የአብስራ ተስፋዬ ይባላል። በዘንድሮ አመት የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ለደደቢት ውጤታማ ጉዞ ምክንያት ከሆኑ ድንቅ ወጣቶች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው። አምና ወደ ዋናው ቡድን አድጎ ብዙም የመሰለፍ እድል ያላገኘው የአብስራ ዘንድሮ የደደቢት ቋሚ አሰላለፍን ሰብሮ በመግባት የወደፊቱ ምርጥ አማካይ እንደሚሆን ፍንጭ የሰጠ አመት በማሳለፍ ላይ ይገኛል። በዚህ ሳምንት ተስፈኛ ተጫዋቾች ዝግጅታችንም ከወጣቱ አማካይ ጋር ያደረግነውን ቆይታ አቅርበንላችኋል።
ትውልድ ፣ እድገትህ እና የእግርኳስ አጀማመርህን ግለጽልን…
ተወልጄ ያደኩት አአ ከተማ መገናኛ እግዚአብሔር አብ ቤተ-ክርስቲያን አካካባቢ ነው። እግርኳስ መጨዋወት የጀመርኩት በሰፈሬ በሚገኘው 24 ሜዳ ነው። በቤተሰቦቼ በኩል ኳስ ተጫዋች እንድሆን አይፈልጉም ነበር ፤ በዚህም ጫና ያሳድሩብኝ ነበር። እኔ ግን አሰልጣኞች እና ጓደኞቼ ያበረታትኝ ስለነበር ከልጅነቴ ጀምሮም እግርኳስን መጫወት እወድ ስለነበር በ24 ሜዳ በአሰልጣኝ ቶማስ የሚሰጥ የፕሮጀክት ውስጥ መግባት ቻልኩኝ። ይህ ፕሮጀከት በአሁን ሰአት ከ17 አመት በታች የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚሳተፈው አፍሮ ፅዮን የሚባለው ክለብ ነው።
ከፕሮጀክቱ ወጥተህ ወደ ደደቢት ልትገባ የቻልከው እንዴት ነው ?
አሰልጣኝ ቶማስ ለሐረር ሲቲ ከ17 አመት በታች እንድጫወት ለሙከራ ይዞኝ ሄዶ ነበር። እዛ እየሞከርኩ ሳለ አሁን የመቐለ ከተማ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አየኝ። ቀጥታ 2006 ላይ ለኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሊመርጠኝ ቻለ። ከብሔራዊ ቡድን ስመለስ አሰልጣኝ ኤልያስ ኢብራሂም ወደ ደደቢት ወስዶኝ መጫወት ጀመርኩ። በደደቢት ከ17 አመት በታች ቡድን ውስጥም ለሁለት አመት ቆይታ አድርጌያለሁ ።
ከደደቢት የ17 አመት በታች ቡድን ጋር በነበረህ ቆይታ ጥሩ ጊዜ አሳልፈሀል። የነበረህን ቆይታ እንዴት ትገልፀዋለህ ?
በሁለት አመት የሀ-17 ቡድን ቆይታዬ በጣም ጥሩ ነበር። አሁን ላለው የእግርኳስ ህይወቴ ትልቁን ትምህርት ልምድ የወሰድኩበት ነበር ፤ በጣም ጥሩ ስብስብ ነበረን። የምድባችንን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ሁሉ አንስተናል። ካስታወስክ አዳማ ላይ 2008 በተካሄደው የማጠቃለያ ውድድር ከወላይታ ድቻ ጋር ስንጫወት በነበረኝ መልካም እንቅስቃሴ ” የአብስራ ድንቅ አቋሙን በማሳየት ከተመልካቹ ከፍተኛ አድናቆት ተሰጥቶታል። ” ተብሎ ከፎቶዬ ጋር ሶከር ኢትዮዽያ ላይ የተለቀቀው ዜና አለ። ይህን አረሳውም ፎቶውም እጄ ላይ ይገኛል ይህም በወቅቱ ትልቅ መነሳሳትም ፈጥሮብኛል።
ወደ ደደቢት ዋናው ቡድን ያደግክበትስ መንገድ እንዴት ነበር?
አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ወደ ኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ከመመረጡ በፊት ደደቢትን በዋና አሰልጣኝነት ሲይዝ በእሱ አማካኝነት በዋናው ቡድን አድጌ መስራት ቻልኩኝ። ነገር ግን ብዙም ሳልቆይ እሱ ወደ ብሔራዊ ቡድን ሲሄድ ተመልሼ ለተስፋው ቡድን መጫወት ጀምርኩ። በኋላ ላይ 2009 አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ደደቢትን መልሶ ማሰልጠን ሲጀምር ተመልሼ ወደ ዋናው ቡድን አደኩ። በተወሰነ መልኩ እየተሰለፍኩ ብጫወትም ብዙ አገልግሎት መስጠት አልቻልኩም። በቡድኑ ውስጥ ብዙ ሲኒየሮች ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች ስለነበሩ የመጀመርያ አመቴም እንደመሆኑ መጠን ብዙ ልምዶችን አግኝቻለው። ዘንድሮ ደግሞ የመሰለፍ እድል አግኝቼ እየተጫወትኩ እገኛለው።
ተቀይረህ በገባህባቸውም ሆነ በመጀመርያ አሰላለፍ በተካተትክባቸው ጨዋታዎች በተለይ በቡድኑ ስኬታማ የማጥቃት ሽግግር ላይ ያለህ አስዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ወቅታዊ አቋምህን እንዴት ትገልፀዋለህ?
በመጀመርያ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታን ማመስገን እፈልጋለው። ይህን እድል ስለሰጠኝ እኔም ገብቼ ጥሩ ነገር እያሳየው ነው ያለሁት።ሁሉም በእኔ ደስተኛ ነው ፤ በጣም ነው እያበረታቱ እያገዙኝ ያለሁት። እኔም በጣም የራስ መተማመኔ የመጫወት ፍላጎቴ ጨምሯል። ክለቤን ከዚህ በላይ ለመጥቀም ጠንክሬ እየሰራሁ እገኛለው።
በአንተ እድሜ በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ስመጫወት ምን ትላለህ? ያለው ጠቀሜታ ምንድነው? የሚከብድ ነገርስ አለው?
የሚከብድ ነገር የለውም። እውነት ለመናገር ትንሽ የልምድ ጉዳይ ካልሆነ በቀር አይከብድም። ልምዱ ደግሞ ከጨዋታ ብዛት እያሻሻልክ የምትመጣበት ነገር ነው። ብዙ ወጣት ተጫዋቾች ይህን እድል ቢገኙ መልካም ነው። ክለባቸውን በተሻለ መጥቀም ይችላሉ። ቢከብዳቸው አንድ ሁለት ጨዋታ እንጂ ሙሉ ለሙሉ ማገልገል አይከብዳቸውም። እኛ ጋር ልምድ ያላቸው ትልቅ ተጫዋቾች ስላሉ ከእነሱ ብዙ ነገር መማሬ ጠቅሞኛል። ከዚህ በኋላ ብዙ ነገሮችን እማራለሁ ብዬ አስባለው።
በተለያዩ አጋጣሚዎች ታዳጊ ተጨዋቾች የመሰለፍ እድል ያገኙና ጥሩ አቋማቸውን በሚያሳዩበት አጋጣሚ ተመልሰው የመሰለፍ እድል ሲያጡ ይስተዋላል። አንተ በዚህ ረገድ ስጋት አለብህ ?
እኔ እንኳ በአሁን ሰአት እንደዚህ አይነት ስጋት የለብኝም። አሰልጣኝ ንጉሴም በእኔ ደስተኛ ስለሆነ አልሰጋም። እንዲሁም በምችለው አቅም ሁሉ ያሳደገኝ ክለቤን የሚፈልገውን ነገር እያደረኩ እገኛለው። ሆኖም ብዙ መስራት እንዳለብኝ አምናለው አሰልጣኜ የሚሰጠኝ ስልጠና ሁሉ በመስራት ደደቢትን ከዚህ በላይ ማገልገል እፈልጋለው።
እግርኳስ ተጨዋች ለመሆን ስትነሳ ምሳሌ ያደረግከው ተጫዋች አለ?
ልጅ እያለው ምንያህል ተሾመን በጣም አደንቀው ነበር። በብሔራዊ ቡድን የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ያስደስቱኝ ነበር። የእሱ አድናቂ ነበርኩ ።
ቀጣይ እቅድህ ምንድነው?
ይህ የመጀመርያ አመቴ እንደመሆኑ መጠን እንደ ጅማሬ ለእኔ ጥሩ ጊዜ ቢሆንም ከዚህ በላይ አቅሜን አውጥቼ ጠንክሬ እሰራለሁ። ልምድ ያላቸው እነ አስራት መገርሳ ፣ ስዩም ተስፋዬ ፣ ጌታነህ ከበደ እና ሌሎች ልምድ አላቸው የሚባሉ ተጨዋቾች ሁሉ እኛ ክለብ ጋር አሉ። እነሱ የሚሰጡኝን ምክር በመቀበል እና ልምዳቸውን በመቅሰም የተሻለ ነገር ለመስራት እጥራለው።
እንዳንተ የመሰለፍ እድል ላገኙም ሆነ ነገ በትልቅ ደረጃ መጫወት ለሚያስቡ የዕድሜ አጋሮችህ የምታስተላልፈው መልክት ?
ያገኙትን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም አለባቸው። ያንን ቦታም እንዳያጡ ሁሌም ጠንክረው መስራት አለባቸው። ይህንን ነው መናገር የምፈልገው። በመጨረሻም እዚህ ለመድረስ ላገዙኝ ቤተሰቦቼ ጓደኞቼ ለአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ፣ ለደደቢት ክለብ አመራሮች ፣ ለአሰልጣኞቼ በሙሉ ልባዊ ምስጋና አቅርባለው።