የዓለምአቀፉ የእግርኳስ አስተዳዳሪ አካል በአዲስ አበባ የምስራቅ አፍሪካ ቢሮ ለመክፈት እንቅስቃሴዎች ከጀመረ ወራቶች ተቆጥረዋል፡፡ የፊፋው ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ለካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያ በ2009 በተገኙበት ወቅት ለቢሮው መከፈት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማሟላት ቃል መግባታቸውን ተከትሎ ነው ይህ ቢሮው አዲስ አበባ ላይ የሚከፈተው፡፡
ፊፋ ነገ ጠዋት ተወካዩን ወደ አዲስ አበባ የሚልክ ሲሆን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ሃላፊዎች ጋር አርብ ውይይት በቢሮው ጉዳይ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ የፊፋ ተወካዩ በአዲስ አበባ በሚኖረው ቆይታ ለቢሮ የሚሆኑ ህንፃዎችን እንደሚመለከት እና ለቢሮ የሚሆኑ ቦታዎችን እንደሚመርጥ ታውቋል፡፡ ቅዳሜ ወደ ስዊዘርላንድ ሲመለስም ለፊፋ የበላይ ሃላፊዎች ሪፖርት በማቅረብ ቢሮው የሚከፈትበትን ግዜ እንደሚያጤን ይጠበቃል፡፡
ክፍለ አህጉራዊው ቢሮ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራትን እንዲያገለግል የሚከፈት ሲሆን ሃገራት የሚያስፈልጋቸው እርዳታ እና ከፊፋ ጋር ያላቸው ግንኙነት ለማጠንከር ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ታምኖበታል፡፡ ፊፋ እንዲህ ዓይነት ቢሮ በአፍሪካ ሲከፍት ይህ ለሶስተኛ ግዜ ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ቢሮዎች በደቡብ አፍሪካ እና ሴኔጋል ይገኛሉ፡፡