በ10ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሜዳው ትግራይ ስታድየም ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው መቐለ ከተማ 2-0 በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል።
ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ ሁለቱም ቡድኖች በተወካያቸው አማካኝነት ስጦታ የተለዋወጡ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም መቐለ ከተማዎች ለድሬዳዋ ከተማ 10 የሚጠጉ የማስታወሻ ኳሶች በስጦታ አበርክተዋል።
በ4-2-3-1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገባው መቐለ ከተማ ሀዋሳን ከገጠመው ስብስብ መካከል በተጎዳው አሌክስ ተሰማ ምትክ ኃይሉ ገብረየሱስን ወደ መጀመርያ አሰላለፍ በመመለስ እና አቼምፖንግ አሞስን ከፍቃዱ ደነቀ ጋር በመሃል ተከላካይነት በማጣመር ወደ ሜዳ ገብቷል። ድሬዳዋ ከተማ በአንፃሩ ከፋሲል ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ዘካርያስ ፍቅሬ እና ያሬድ ዘውድነህን በዳኛቸው በቀለ እና አህመድ ረሺድ ምትክ በማስገባት ቀርቧል።
በፈጣን እንቅስቃሴ እና በሙከራዎች ታጅቦ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች እንግዶቹ ድሬ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ሆነው ቢታዩም የግብ ሙከራ በማድረግ በኩል ቀዳሚዎቹ መቐለዎች ነበሩ። በ10ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከሳጥኑ ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ በጀማል ጣሰው በቀላሉ ተመልሶበታል። በእነዚህ 20 ደቂቃዎች መቐለ ከተማዎች በጋይሳ አፖንግ ፣ ድሬዳዋ ከተማዎች በዘካርያስ ፍቅሬ አማካኝነት ጥረት ሲያረጉ ሲስተዋል በ18ኛው ደቂቃ ላይ በመድሃኔ ታደሰ በተሰራው ጥፋት የቅጣት ምት ሲሰጥ ረዳት ዳኛው ወደ ሜዳ በመግባት ከተጫዋቾች ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ ሲገቡ መታየቱም ሌላው በጨዋታው ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች አንዱ ነበር።
ከ25 ደቂቃ በኋላ በነበረው እንቅስቃሴ ድሬዳዋ ከተማዎች ተደጋጋሚ ስህተቶች እና የትኩረት ማጣት ችግሮች የተስተዋሉባቸው ሲሆን በተለይም በ32 ደቂቃ ላይ አማኑኤል የተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው አሞስ አሻግሮለት ጋናዊው ሁለገብ የሞከረውና ሰንደይ ሙቱኩ በልዩ ብቃት ያወጣበት ኳስ ይህን የሚያሳይ ነበር።
በ41ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ጋይሳ አፖንግ በግምት ከ30 ሜትር አክርሮ የመታው ኳስ የጀማል ጣሰው መረብ ላይ አርፋ መቐለን መሪ ማድረግ ችሏል። የመጀመርያው ጎል ከተቆጠረ 1 ደቂቃ በማይሞላ ግዜ ውስጥ በድሬዳዋ ተጫዋቾች ስህተት የተገኝውን ኳስ አማኑኤል በግል ጥረቱ ወደ ውስጥ ይዞ በመግባት አስቆጥሮ የመቐለን መሪነት ወደ 2-0 ከፍ አድርጓል።
በድሬዎች በኩል በመጀመርያው አጋማሽ አንድ ሙከራ ብቻ ማድረግ የቻሉ ሲሆን አትራም ክዋሜ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በፊሊፕ ኢቮኖ ተመልሶበታል።
በሁለተኛው ኣጋማሽ ድሬዎች ዮሴፍ ዳሙዬን በአትራም ኩዋሜ ቀይረው በማስገባት የአማካይ ክፍል ተጫዋቾች ቁጥር በማብዛት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ሲሞክሩ መቐለዎች በአንፃሩ መድሃኔን በያሬድ ከበድ በመተካት ደ 4-4-2 ቅርፅ ተለውጠው ቀርበዋል።
በዚህ የጨዋታ አጋማሽ ድሬዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ቢወስዱም መቐለዎች በመከላከል ወረዳ በቁጥር በዝተው በመንቀሳቀስ ለድሬዎች የጎል እድል የመፍጠርያ ክፍተትን ሳይሰጡ ውጤታቸውን ማስጠበቅ ችለዋል። ድሬዎች በተለይም ከ70 ደቂቃ በኋላ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ዘካርያስ ፍቅሬ በ75ኛው ደቂቃ የመቐለ ተከላካዮችን አልፎ የሞከረውና ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ በድሬ በኩል የሚጠቀስ ሙከራ ሲሆን በ86ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ ዱላ ሙላቱ በጥሩ ሁኔታ ቢያገኘውም ኢማኑኤል ላርያ ያወጣበት ኳስ በመቐለ በኩል የግብ ልዩነቱን ልታሰፋ የምትችል አጋጣሚ ነበረች።
ጨዋታው በመቐለ ከተማ 2-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ በአመቱ ለሁለተኛ ጊዜ በሜዳው ድል የቀናው መቐለ ከተማ ነጥቡን 14 በማድረስ ወደ6ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ከአንደኛው ሳምንት በኋላ ከድል ጋር የተራራቀው ድሬዳዋ ከተማ በ8 ነጥብ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ገብቷል።