በ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ቀን መርሃግብር በገልተኛ ሜዳ እንዲደረግ የተወሰነው የፋሲል ከተማ እና መቐለ ከተማ ጨዋታ አዲስአበባ ስታዲየም ላይ በከፍተኛ ውጥረት ታጅቦ ተካሂዶ ያለግብ ተጠናቋል፡፡
ፋሲል ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ አዲስአበባ ስታዲየም ላይ መከላከያን 1ለ0 ከረታው የቡድን ስብስብ ውስጥ በጨዋታው በተመለከተው የቀይ ካርድ በዛሬው ጨዋታ ላይ መሰለፍ ባልቻለው አብዱረህማን ሙባረክ ምትክ የፊት አጥቂው ፊሊፕ ዳውዝን እንዲሁም አማካይ ክፍል ላይ በሄኖክ ገምቴሳ ምትክ ኤፍሬም አለሙን ብቻ በመቀየር በተመሳሳይ 4-3-3 ቅርጽ ጨዋታውን ጀምሯል፡፡
በአንጻሩ መቐለ ከተማዎች ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳቸው ድሬዳዋ ከተማን 2ለ0 ከረታው የቡድን ስብስብ ውስጥ በተከላካይ ስፍራ ላይ ሃይሉ ገ/እየሱስ ምትክ ዳንኤል አድሀኖምን እንዲሁም በመስመር አጥቂው መድሀኔ ታደሠ ምትክ ያሬድ ከበደን በመተካት በ4-2-3-1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
ከጨዋታው መጀመር በፊት የሁለቱም ቡድኖች የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾች እጅ ለእጅ ተያይዘው በመዞር በስታዲየሙ ለታደመው ተመልካች የሁለቱን ቡድኖች አንድነት ለማሳየት ሞክረዋል፡፡
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ፋሲሎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የኳስ ቁጥጥር እንዲሁም ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት በማድረግ በኩል ተሽለው ተስተውሏል፡፡ ሆኖም የጨዋታውን የመጀመሪያ አስደንጋጭ ሙከራ ማድረግ ችለው የነበሩት መቐለ ከተማዎች ነበሩ። በ6ኛው ደቂቃ ላይ አንተነህ ገ/ክርስቶስ ከግራ መስመር በረጅሙ የወረወረውን የእጅ ውርወራ አጥቂው ጋይስ አፖንግ ሲሸርፈው ያሬድ ከበደ ሳይጠበቅ ከፋሲል ተከላካዮች አምልጦ ወደ ግብ የሞከራትን ኳስ የፋሲሉ ግብጠባቂ ሚኬል ሳማኬ በአስደናቂ ሁኔታ አድኖበታል።
ፍፁም መከላከልን መርጠው ወደ ሜዳ የገቡ የሚመስሉት መቐለ ከተማዎች በ4-2-3-1 ቅርፅ መጫወታቸው የፈጠረላቸውን በሜዳው ቁመት የተመጣጠነ የተጫዋቾች ስርጭትን በመጠቀም በመስመሮች መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ ለፋሲል ከተማ የመሀል ሜዳ እንዲሁም የፊት መስመር ተጫዋቾች ጨዋታውን ፈታኝ ማድረግ ችለው ነበር፡፡ ከወትሮው በተለየ በሚታወቁበት ፈጣን የመስመር ማጥቃት አጨዋወት ተዳክመው የተስተዋሉት ፋሲል ከተማዎች ከተከላካይ አማካያቸው ያስር ሙጌርዋ ጎን የተሰለፉት ዳዊት እስጢፋኖስና ኤፍሬም አለሙ ወደ መሀል እጅግ በጠበበ ቅርፅ መጫወታቸው ከተጠቀጠቀው የመቐለ ተጫዋቾች ጋር ተዳምሮ በፋሲል ከተማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ዋንኛ ተዋንያን የሆኑትን ሁለቱ የፋሲል የመስመር አጥቂዎች በተለይም ኤርሚያስ ሀይሉ እንዲነጠሉ ምክንያት ሆኗል፡፡
ደቂቃዎች እየገፉ በመጡ ቁጥር በጣም ከፊት ተነጥለው ይታዩ ከነበሩት ሶስቱ የፋሲል አጥቂዎች መካከል ራምኬል በጥልቀት ወደ መሀል እየተሳበ በመግባት በመሀል ሜዳ ላይ ፋሲሎች የተወሰደባቸውን የቁጥር ብልጫ ለማካካስና ለቡድን አጋሮቹ የተሻሉ ኳሶችን ወደ ፊት ለማድረስ ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል። በ16ኛው ደቂቃ ዳዊት እስጢፋኖስና ራምኬል በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ያለፉትን ኳስ ራምኬል በሚያስቆጭ ሁኔታ ያመከናት ኳስ የዚህ ጥረት ማሳያ ነበረች፡፡
ሁለቱ የመቐለ የመስመር ተከላካዮች ማለትም ዳንኤል አድሀኖምና አንተነህ ገ/ክርስቶስ የእጅ ውርወራ ለመወርወር ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ከገቡባቸው ጥቅት አጋጣሚዎች በስተቀር ከሁለቱ የመሀል ተከላካዮቻቸው ጋር ተዳምረው ለግብጠባቂያቸው እጅጉኑ ቀርበው ሲከላከሉ ተስተውሏል። ከእነሱም በተጨማሪ ከጋይስ ጀርባ ከነበሩት ሶስት የአጥቂ አማካዮች ሁለቱ የመስመር አማካዮች ቡድኑ ኳስ በሚያጣበት ወቅት ለመስመር ተከላካዮቻቸው በመቅረብ የቡድናቸውን ተጋላጭነት በእጅጉ ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና ተወጥተዋል፡፡
