ሪፖርት | አዳማ ከተማ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ያደረገበትን ድል ቡና ላይ አስመዝግቧል

የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት አዳማ አበበ በቂላ ስታድየም በተደረገው ጨዋታ አዳማ ከተማ ኢትዮዽያ ቡናን 2-1 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አድርጓል

አዳማ ከተማ ወደ አአ ተጉዞ ኢትዮ ኤሌትሪክን 3-2 ከረታበት የቡድን ስብስቡ ውስጥ ታፈሰ ተስፋዬን በቡልቻ ሹራ ፣ ደሳለኝ ደባሽን በአንዳርጋቸው ይላቅ እንዲሁም ሱራፌል ዳኛቸውን በኤፍሬም ዘካርያስ በመተካት በ4-4-2 አሰላለፍ ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርብ በኢትዮዽያ ቡና በኩል የሰርግ ስነ ስርአቱን ዛሬ በፈፀመው ኤልያስ ማሞ ምትክ አማኑኤል ዮሀንስን ፣ በአስናቀ ሞገስ ደግሞ አብዱሰላም አማንን በመተካት በ4-3-3 ቅርፅ ወደ ሜዳ ገብቷል።

የአዳማ አበበ በቂላ ስታድየም ተመልካች ከመያዝ አቅም በላይ እጅግ በርካታ ቁጥር ባለው የአዳማ እና የኢትዮዽያ ቡና ደጋፊዎች የተጨናነቀ ሲሆን መጥቶ የተመለሰውም ተመልካች ቀላል አልነበረም። ለረጅም አመታት የአዳማ ከነማ የልብ ደጋፊ የሆነው በቅፅል ስሙ ‹‹እሙጥሽ›› ዛሬ በስታድየሙ ውስጥ የጋብቻ ስነ ሥርአቱ መፈፀሙ ሌላው ድምቀት ነበር።

ፌደራል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው በጥሩ ብቃት የመራው የዛሬው ጨዋታ ጎሎች ያስተናገደው ብዙም ደቂው ሳይገፋ ነበር፡፡ 4ኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከ18 ሜትር ርቀት ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት በዘንድሮ የውድድር አመት ከአዳማ ከተማ ጋር ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ዳዋ ሁቴሳ ከግቡ አግዳሚ ጋር አጋጭቶ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር አዳማ ከተማን ቀዳሚ ሲያደርግ የውድድር አመቱን አምስተኛ ጎል በስሙ ማስመዝገብም ችሏል። ሆኖም አዳማዎች ደስታቸውን ገልፀው ብዙም ሳይቆዩ ከሁለት ደቂቃ በኋላ እያሱ ታምሩ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ የአዳማ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጭ አቋቋም ነው በማለት መዘናጋታቸውን ተከትሎ ሳሙኤል ሳኑሚ ወደ ግብነት በመቀየር ኢትዮዽያ ቡናን አቻ ማድረግ ችሏል።

በጨዋታው በሁለቱም በኩል ከመስመር በሚነሱ አጥቂዎቻቸው አማካኝነት አደጋ ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች የተሳኩ ነበር፡፡ በኢትዮዽያ ቡና በኩል አስቻለው ግርማ እና እያሱ ታምሩ በአዳማ ከተማ በኩል ዛሬ የቀኝ መስመር አጥቂ ሚና ተሰቶት የነበረው ሱሌይማን ሰሚድ እና በረከት ደስታ የሚያደርጉት የማጥቃት እንቅስቃሴ መልካም የሚባል ነበር።

ከሁለቱም ጎል መቆጠር በኋላ ጠንካራ የጎል ሙከራ የተመለከትነው ሁለት ጊዜ ነበር፡፡ በኢትዮዽያ ቡና በኩል 23ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ግርማ በግሩም ሁኔታ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ተከላካዮችን በማለፍ ወደ ሳጥኑ በመግባት ነፃ አቋቋም ለቆመው ሳሙኤል ሳኑሚ ከማሻገር ይልቅ ራሱ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ጃኮ ፔንዜ ያዳነበት ኳስ ቡናዎችን መምራት የምታስችል አጋጣሚ ነበረች። በአዳማ በኩል ደግሞ 29ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ክልሉ እየወጣ ተደጋጋሚ ስህተት ይሰራ የነበረው የኢትዮዽያ ቡና ግብ ጠባቂ ሀሪሰን ከግብ ክልሉ መውጣቱን ያየው አንዳርጋቸው ይላቅ ከርቀት የመታውን ኳስ ሀሪሰን እንደምንም ያወጣበት አጋጣሚ ጥሩ የግብ እድሎች ነበሩ ።

ጨዋታው በአስገራሚ የደጋፊዎች ድጋፍ እንቅስቃሴ ቀጥሎ 40ኛው ደቂቃ ላይ ኢስማኤል ሳንጋሪ በጥሩ ሁኔታ ከርቀት ያሻገረለትን ኳስ ወጣቱ በረከት ደስታ በደረቱ አብርዶ ወደ ሳጥን በመግባት ግሩም ጎል አስቆጥሮ አዳማ ከተማን በድጋሚ መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ አምና ወደ ዋው ቡድን አድገ ዘንድሮ በበርካታ ጨዋታዎች ላይ የሰለፍ እድል ያገኘው በረከት ከጎሉ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ምክንያት ለህክምና ወደ ሆስፒታል አምርቷል።

