በ13 ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሜዳው ሲዳማ ቡናን የገጠመው መቐለ ከተማ 1-0 በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል።
መቐለ ከተማ በተስተካካይ ጨዋታ ወልዲያን 1-0 ካሸነፈው ስብስብ ኃይሉ ገብረየሱስ እና ሐብታሙ ተከስተ ምትክ ዮናስ ግርማይ እና ጋይሳ አፖንግን ወደ መጀመርያ አሰላለፍ በማካተት ጨዋታውን ሲጀምር ሲዳማ ቡና ይርጋለም ላይ ፋሲልን 3-0 ከረታወ ስብስብ ክፍሌ ኪአን በዮናታን ፍስሀ ምትክ በመጠቀም ወደ ሜዳ ገብቷል።
በፈጣን እንቅስቃሴ እና ሙከራዎች ታጅቦ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች እንግዶቹ ተሸለው የታዩ ሲሆን በተለይም በ2ኛው ደቂቃ ከትርታዬ የተሻገረለትን ኳስ አዲስ ግደይ ሞክሮ በኢቮኖ ልዩ ብቃት የዳነችበት የመጀመርያው አስደንጋጭ ሙከራ ነበር። በሙከራው የተነቃቁት እና አጥቅተው ለመጫወት ድፍረት የነበራቸው ሲዳማዎች በ8ኛው ደቂቃ ላይ በወንደሜነህ አማካኝነት ከርቀት ኢላማዉ የጠበቀ ሙከራ አድርገውም ነበር። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ሪትም የገቡት ባለሜዳዎቹ መቐለዎች በ12ኛው ደቂቃ አማኑኤል እና ቢስማርክ በአንድ ሁለት ቅብብል ገብተዉ አማኑኤል ከርቀት ሞክሮ ግሩም አሰፋ ተደርቦ ወደ ውጭ ያወጣበት የመጀመርያው ሙከራ ነበር።
ከ15ኛው ደቂቃ በኋላ ሲዳማ ቡናዎች ተዳክመው የታዩ ሲሆን መቐለዎች ፍፁም የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። በቀኝ መስመር ባጋደለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የሲዳማን ተከላካይ ማስጨነቅ የቻሉት መቐለዎች በ28ኛው ደቂቃ በአማኑኤል እንዲሁም በ33ኛው ደቂቃ በአንተነህ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ሙከራዎች አደርገው ነበር። በተለይ ደግሞ በ33ኛው ደቂቃ አንተነህ ከቀኝ መስመር በረጅሙ የመታዉ ኳስ የግቡን ብረት ለትሞ የመወጣው ኳስ በመቐለ በኩለ የምታስቆጭ ሙከራ ነበረች።
በመጀመርያው አጋማሽ ከአማካዮች ዮናስ ግርማይ እና አመለ በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት ሲሞክሩ የነበሩት መቐለዎች በተደጋጋሚ በሲዳማ ተከላካዮች በቀላሉ ሲመልሱባቸው የተስተዋለ ሲሆን በ35ኛው ደቂቃ ግን ዮናስ ያሻገረው ኳስ ሚካኤል በግምባር በመግጨት አመቻችቶለት ያሬድ ከበደ በማይታመን ሁኔታ ጎል እና መረብ ሳያገኘ ቀርቷል። የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ያሬድ ከበደ ከሳጥኑ ጠርዝ ያሻማውን ኳስ አማኑኤል በግንባሩ ቢገጭም ኳሷ ኢላማዋን ሳትጠብቅ ወደ ውጭ ወጥታለች።
በ53ኛው ደቂቃ ሚካኤል ያሻማውን የማዕዘን ምት አፖንግ ሞክሮ አበበ ተደርቦ ባወጣው ኳስ ሁለተኛው አጋማሽን በሙከራ ቀዳሚ የሆኑት መቐለዎች በዚህ አጋማሽ በተመሳሳይ አቀራረብ ወደ ሜዳ ሲገቡ ሲዳማዎች የተከላካይ መስመራቸውን ወደ መሀል በማስጠጋት የአማካይ ተጫዋቾቻቸውን ቁጥር ወደ 5 ከፍ ማድረግ ቢችሉም መቐለዎች ኳስ እንዳይመሰርቱ ጫና ባለመፍጠራቸው እና ሰፊ የመጫወቻ ቦታ በመስጠታቸው የመቐለ ተጫዋቾች ከሲዳማ ተከላካዮች ጀርባ የሚገኘውን ክፍተት በመጠቀም የጎል እድሎች ሲፈጥሩ ተስተውለዋል። በተለይም በ58ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ያመከናት ኳስ ለዚ ማሳያ ነበረች።
ሲዳማ ቡናዎች በ60ኛው ደቂቃ በወንድሜነህ አማካኝነት ሙከራ አድርጎ ኢቮኖ ሲያመክነው በ67 ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረው የነበረ ቢሆንም ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ተሽሯል። በዚህም የተነሳ የሲዳማ ቡድን አባላት ከ4ኛ ዳኛው ጋር አላስፈላጊ እሰጣ ገባ ውስጥ ሲገቡ ታይተዋል።
ጥፋቶች በበዙበት የመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች መቐለ ከተማዎች ጫና ፈጥረዉ የተጫወቱ ቢሆንም የረባ የጎል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ሆኖም በ86ኛው ደቂቃ በጨዋታው ተቀይሮ በመግባት ጥሩ የተንቀሳቀሰው ሚካኤል አካፉ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ጋይሳ አፖንግ መሬት ለመሬት በመምታት ወደ ግብነት ለውጦ መቐለ ከተማን 3 ነጥብ አስጨብጧል።
ከጎሉ በኋላ እስከ ጨዋታው ፍፃሜው ድረስ በሽኩቻዎች እና አለመግባባቶች የተሞላ ሲሆን በሁለቱ ቡድኖች ለአሰልጣኞች መካከልም ዱላ ቀረሽ የሆነ ውዝግብ ተስተውሏል።