በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ሲዳማ ቡና ትላንት በሜዳው ሀዋሳ ከተማን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል። ሙሉ የጨዋታው ክፍለጊዜ ተጠናቆ አዲስ ግደይ ላይ በተሰራ ጥፋት በተሰጠው የፍፁም ቅጣት ራሱ አዲስ መትቶ የሀዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳ መልሶበት የተሻማውን የማዕዘን ምት አዲስ በግንባሩ በመግጨት ሲዳማን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አስጨብጧል።
አዲስ ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ጎሉ የተለየ ስሜት እንደፈጠረበት ተናግሯል። ” ጨዋታው በጣም ፈታኝ ነበር። ደርቢ እንደመሆኑ እና ጎሉንም ያስቆጠርነው ባለቀ ሰአት ላይ እንደመሆኑ በጣም ፈተና የበዛበት እና ጫና የነበረው ጨዋታ ነበር። ግቧ በኔ በኩል ልዩ ስሜት ፈጥሮብኛል። ምክንያቱም ባለቀ ሰአት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተን እኔ አምክኜው ነበር። ከዛ መንፈስ በቅፅበት ነው ጎሉ ሊቆጠር የቻለው። ለኔ በጣም ልዩ ስሜት አለው። ” ብሏል።
በውድድር አመቱ ሲዳማ ቡና የተቀዛቀዘ ጊዜ እያሳለፈ ቢገኝም አዲስ ግደይ በግሉ መልካም እንቅስቃሴ እያሳየ ይገኛል። የግብ እድሎችን ወደ ጎልነት የመቀየር ብቃቱ እየተሻሻለ ሲሆን እስካሁንም በ8 ጨዋታዎች 5 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። አዲስ ከዚህም በላይ መሻሻል እንደሚፈልግ ይናገራል። ” በጥሩ አቋም ቡድኔን ካለሁበት በተሻለ ለማገልገል እፈልጋለሁ። ከጊዜ ወደ ጊዜም ራሴን ማሻሻል እፈልጋለሁ። በሒደት ለውጦችን እፈልጋለሁ። ወደ ውጪ ሀገራት ክለቦች ለማምራት መንገዶችን እያመቻቸው ነው። ለሲዳማ ቡናም ከአመት አመት የተሻለ ነገር ለማድረግም ነው ጥረት የማደርገው ፤ ዘንድሮ ደግሞ ከአምና እና ካችአምና የተሻለ ነገር እያደረኩ ነው። በየጫወታው ግብ ማስቆጠሬን መቀጠል እና ለሲዳማ ቡና አሸናፊነት መታገልን እፈልጋለሁ ”
አዲስ ግደይ በመጨረሻም ሲዳማ ቡና በ2009 ወደነበረው ተፎካካሪነት እና ወጥ አቋም እየተመለሰ እንደሆነ ገልጿል። ” በ2009 የውድድር ዘመን ሲዳማ ቡና የተሻለ ውጤት ነበረው። ዘንድሮ ላይ ግን ያን ውጤት መድገም አልቻለም። ሆኖሞ ከጨዋታ ጨዋታ የቀደመው ሲዳማ ቡናን ለመመለስ እየጣርን ነው። በቅርብ ጨዋታዎችም ነጥቦችን እየሰበሰብን እንገኛለን፡፡ “