የመጀመርያው አጋማሽ የመጠናቀቂያ ፊሽካ ሲጠበቅ ሳሙኤል ሳኑሚ ያገኘውን ነፃ ኳስ ቺፕ አርጎ ወደ ግብ ሞክሮ በጎሉ ጠርዝ ለጥቂት የወጣው አጋጣሚ የሚያስቆጭ ነበር።

 

ከእረፍት መልስ የተጨዋች ቅያሪ በማድረግ ወደ ሜዳ የገቡት ቡናዎች የተሻለ ሆነው የቀረቡበት ቢሆንም ከጥረት ባለፈ የመጨረሻው ሦስተኛው የሜዳው ክፍል ሲደርሱ የሚሰሩት ስህተት ፣ የስል አጥቂ አለመኖር እና የአዳማ ተከላካዮች ጥንካሬ ተጨምሮ ጠንካራ የጎል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። 89ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው በረከት ይስሀቅ ከመስኡድ መሀመድ የተጣለለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት የወጣበት ኳስ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።

አዳማዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ በማሰብ አመዛኙን ከእረፍት መልስ የነበረው አጨዋወታቸው ጥንቃቄ የተሞላበት ጠንካራ የመከላከል ስራ እና ሰአት የማባከን አጨዋወት የተከተሉት ሲሆን ጨዋታውንም እንዳሰቡት ጎል ሳይቆጠርባቸው 2-1 ማሸነፍ ችለዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተመዘገበው ውጤቱ የተከፉት የኢትዮዽያ ቡና ጥቂት የማይባሉ ደጋፊዎች ተጫዋቾቹን ሲቃወሙ ለመመልከት የቻልን ሲሆን በተለይ ከወንድይፍራው ጌታሁን ጋር ኃይለ ቃል የተሞላበት መጠነኛ ግጭት ሲፈጠር ተመልክተናል።

ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ ደረጃውን በማሻሻል ሁለተኛ ደረጃ ሲቀመጥ በአንፃሩ ኢትዮዽያ ቡና ከ8ኛ ደረጃው በአንድ ደረጃ ዝቅ በማለት 9ኛ ደረጃን ይዟል።

ከአዳማ ከተማ ጋር በተያያዘ ዜና የክለቡ ፕሬዝደንት አቶ አለማየሁ ቱሉ ለአዲሱ ፕሬዝዳንት አቶ ገመቹ መኮንን የክለቡን አርማ በመለዋወጥ ሽግግር ያደረጉ ሲሆን ከዚህ ባሻገር የኢ/እ/ኳስ ፌዴሬሽንን ለጥቂት ወራት የቴክኒክ ዳሬክተር በመሆን ያገለገሉት አቶ ዳንኤል ገ/ማርያምን የክለቡ የቴክኒክ ዳሬክተር ሆነው ተሸመዋል።

 

የአሰልጣኞች አስተያየት

ተገኔ ነጋሽ – አዳማ ከተማ

ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ ጠንካራ ፉክክር ታይቶበታል፡፡ ኢትዮዽያ ቡና ከጨዋታው ውጤት ፈልጎ እንደመጣ ያስታውቃል። እኛም ደግሞ አሸንፈን ለመውጣት እንፈልግ ነበር፡፡ ያም ተሳክቶልን በማሸነፈችን ደረጃችንን ሁለተኛ ማድረግ ችለናል ። ይህንን ጥንካሬችንን ጉዳት ላይ ያሉ ተጨዋቾች ሲመለሱ ደግሞ የተሻለ ነገር እንሰራለን ብዬ አስባለው ።

መሐመድ ኢብራሂም – ኢትዮዽያ ቡና (ረዳት አሰልጣኝ)

የአዳማ ደጋፊ ላደረገልን ነገር እያመሰገንኩ በተመዘገበው ውጤት ደስተኛ ላልሆኑት ደጋፊዎቻችን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ ጥሩ ፉክክር አሳይተናል፡፡ አስበን ወደ ሜዳ የገባነውን መጫወት አልቻልንም ፤  በተቆጠረብን ሁለት ጎሎች ተሸንፈናል። ቡድኑ ነጥብ መጣሉ ብዙ ነገሮች የሚያካትት ቢሆንም የተጨዋቾች ጉዳት ክፍተቶችን ፈጥሮብናል፡፡ እንግዲህ አዲስ አሰልጣኞች ነን ቡድኑን አስተካክለን ወደ ቀድሞ ቦታችን ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ቡድኑ ወደ የሚታወቅበት የጨዋታ ባህል ለመመለስም በጣም ጊዜ እንፈልጋለን፡፡ ደጋፊውም ሊታገሰን ይገባል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *