በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ብቸኛ መርሃግብር በአዲስአበባ ስታድየም ኢትዮ ኤሌክትሪክን የገጠመው አዳማ ከተማ ከመመራት ተነስቶ 3-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችሏል፡፡
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሳምንቱ መጀመሪያ ወደ ወላይታ ሶዶ አቅንቶ በወላይታ ድቻ 2ለ0 ከተረታው የቡድን ስብስብ ውስጥ በቅጣት ከቡድኑ በተለዩት ተስፋዬ ነጋሽና በኃይሉ ተሻገር ምትክ ዳንኤል ራህመቶንና ምንያህል ይመር ሲተኩ ከእነሱ በተጨማሪም አዲስ ነጋሽ ከቅጣት መልስ እንዲሁም ተክሉ ተስፋዬን ወደ ቡድን ስብስባቸው በማካተት ጨዋታውን በ4-1-3-2 ቅርጽ መጨመር ችለዋል፡፡ በአንጻሩ እንግዳዎቹ አዳማ ከተማዎች በሜዳቸው ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ ከተለያየው የቡድን ስብስብ ውስጥ አዲስ ህንጻ እና ከነአን ማርክነህን አስወጥተው ሱራፌል ዳኛቸውንና ደሳለኝ ደባሽን በመተካት በ4-4-2 ቅርፅ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡
ሳቢ ባልነበረውና ይህ ነው የሚባል ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ ባልታየበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ እንቅስቃሴ በርካታ ቀጣይነት የሌላቸው ያልተሳኩ ቅብብሎች እንዲሁም ያለአላማ የሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች በርከት ብለው የተስተዋሉበት ነበር፡፡
በሁለቱ መስመሮች በኩል በሚገኙት ፈጣን ተጫዋቾቻቸው ሱራፌል ዳኛቸውና በረከት ደስታ በመጠቀም በፈጣን የመስመር አጨዋወት ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት እንግዶቹ አዳማ ከተማዎች በ28ኛው ደቂቃ አዲስ ነጋሽ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ዳዋ ሆቴሳ ወደ ግብ ከሞከራትና አቡ ሱሊይማን ካዳነበት ኳስ ውጪ ይህ ነው የሚባል የጠሩ የግብ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
በአንጻሩ በመጀመሪያ አጋማሽ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ኤሌክትሪኮች በ16ኛው ደቂቃ ጫላ ድሪባ ከቀኝ መስመር ያሻማትን ኳስ ተጠቅሞ አልሀሰን ካሉሻ የሞከራትና ኳስ በግቡ አግዳሚ የተመለሰበት ኳስ በመጀመሪያ አጋማሽ ከታዩት ሙከራዎች አስደንጋጭዋ ነበረች፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ሁለት ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩ በአዳማ ከተማ የግብ ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ከሶስት ጨዋታ ቅጣት የተመለሰው የኤሌክትሪኩ አምበል አዲስ ነጋሽ አስቆጥሮ የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1ለ0 መሪነት ማሳረግ ችሏል፡፡
ጨዋታውን ከተመልካች ጋር ሆነው ሲከታተሉ የነበሩት አዲሱ የኢትዮ ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ሁለቱ ቡድኖች ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ሲያመሩ ለቡድኑ ጊዜያዊ አሰልጣኞች መልእክቶችን ሲያተላልፉ ተስተውለዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በእጅጉ ተሻሽለው ወደ ሜዳ የገቡት አዳማ ከተማዎች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረስ በርካታ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ በ49ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው አጥቂ ዳዋ ሆቴሳ ሁለት የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከላካዮችን ቀንሶ ያመከናት ኳስም በጣም አስቆጪዋ አጋጣሚ ነበረች፡፡
ይበልጥ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት አዳማዎች በ60ኛው ደቂቃ ኄኖክ ካሳሁን ሱራፌል ዳንኤል ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ በግቧ መቆጠር ይበልጥ የተነቃቁት አዳማ ከተማዎች በ73ኛው ደቂቃ ላይ ከተከላካዮች በረጅሙ የተሻገለትን ኳስ ተጠቅሞ ዳዋ ሆቴሳ የግል ጥረቱን በማከል ማራኪ የሆነች ግብን በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል፡፡ በደቂቃዎች ልዩነት ዳዋ ሆቲሳ ሐት-ትሪክ ሊሰራበት የሚችለውን አጋጣሚ ከኢትዮ ኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ አቡ ሱይይማን ጋር ተገናኝቶ በሚያስቆጭ ሁኔታ አምክኗታል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ፍፁም የበላይነትን ወስደው መጫወታቸውን የቀጠሉት አዳማዎች በ87ኛው ደቂቃ ላይ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ቡልቻ ሹራ የኤሌክትሪክ ተከላካዮች የጨዋታ ውጪ መስመር የመስራት ስህተትን ተከትሎ ያገኛትን ኳስ በማስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሶስት ያሳደገችን ግብ አስገኝቷል፡፡
ኤሌክትሪኮች ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል ካሉሻ አልሀሰን ባስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ውጤቱን ማጥበብ ቢችሉም ጨዋታው በአዳማ ከተማ የ3-2 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
ቅጣው ሙሉ- ኢትዮ ኤሌክትሪክ
” በመጀመሪያው አጋማሽ ከሁለተኛው በተሻለ ጥሩ መንቀሳቀስ ችለናል፤ ነገርግን ያገኘናቸውን የግብ ማግባት አጋጣሚ አለመጠቀማችን ዋጋ አስከፍሎናል፡፡
ተገኔ ነጋሽ-አዳማ ከተማ
“በመጀመሪያው አጋማሽ በተጋጣሚያችን ብልጫ ቢወሰድብንም በሁለተኛው አጋማሽ ስህተቶቻችንን በማረም ጨዋታውን አሸንፈን ለመውጣት ችለናል፡፡”