የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒየንሺፕ (ቻን) ማራካሽ ላይ ሐሙስ ሲቀጥል የምድብ ሁለትም ልክ እንደምድብ አንድ ሁሉ ሩብ ፍፃሜ ያለፉ ሃገራትን በግዜ ያተወቁበት ሆኗል፡፡ ዛምቢያ እና ያልተጠበቀችው ናሚቢያ ወደ ቀጣዩ ዙር ሲያመሩ የ2016 ቻን ሶስተኛ ደረጃን ያገኘችው ኮትዲቯር እና ዩጋንዳ ከምድብ ተሰናብተዋል፡፡
ማራካሽ ላይ ዛምቢያ ኮትዲቯርን ገጥም በኦገስቲን ሙሌንጋ ሁለት ግቦች 2-0 ማሸነፍ ችላለች፡፡ ሙሌንጋ ጨዋታው በተጀመረ በ8ተኛው ደቂቃ ከሳጥኑ ውጪ መቶ ባስቆጠረው ግብ ቺፖሎፖሎዎቹ መሪ መሆን ችለዋል፡፡ በተደጋጋሚም የኮትዲቯር የመስመር ተከላካዮች ደካማነት በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ አርነስት ሙቤዌም የግብ አግዳሚ የመለሰበትን ሙከራ ማድረግ የቻለው በመጀመሪው 45 ነበር፡፡ ሙሌንጋ በ72ኛው ደቂቃ ልዩነቱን ወደ ሁለት ያሰፋበትን ግብ የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ አስቆጥሯል፡፡ ሙሌንጋ ሶስት የኮትዲቯር ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ነው ኳስ እና መረብን ያገናኘው፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ዝሆኖቹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥራቸውን ወደ ግብነት ለመቀየር አልቻሉም፡፡
ዩጋንዳ አሁንም ቻን ላይ በደካማ ጉዟዋ ቀጥላለች፡፡ ክሬንሶቹ ከ2011 ጀምሮ ለተከታታይ አራት የቻን ውድድሮች ቢያልፉም አንድም ግዜ ከምድብ መውጣት አቅቷቸው በግዜ መሰናበት ባህላቸው አድርገውታል፡፡ ዩጋንዳ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባት ግብ ለናሚቢያ እጇን ሰጥታለች፡፡ ያልተጠበቀችው ናሚቢያም ሁለት ግዜ በመገባደጃ ደቂቃዎች ባስቆጠረቻቸው ሁለት ግቦች ኮትዲቯርን እና ዩጋንዳን አሸንፋለች፡፡ ዩጋንዳ የተሻለ በነበረችነት ጨዋታ ዴሪክ ንስምባምቢ በሁለተኛው 45 የሞከራቸው ሁለት ኳሶች ዩጋንዳ መሪ ማድረግ የመቻል አቅም የነበራቸው ቢሆንም የግቡ አግዳሚ እና የናሚቢያው ግብ ጠባቂ ሎይድ ካዛፑዋ መልሰውበታል፡፡ ናሚቢያዎች በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ኢታሙኑአ ኬይሙን የዩጋንዳ ተከላካዮች በአግባቡ ከአደጋ ክልሉ ማራቅ ያልቻሉትን ኳስ ተጠቅሞ ግብ አስቆጥሯል፡፡ የዩጋንዳው ተከላካይ ቲሞቲ አዎኒ በሁለት ቢጫ ከሜዳ በጨዋታው ላይ ተወግዷል፡፡ አዲሱ የዩጋንዳ አሰልጣኝ ሰባስቲያን ዴሳቤሬ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈትን አስተናግደዋል፡፡
ዛምቢያ እና ናሚቢያ በእኩል 6 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ምድቡን የሚመሩት ሲሆን የምድቡ የበላይ ለመሆን በመጪው ሰኞ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል፡፡ ሞሮኮ እና ሱዳን ከምድብ አንድ ያለፉ ሌሎቹ ሃገራት ሲሆኑ ጊኒ፣ ሞሪታንያ፣ ዩጋንዳ እና ኮትዲቯር ከምድብ ተሰናብተዋል፡፡
ዛሬ የምድብ ሶስት መሪዋ ሊቢያ በተጠባቂ ጨዋታ ናይጄሪያን ስትገጥም ምሽት ላይ ሩዋንዳ ከኤኳቶሪያል ጊኒ ይፋለማሉ፡፡ ጨዋታዎቹ በታንገ በሚገኘው ግራንድ ስታደ ደ ታንገ ይደረጋል፡፡
የሐሙስ ጨዋታዎች
ዛምቢያ 2-0 ኮትዲቯር
ዩጋንዳ 0-1 ናሚቢያ
የዛሬ ጨዋታዎች
1፡30 – ሊቢያ ከ ናይጄሪያ
2፡30 – ሩዋንዳ ከ ኤኳቶሪያል ጊኒ