የ10ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ ዛሬ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ተደርጎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሁለት ጎል አልባ ጨዋታዎች በኃላ በአበባው ቡጣቆ ሁለት ቅጣት ምቶች እና በአዳነ ግርማ የግንባር ጎል ጅማ አባ ጅፋርን 3-0 አሸንፏል።
ጨዋታው ባሳለፍነው ሳምንት ጅማ ላይ የተካሄደውን የጅማ አባ ቡናን እና የስልጤ ወራቤን የከፍተኛ ሊግ ጨዋታ ዳኝቶ ሲመልስ ለእልፈት የተዳረገውን የፌዴራል ረዳት ዳኛ ሀብቱ ኪሮስን አጭር የህይወት ታሪክ በማሰማት እና የህሊና ፀሎት በማድረግ ነበር የጀመረው።
ጉዳት አጋጥሟቸው የነበሩትን ኦኪኪ አፎላቢ ፣ ተመስገን/ገኪዳን ፣ ዮናስ ገረመው እና ሔኖክ ኢሳያስን በቋሚ አሰላለፉ ውስጥ አካቶ ጨዋታውን የጀመረው ጅማ አባ ጅፋር በሰሞንኛው አሰላለፉ 4-4-2 ተጠቅሟል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ከመከላከያ ጋር ያለግብ ከተለያየበት ጨዋታ አብዱልከሪም ኒኪማን እና ጋዲሳ መብራቴን በአዳነ ግርማ እና በሀይሉ አሰፋ የተካ ሲሆን የቦታ ለውጥ በማድረግ ኢብራሂማ ፎፋናን በቀኝ መስመር እንዲሁም አቡበከር ሳኒን በመሀል አጥቂነት ተጠቅሟል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታ ግብ ለማስተናገድ ሶስት ደቂቃዎች ብቻ አስፈልገውታል። 3ኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት የተሰጠውን ቅጣት ምት አበባው ቡጣቆ ነበር በቀጥታ በመምታት ያስቆጠረው። ከግቡ መቆጠር በኃላም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደተጋጥሚ ሜዳ ከደረሱ በኃላ ወደ መስመር አጥቂዎቻቸው በሚላኩ ኳሶች ጫናቸው ቀጥሎ ታይቷል። 11ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ሳኒ ከቀኝ መስመር ተከላካዮችን አልፎ ግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ ድረስ ከደረሰ በኃላ የተነጠቀው ኳስ ቡድኑ ብልጫ በወሰደባቸው ደቂቃዎች የተፈጠረው የተሻለ የግብ ዕድል ነበር። 8ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ከሳጥን ውጪ ሞክሮ ኢላማውን ሳይጠብቅለት ከቀረው ኳስ ውጪ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተዳክመው የታዩት አባ ጅፋሮች ከ15ኛው ደቂቃ በኃላ የተጨዋቾችን ቦታ በማሸጋሸግ ኦኪኪ አፎላቢን በብቸኛ አጥቂነት በመጠቀም እና ተመስገንን ወደ ቀኝ መስመር በማውጣት የኳስ ቁጥጥራቸው የተሻለ ጉልበት እንዲኖረው አድርገዋል። ሆኖም ያሰቡትን ለውጥ በቶሎ ማግኘት አልቻሉም። በፍጥነት ጎል ማስተናገዳቸውን ተከትሎ በሚመስል ሁኔታም ቅብብሎቻቸው የሜዳውን አጋማሽ እንዳለፉ በቀላሉ ሲቋረጡ ይታይ ነበር። ጨዋታውም ከመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች በኃላ የተጨዋቾች ግጭት እና ተደጋጋሚ የቅጣት ምቶች የተበራከተበት ነበር። ጅማዎች የኳስ ቁጥጥራቸው ባልተረጋጋበት በነዚህ ደቂቃዎችም የተሻለ የግብ ዕድል የፈጠሩት ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነበሩ። በዚህም 12ኛው ደቂቃ ላይ አዳነ ግርማ ከምንተስኖት አዳነ ተቀብሎ ከሳጥን ውስጥ የሞከረው እና ምንተስኖት 28ኛው ደቂቃ ላይ ከጅማ የመሀል ተከላካይ ቢኒያም ሲራጅ ቀምቶ ከቅርብ ርቀት የሞከረው ኳስ ተገቢው ጉልበት ቢኖራቸው ጎል መሆን የሚችሉ ናቸው። ቀስ በቀስ የኳስ ቁጥጥራቸው እስከ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል መዝለቅ የቻለው አባ ጅፋሮች በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። 34ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ከቀኝ መስመር የጣለውን ኳስ ደጉ ደበበ በግንባር ሊያወጣ ሲሞክር የአቻነት ጎል ለማግኘት ተቃርበው የነበሩት ጅማዎች የማጥቃት ተሳትፎው እየጎላ የመጣው ቀኝ መስመር ተከላካያቸው ሔኖክ አዱኛ ከቀኝ በኩል አንድ ጊዜ ከቅጣት ምት ሌላ ጊዜ ደግሞ ከጨዋታ እንቅስቃሴ ያሻማቸውን ኳሶች ኦኪኪ አፎላቢ እና ይሁን እንዳሻው ይጠቀሙበትት ቀሩ እንጂ ቡድኑ ከፈጠረው ጫና የተገኙ ጥሩ ዕድሎች ነበሩ።
ሁለተኛው አጋማሽ ቡድኖቹ በኳስ ቁጥጥሩ የበላይ በመሆን የግብ ዕድሎችን ለማግኘት የተፎካከሩበት ነበር። ሆኖም ቅዱስ ጊዮርጊስ ካስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ሌላ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ከሁለቱም በኩል ያልተመለከትንበት እና የተቀዛቀዘ ሆንም ነበር ያለፈው። ይሁን እንዳሻውን ከመጀመሪያው በተለየ መልኩ ለዮናስ ገረመው ቀርቦ እንዲጫወት ያደረጉት አባ ጅፋሮች አሁንም አጥቅቶ ለመጫወት የነበራቸውን ድፍረት አሳይተዋል። በዚህ መልኩ የይሁን እና የአሚኑ ጥምረት በሜዳው አግድሞሽ መሆኑ ቀርቶ በቁመት በመሆኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አማካዮች መሀከል በተለይም ምንተስኖት አዳነ የተሻለ ነፃነት ኖሮት ታይቷል።
ኦኪኪ አፎላቢ ጉዳቱ አገርሽቶበት ከእረፍት መልስ ተቀይሮ ከመውጣቱ ጋር ተዳምሮ አባ ጅፋሮች የተሻለ የኳስ ፍሰት በሚያሳዩባቸው አጋጣሚዎች እንኳን በሳጥን ውስጥ የነበራቸው አስፈሪነት እምብዛም ነበር። ቡድኑ የተሻለ ሊባል በሚችል ሁኔታ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሳትን ውስጥ ሲገኝ የታየው 83ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በኩል በተከፈተ ጥቃት ሲሆን ሔኖክ አድኛ ከቅርበት ያሻማውን ኳስ ሳምሶን ቆልቻ በግንባሩ መሞከር ሳይችል ቀርቷል። የአማካይ መስመር እንቅስቃሴያቸው እንደአብዛኛው ጊዜ ሁሉ ጥሩ መልክ ያልነበረው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተጋጣሚያቸው በማጥቃት ላይ ሰፊ ጊዜውን ከማጥፋቱ እና የቦታ ሽግሽግ ከማድረጉ አንፃር ሊኖራቸው የሚገባውን የበላይነት ባንመለከትም በፈጠሯቸው ጫናዎች ያገኟቸውን የቆሙ ኳሶች በመጠቀም በሰፊ ጎል ማሸነፍ ግን አልተሳናቸውም። 65ኛው ደቂቃ ላይ አዳማ ሲሶኮ በኬይታ ሲዴ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል አካባቢ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ቅጣት ምት አበባው ቡጣቆ በድጋሜ ማስቆጠር ችሏል። 78ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አዳነ ግርማ የበሀይሉ አሰፋን የማዕዘን ምት በግንባሩ በማስቆጠር የፈረሰኞቹን አሸናፊነት አረጋግጧል። እስከመጨረሻው ድረስ ለማጥቃት ከመሞከር ያልተቆጠቡት አባ ጅፋሮች ውጤቱን ማጥበብ የሚችሉበት አጋጣሚ ሳይፈጠርም ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል። ውጤቱን ተከትሎም ነጥቡን 16 ያደረሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሸናፊውን ጅማ አባ ጅፋር የሁለተኛነት ቦታ ተረክቧል።