጊዜያዊነት በዋና ፀሃፊነት ስታገለግል የቆየችው መስከረም ታደሰን በመተካት አዲሱ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እስኪመረጥ ድረስ የሚዘልቁ ይሆናል፡፡
የመስከረም በቦታው መነሳት የተለየ ምክንያት ይኖረው ይሆን ተብለው በሶከር ኢትዮጵያ የተጠየቁት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ጁነይዲ ባሻ ወ/ሪት መስከረም በስራ ጫና ምክንያት እንደተነሱ ገልፀዋል። “አሁን የቻን ውድድር ሞሮኮ ላይ ስላለ በአዘጋጅ ኮሚቴው ከኢትዮጵያ የተመረጠችው መስከረም ነች፡፡ የውድድር ጊዜው ረጅም እና ሃገርን ወክሎ መስራትም ትልቅ ነገር ስለሆነ በጊዜያዊነት አቶ ሰለሞን ወደ ቦታው መጥተዋል፡፡ እሷንም ይሁን አቶ ሰለሞንን በጊዜያዊነት ነው የሾምነው፡፡” ብለዋል፡፡
ፌዴሬሽኑ ከ2007 መጨረሻ ጀምሮ ሶስት ጊዜያዊ ዋና ፀኃፊዎችን ሾሟል፡፡ ከዚህ ቀድም ዋና ፀሃፊ የነቡት አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በአስተዳደር ችግር የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣሪያ ውጪ ሲሆኑ ከስልጣናቸው የተነሱ ሲሆኑ የኋላ ኋላ ሊሱዎቹ ወደ ማጣሪያው መመለስ ቢችሉም የፌዴሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት የነበሩት አቶ ወንድምኩን አላዩ በጊዜያዊ ዋና ፀኃፊነት እስከ ህዳር 2010 አገልግለው ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ለቀዋል፡፡ ሌላዋ ጊዜያዊ ዋና ፀኃፊ መስከረም በበኩሏ ለአስመራጭ ኮሚቴው እገዛ ስታደርገ ቆይታለች፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጥር 5 በሰመራ ከሚደረገው ምርጫ በኋላ ቋሚ ዋና ፀሃፊ እንደሚሾም ይጠበቃል፡፡