የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባል እና የውድድር ስነስርአት ሰብሳቢ አቶ አበበ ገላጋይ ፣ የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ልዑል ሰገድ በጋሻው እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ዛሬ በኢንተር ኮንትኔንታል አዲስ ሆቴል በሁለቱም ጾታዎች ለሀያ ሁለት ዋና ዳኞች እና ረዳት ዳኞች ከፊፋ የተላከላቸውን የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ በይፋ ተቀብለዋል።
በርክክቡ ላይ ንግግር ያደረጉት የዳኞች ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው የኢንተርናሽናል ዳኞች ቁጥር እያደገ አረንደሆነ ገልፀዋል። ” በካፍም ሆነ በፊፋ ለኢትዮዽያውያን ዳኞች የሚሰጠው ግምት እና ትኩረት በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ መልካም አጋጣሚ እየፈጠረልን ይገኛል። ይህ ዕውቅና እንዲቀጥል ነባሮቹም አዲሶቹም በርትታቹ በመጠንከር ሙያችሁን በማክበር የሀገራችሁን ስም ልታስጠሩ ይገባል። የዛሬ አራት አመት በወንዶች 2 ኢንተርናሽናል ዳኞች 7 ረዳት ዳኞች ነበሩ ። በሴት በኩል 2 ዋና እና 2 ረዳት ኢንተርናሽናል ዳኞች ብቻ ነበሩ። አሁን ግን 22 በሴትም በወንድም ኢንተርናሽናል ዳኛ መድረሱ ትልቅ ስኬት ነው” ብለዋል።
በመቀጠል ለ22 ዳኞች የፊፋ የኢንተርናሽናልነት ባጅ የተሰጣቸው ሲሆን በወንድ ዋና ኢንተርናሽናል ዳኝነት ባምላክ ተሰማ፣ አማኑኤል ኃይለላሴ፣ ለሚ ንጉሴ ብሩክ የማነብርሃን እና በላይ ታደሰ ነባር ዳኞች ሲሆኑ ለመጀመርያ ጊዜ የኢንተርናሽናልነት ዳኝነት በዋና ዳኝነት ያገኙት ዳዊት አሳምነው እና ቴዎድሮስ ምትኩ ናቸው። በረዳት ኢንተርናሽናል ዳኝነት አዲስ የገባ የሌለ ሲሆን ተመስገን ሳሙኤል ፣ ሸዋንግዛው ተባበል፣ ትግል ግዛው ፣ ክንዴ ሙሴ ፣ ክንፈ ይልማ ፣ ኃይለራጉኤል ወልዳይ እና በላቸው ይታየው ናቸው።
በሴት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኝነት ሊዲያ ታፈሰ ፣ ጌራወርቅ ከተማ ነባር ዳኞች ሲሆኑ አዲስ የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ ያገኙት ፀሀይነሽ ከተማ እና አስናቀች ገብሬ ናቸው። በረዳት ኢንተርናሽናልነት ደግሞ ወይንሸት አበራ እና ወጋየሁ ዘውዴ ነባር ረዳት ዳኞች ሲሆኑ አዲስ የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ ያገኙት ይልፋሸዋ አበበ እና አዜብ አያሌው ናቸው ።
ኢንተርናችናል ዳኝነት ባጁን ካገኙት ዳኞች መካከል አንዱ የሆነው ባምላክ ተሰማ በሰጠው አስተያየት የተሰማውን ስሜት ገልጿል። ” ይህ ቀን ለእኛ ታለቅ በአል ነው። ከዚህ ባሻገር ቃልኪዳን የምንገባበት ቀንም ጭምር ነው። በአሁን ወቅት ዳኝነት ትልቅ ሙያ ነው። ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠይቅ ስራ ሲሆን የሀገራችን ሊግ ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግበት በመሆኑ እያንዳንዱ ጨዋታ የዋንጫ ጨዋታ ነው። ውድድሮችን በብቀት ለመምራት ከፍተኛ እምነት እና ምግባር የሚፈልግ በመሆኑ የአካል ብቃታችንን ማስተካከል ፣ ህጉን ማንበብ ፣ አዳዲስ ህጎችን ማወቅ ያስፈልጋል።” ብሏል።
በመጨረሻም አቶ አበበ ገላጋይ የመዝግያ ንግግር አድርገው የመርሀ ግብሩ ፍፃሜ ሆኗል።