የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ጥር 5 ሊያደርገው ያቀደው የፕሬዝደንታዊ እና ስራ አስፈፃሚ ምርጫን በተመለከተ የዓለምአቀፉ የእግርኳስ የበላይ አስተዳዳሪ አካል ፊፋ ዛሬ ደብዳቤ ለፌድሬሽኑ ልኳል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዘሪሁን መኮንን ለፊፋ ላኩት በተባለው ደብዳቤ የመንግስት ጣልቃ ገብነት አለ በሚል ምርጫው ምርመራ እንዲደረገብት ማሳወቃቸውን ተከትሎ ፊፋ የመንግስት ጣልቃ ገብነት መኖሩን እና አለመኖሩን ማጣራት እንደሚያደርግ በደብዳቤው ተገልጿል፡፡ የፌድሬሽኑ ምርጫ ህግ እና ስርዓትን ያልተከተሉ የተለያዩ ጉዳዮች ሲንፀባረቅበት የቆየ ሲሆን ፊፋ የመንግስት ጣልቃ ገብነት አለ ብሎ የሚያምን ከሆነ ምርጫው ሊራዘም ይችላል፡፡ ምርጫው የሚራዘም ከሆነም ይህ ለሶስተኛ ግዜ ነው፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ስብሰባ የተቀመጡ ሲሆን ባገኘነው መረጃ መሰረት ውጥረት በስብሰባው ላይ ነግሷል፡፡ የመንግስት ጣልቃ ግብነት የፊፋን ህልውና ከሚፈታተኑ ጉዳዮች ዋነኛው በመሆኑ ፊፋ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ላይ ትግስተኛ ሲሆን አይታይም፡፡ በተደጋጋሚም የመንግስት ጣልቃ ገብነት በእግርኳሳቸው ላይ በታዩባቸው ሃገራት ላይ ቅጣት እና ከአለማቀፍ እግርኳስ ሲያግድ ይስተዋላል፡፡