​ሪፖርት | ጅማ አባጅፋር ወደ ድል በመመለስ ደረጃውን አሻሽሏል

በ12ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ ስታድየም ላይ ጅማ አባ ጅፋር ወልዲያን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ 3ኛ ማሻሻል ችሏል።

ጅማ አባ ጅፋሮች ባለፈው ሳምንት በሜዳቸው ከመከላከያ አቻ ከተለያየው ቡድናቸው መካከል ከጉዳት የተመለሰው ኦኪኪ አፎላቢን በሳምሶን ቆልቻ ምትክ በመጀመርያ አሰላለፍ በማካተት በተለመደው አሰላለፋቸው 4-4-2 ወደ ሜዳ ገብተዋል። በወልዲያ በኩል ከመቐለ ከተማ ጋር ካደረጉት ተስተካካይ ጨዋታ የ4 ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ መለሉቀን አከለ ፣ ብሩክ ቃልቦሬ ፣ ነጋ በላይ እና ኤደም ኮድዞን በመጀመርያ አሰላለፍ ሲያካትት ቢያድግልኝ ኤልያስ እና ፍፁም ገ/ማርያም ወደ ጅማ ከተጓዙት የቡድኑ አባላት ጋር ሳይካተቱ ቀርተዋል። በተጨማሪም ወልዲያ በተጠባባቂ ወንበር ላይ አንድ ግብ ጠባቂ እና 2 ተጫዋቾችን ብቻ በመያዝ በጨዋታው ምንም ቅያሪ ማድረግ ሳይችል ቀርቷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ  ባለሜዳዎቹ አባጅፋሮች በግራና በቀኝ መስመር በኄኖክ አዱኛ እና በዮናስ ገረመው አማካይነት በተደጋጋሚ የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር መረበሽ የቻሉ ሲሆን በተለይ ከኄኖክ ይጣሉ የነበሩ ኳሶች በወልዲያ ተከላካዮች ጥረት ውጤታማ መሆን ባይችሉም የግብ አጋጣሚዎችን የፈጠሩ ነበሩ። በአንፃሩ ወልድያዎች ጥብቅ መከላከልን መሠረት ባደረገ ኃይል የተቀላቀለበት አጨዋወት እና አልፎ አልፎ በያሬድ ብርሃኑ በኩል በሚሰነዘር የመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሞክረዋል። የጨዋታው እቅስቃሴም የተጨዋቾች ግጭት የተበራከተበት እና በመሀል ዳኛው ፊሽካ በተደጋጋሚ የሚቆራረጥ ነበር።

በመጀመርያው አጋማሽ ወደ ጎል በመቅረብ አባ ጅፋሮች የተሻሉ ሲሆኑ በ27ኛው ደቂቃ ከኄኖክ አዱኛ የተሻማውን ኳስ ኦኪኪ በግንባሩ የሞከረው እንዲሁም ዮናስ ገረመው ለኦኪኪ አመቻችቶ ያቀበለውን ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የግቡን አግዳሚ መቶ የወጣው ኳስ በአባጅፋሮች በኩል የሚያስቆጭ አጋሚዎች ነበሩ።

ከእረፍት መልስ የነበረው የጨዋታው መልክ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ቀዝቀዝ ያለ ሲሆን በተደጋጋሚ ጥፋቶች እና የዳኛ ፊሽካ ጎልቶ መታየቱ ግን አልቀረም።  የአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ቡድን በ49ኛው ደቂቃ ላይ ባደረገው የተጫዋች ቅያሪ እንዳለ ደባልቄ ወጥቶ ኄኖክ ኢሳይያስ የገባ ሲሆን ይህም በጨዋታው ላይ ልዩነት መፍጠር ችሏል። በመሆኑም ከቅያሪው በኋላ አባ ጅፋሮች ከግራ መስመር የሚነሳው የማጥቃት እቅስቃሴያቸው ላይ የተሻለ ጫና መፍጠር ሲችሉ ታይቷል። በዚህ ሁኔታ 64ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ከአስራስድስት ከሀምሳ ውስጥ ሄኖክ ወደ ግብ አክርሮ የመተውን ኳስ ብርሀኔ አንለይ በእጁ በመንካቱ የተሠጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ኦኪኪ አፎላቢ አስቆጥሮ ቡድኑ ካለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ መጣል በኃላ ወደ ድል የተመለሰበትን ውጤት እንዲያስመዘግብ አድርጓል።

ድሉን ተከትሎ ጅማ አባ ጅፋር የነጥብ ድምሩን 18 በማድረስ ደረጃውን ወደ ሶስተኝነት ከፍ ሲያደርግ በተከታታይ ጨዋታዎት ነጥብ የጣለው ወልዲያ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ11 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።


የአሰልጣኞች አስተያየት 


ገ/መድህን ኃይሌ – ጅማ አባጅፋር

አጥቅተን ለመጫወት ሞክረናል። ሆኖም ተጋጣሚያችን በተደራጀ ሁኔታ በመከላከሉ ተጨማሪ ግብ ማግባት አልቻልንም። በዳኝነት ላይ ያን ያህል የተጋነነ ነገር የለም።
ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ – ወልዲያ
በታክቲኩ ረገድ ከተጋጣሚያችን የተሻልን ነበርን። ነገር ግን አግባብ ያልሆነ የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቶብን ልንሸነፍ ችለናል። በዳኝነት ቅሬታ አለኝ የተደረበ ኳስን ነው የፍፁም ቅጣት ምት ብሎ የሰጠብን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *