እግርኳስን ላለፉት 14 ዓመታት የተጫወተው ዋሊድ አታ ጫማውን መሰቀሉን በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል፡፡ የመሃል ተከላካዩ በህዳር ወር የሳውዲ አረቢያ ክለብ የሆነው አል ካሊጅ ጋር የነበረውን ውል በስምምነት ካፈረሰ በኃላ ወደ ስዊድን ተመልሶ ሌሎችን ክለቦችን እንደሚቀላቀል ቢጠበቅም እግርኳስን ማቆም የመጀመሪያ ምርጫው አድርጓል፡፡
የ31 ዓመቱ ተጫዋች እግርኳስን ማቆም የወሰነበትን ምክንያት ከጉዳት ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ አስረድቷል፡፡ “እግርኳስን ማቆም ያሰብኩት ቀድም ብዬ ነው፡፡ ከአል ካሊጅ ከለቀቅኩ በኃላ ወደ ሌሎች ክለቦች የማምራት እድሎችን ቢኖሩም ማቆም እንዳለብኝ እራሴን አሳምኜ ነው ያደረግኩት፡፡ የተጫዋቾች ወኪል ድርጅት ከፍቶ የሚሰራ የቅርብ ወዳጅ አለኝ፡፡ አብሬው እንድሰራ በጣም ይፈልግ ነበር ስለዚህም ነገሮችን በጥሞና ካየሁ በኃላ ነው ወደ ውሳኔው ልደርስ የቻልኩት እንጂ ከጉዳት ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡” ሲል ሃሳቡን ይሰጣል፡፡
ዋሊድ ከዚህ በኃላም ከእግርኳስ ሳይርቅ በተጫዋቾች ወኪልነት እንደሚሰራ ተናግሯል፡፡ “አዎ ከእግርኳስ መራቅ ፈፅሞ አልችልም፡፡ ለዚህም የተጫዋቾች ወኪል ሆኞ ለመስራት ወዳጄ በከፈተው የውክልና ድርጅት ውስጥ ለመስራት ተስማምቻለው፡፡ መቀመጫዬን ካታር በማድረግም በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ነው ለአሁን ስራዬን የምጀምረው፡፡ ግንኙነቶችን በመፍጠር እና በተለያዩ ቦታዎች በመዞር በዚሁ ስራ ስኬታማ መሆን እፈልጋለው፡፡ በድርጅቱ ውስጥ የምንወክላቸው በጣም ጥሩ ተጫዋቾች አሉን፡፡ አንዳንዶቹም በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ውስጥ የሚገኙት፡፡ በዚህ ስራዬም ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾችን መርዳት እቅዴ ነው፡፡ በእግርኳስ ትምህርት እና ወደ አውሮፓ ሄደው የሚጫወቱበትን መንገድ ለመክፈት ሁሌም የማልመው ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ተመልሼ መጥቼ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾችን መርዳት እፈልጋለው፡፡” ከዚህ ቀደም ዴቪድ በሻ እግርኳስን ካቆመ በኃላ የተጫዋች ወኪል ሆኖ መስራት መጀመሩ የሚታወቅ ነው፡፡
በ12 ክለቦች የተጫወተው ዋሊድ በሳለፈው የእግርኳርስ ህይወቱ ሁሌም ደስተኛ እንደሆነ ይናገራል፡፡ “በእግርኳስ ህይወቴ በጣም ደስተኛ ነበርኩ፡፡ በማቆሜ አዝናለው ግን ባሳለፍኩት ነገር እጅግ ሲበዛ ደስተኛ ነኝ፡፡ መጫወትን መቼም ቢሆን እናፍቃለው ግን የተሳኩ ግዜያት በእግርኳሱ አሳልፍያለው፡፡ ከኤአልኤ ጋር የሊግ እና የሱፐር ካፕ አሸናፊ፣ ከሄልሰንበርግ ጋር የሱፐር ካፕ ዋንጫን አሸንፊያለው፡፡ በተለያዩ ሃገራት ከመጫወቴ በተረፈ የኢትዮጵያን መለያ ለብሼ ለብሄራዊ ቡድን መጫወት መቻሌ ለእኔ የስኬቶቼ መገለጫዎች አድርጎ ነው የማስባቸው፡፡”
በሪያድ ከኢትዮጵያዊ እናት እና ኤርትራዊ አባት የተወለደው ዋሊድ ከኤአይኬ እና ሄልሰንበርግ ጋር በስዊድን ዋንጫዎችን ያሸነፈ ሲሆን ከሁለቱም ክለቦች ጋር በቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል፡፡ እንዲሁም ከሄልሰንበርግ ጋር የዩሮፓ ሊግ የምድብ ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ ለስዊድን ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንም ተሰልፎ የተጫወተው ተከላካዩ ከአምስት አመታት በፊት ኢትዮጵያን ለመወከል ፍላጎት ማሳየቱን ተክተሎ አራት ግዜ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ችሏል፡፡