የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፈዴሬሽን (ካፍ) ረቡዕ ምሽት በጋና ርዕሰ መዲና አክራ ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የአመቱ ምርጥ አርቢትር እና በአፍሪካ ሊጎች ውስጥ የሚጫወት የአመቱ ምርጥ የአፍሪካ ተጫዋች ሽልማቶች ከአቲዮ የካፍ ሽልማት ዝርዝር ውስጥ የመሰረዛቸውን ምክንያት ይፋ አድርጓል፡፡
ካፍ የመጨረሻ እጩዎችን ከሳምንታት በፊት ሲያሳውቅ እኚህ ሁለት ዘርፎችን መዝለሉ የሚታወስ ሲሆን በሽልማቶቹም ዙሪያ ምንም መገለጫ ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡ ዛሬ ምሽት ከሚደረገው የካፍ አቲዮ ሽልማት አስቀድሞ በተሰናዳው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የካፍ ፕሬዝደንት አህመድ አህመድ ዝርዝሮቹ ለምን እንደተሰረዙ አሳውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያዊው አርቢትር ባምላክ ተሰማ እጩ ሆኖ ቀርቦበት የነበረው የአርቢትሮች ሽልማት ለብልሹ አሰራር መንገድ የሚከፍት በመሆኑ እንዲሰረዝ እንደተወሰነ አህመድ ገልፀዋል፡፡ “ጥሩ የተባሉት አርቢትሮች ሁሌም ትልቅ የሆኑ ጨዋታዎች በአህጉሪቱም ሆነ በውጪ ሃገራት ይመራሉ፡፡ ይህ በራሱ ሽልማታቸው ነው፡፡ ካፍ ሙስናን በአርቢትሮች ኢንደስትሪ ውስጥ ማበረታታት አይፈልግም፡፡ ይህ ሽልማትም ለብልሹ አሰራር በር ከፋች ነው፡፡” ብለዋል፡፡
የአርቢትሮች ሽልማት በቀደም ባሉ ዓመታት ሲሰጥ የነበረ ሲሆን ጋምቢያዊው ባካሪ ፓፓ ጋሳማ በተከታታይ የሽልማቱ አሸናፊ መሆን ችለው ነበር፡፡ በዘንድሮው ሽልማት እጩነት ውስጥ ተካቶ የነበረው ባምላክ በ2017 ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ውድድሮች መምራት የቻለ ሲሆን ዓለም ዋንጫ ላይ ይዳኛሉ ተብሎ ከሚጠበቁ አርቢትሮች መካከል አንዱ ነው፡፡
አህመድ ሲቀጥሉ በአፍሪካ ውስጥ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሰጠው ሽልማትም መቅረቱን ተናግረዋል፡፡ “አንድ ምርጥ ነው ሊኖር የሚችለው፡፡ በአፍሪካ ሊጎች ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾችም በአፍሪካ ምርጥ መሆን ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ለዚህ የተለየ ሽልማት መዘጋጀት አለበት የሚል እምነት የለንም፡፡” ብለዋል፡፡
ዛሬ ካፍ ሽልማት በአክራ የሚከሄድ ሲሆን በታዳጊ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አሰልጣኞች፣ ብሄራዊ ቡድኖች እና ተጠባቂው የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት አሸናፊዎች የሚታወቁ ይሆናል፡፡