ብዙም የግብ ሙከራ ባልተስተዋለበትና ጨዋታውን በመሩት ፌደራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ፌሽካ በተደጋጋሚ ይቆራረጥ በነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ሜዳ ላይ ከነበረው እንቅስቃሴ ይበልጥ እጅግ በርካታ በሚባል ቁጥር ወደ ሜዳ ገብተው የነበሩት የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ማራኪ አደጋገፍ ትኩረትን የሚስብ ነበር፡፡ በ31ኛው ደቂቃ ዳዊት እስጢፋኖስ ከቋመ ኳስ ያሻማውን ከኳስ ተጠቅሞ ፌሊፕ ዳውዝ ወደ ግብ የላካትና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችው ኳስ ሌላው ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ፋሲል ከተማዎች ከመጀመሪያው በተሻለ በጣም ወደ ኃላ በማፈግፈግ ተጠቅጥቆ ሲከላከል የነበረውን መቐለ ከተማን የመከላከል አደረጃጀት ለመስበር ኳሶችን ፈጣን ወደሆኑት የመስመር ተጫዋቾች በመላክ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል በመድረስ አደጋ ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ነገርግን ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅጉን ደካማ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ በ54ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ካሻማትና ፊሊፕ ዳውዝ የመጀመሪያ ኳስ በማሸነፍ ለኤፍሬም አለሙ አቀብሎት ኤፍሬም ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታትና ኦቮኖ ካዳነበት ኳስ ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሊያስመለክተን አልቻለም፡፡
እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ መቐለ ከጋይሳ ጀርባ የነበሩት ሶስቱ አጥቂ አማካዮች የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በሚያገኙበት ወቅት ከተከላካዮቹ ፊት የተሰለፉት አመለና ሃብታሙ የመልሶ ማጥቃት ሂደቱ ላይ እንዳይሳተፉ የተሰጣቸው ሚና ከተከላካዮቹ እንዳይርቁ ስለገደባቸው መቐለዎች ለማጥቃት ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ከተጋጣሚያቸው አንጻር በቁጥር በጣም ስለሚያንሱ ለማጥቃት የሚያደርጉት ጥረት እምብዛም አስፈሪ አልነበረም፡፡ በአንጻሩ ፋሲል ከተማዎች በርካታ የኳስ ቅብብሎችን በሜዳኛው የመሀከለኛው ክፍል ላይ ማድረግ ቢችሉም የተደራጀውን የመቐለ ከተማ የመከላከል ስርአት ጥሰው መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
ጨዋታው 0ለ0 መጠናቀቁን ተከትሎ ፋሲል ከተማ በነበረበት 3ኛ ደረጃ ላይ በ16 ነጥብ ሲረጋ በአንጻሩ መቐለ ከተማ በ15 ነጥብ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
ዮሀንስ ሳህሌ – መቐለ ከተማ
“በአጠቃላይ ጨዋታው ብዙም የማጥቃት እንቅስቃሴ የነበረው ጨዋታ ስላልነበር እምብዛም ለተመልካቾች የሚያስደስት አልነበረም፡፡በግሌ በጨዋታው ሙሉ በሙሉ ደስተኛ አይደለሁም፡፡በጨዋታው ለልጆቻችን የመጣው ደጋፊ ተደስቶ እንዲሄድ ከፍተው እንዲጫወቱ ነበር ያዘዝነው ነገር ግን ብዙ ማጥቃት እየቻልን ሜዳ ላይ ያየነው ነገር ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡”
ምንተስኖት ጌጡ- ፋሲል ከተማ
“በኳስ ቁጥጥር እንዲሁም የጎል እድሎችን በመፍጠር በኩል የተሻልን ነበር ነገርግን የጨዋታው ውጤት ጨዋታውን ባይገልፀውም የግብ እድሎችን ወደ ጎልነት መቀየር ባለመቻላችን አቻ ለመውጣት ተገደናል፡፡ ጨዋታው ከነበረው ጫናና ውጥረት አንጻር በሰላም ተጀምሮ በሰላም መጠናቀቁ ትልቁ ውጤት ነው፡፡”