የከፍተኛ ሊጉ 11ኛ ሳምንት የምድብ ለ ጨዋታዎች እሁድ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ሲካሄዱ በሰንጠረዡ አናት። የሚገኙ ክለቦች ነጥብ ጥለዋል።
ናሽናል ሴሜንት 1-1 ዲላ ከተማ
(በዳንኤል መስፍን)
10:00 ላይ በተካሄደውና የምድብ ለ መሪ ዲላ ከተማን ናሽናል ሴሜንት ያገናኘው ጨዋታ ጠንካራ እንቅስቃሴ ተደርጎበታል። ለጎል የቀረበ ሙከራ በማድረግ ዲላዎች ቀዳሚ ሲሆኑ ሙና በቀለ ከቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት አክሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ያዳነበት አጋጣሚ መልካም አጋጣሚ ነበር። ጨዋታው በጥሩ ፉክክር እየቀጠለ ባለበት ወቅት በሁለቱም ቡድኖች መካከል በተፈጠረ ግጭት ጨዋታው ለተወሰነ ደቂቃ ሲቋረጥ ጨዋታውን የመራችው ኢ/ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ወንደሰን ቃይሌን ከዲላ ፣ መሀሙድ መሀመድን ከናሽናል ሴሜንት በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወግዳቸዋለች። ጨዋታው ቀጥሎ ምንም ጎል ሳይቆጠርበትም ወደ መልበሻ ክፍል ለእረፍት አምርተዋል ።
እልህ የተቀላቀለበት ጠንካራ ፉክክር በሁለተኛው አጋማሽ ቀጥሎ 61ኛው ደቂቃ ላይ ኤሊያስ እንድርያስ በጥሩ ሁኔታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ማስረሻ ደረጄ ወደ ጎልነት ቀይሮ ዲላ ከተማዎችን መምራት አስችሎ የነበረ ቢሆንም በ71ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው መሀመድ አብዱላሂ በግንባሩ ገጭቶ ያስቆጠራት ጎል ናሽናልን ወደ አቻነት አሸጋግሮታል።
በቀሪው ደቂቃ እጅግ አስገራሚ ፉክክር እንድናይ አስችሎናል። በተለይ ናሽናል ሴሚንቶች ተመልካቹን ቁጭ ብድግ የሚያደርግ የጎል ሙከራዎች ቢያደርጉም በዲላዎች ግብ ጠባቂ ተካልኝ ኃይሌ ጥረት ከሽፈው ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ጅማ አባ ቡና 1-1 መቂ ከተማ
(በቴዎድሮስ ታደሰ)
በጅማ ስቴድየም በተደረገው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ የጎል ሙከራ ማድረግ የጀመሩት ገና በመጀመሪያው ደቂቃ ሲሆን በተለይ ኳስን ተቆጣረው በመጫወት የተቃራኒ ተከላካዮችን በመረበሽ ተደጋጋሚ ኢላማቸውን ያልጠበቁ የጎል ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በመቂ ከተማ በኩል መከላከልን መሰረት ባደረገ የመልሶ ማጥቃት ስኬታማ ያልነበረ ሲሆን በመጀመርያው አጋማሽ የተከላካይ ክፍሉ ጫና በዝቶበት ታይቷል።
በ9ኛው ደቂቃ በድሉ መርድ ያሻማውን ቅጣት ምት አብዱረዛቅ ናስር በግንባሩ በመግጨት ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከጎሉ መቆጠር በኃላ በ26ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የገቡት አባቡናዎች አብዱረዛቅ ናስር ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያመከነው እና በ 34ኛው እና 42ኛው ደቂቃዎች ቴዎድሮስ ታደሰ በብዙ ንክኪ የተገኙትን አጋሚዎች አመጠቀሙ በሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ።
ከእረፍት መልስ ባልተለመደ መልኩ ሁለቱም ቡድኖች ተቀዛቅዘው የታዩ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ከተገኙት አጋሚዎች መካከል በ75ኛው ደቂቃ ብዙአየሁ እንደሻው በመቂ ከተማ ግብ ጠባቂ ስህተት የተገኘውን ክፍት ጎል መጠቀም አለመቻሉ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።
በ80ኛው ደቂቃ የአባቡናው ግብ ጠባቂ ስህተትን በመጠቀም ድንቁ በዳኔ አስቆጥሮ በጨዋታው እምብዛም ወደ ጅማ አባ ቡና የግብ ክልል ሲደርሱ ያልታዩት መቂ ከተማዎችን አቻ አድርጓል። መቂዎች ግብ ካስቆጠሩ በኃላ የአባቡና ደጋፊዎች በክለቡ አመራሮች ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን ተቃውሞው ተባብሶ በሜዳ ተገኝተው የነበሩ የክለቡ አመራሮች ላይ ቁሳቁስ በመወርወር ሜዳውን ለቀው ወጥተዋል። ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላም የክለቡን ተጫዋቾች ከሜዳ አናስወጣም በማለታቸው በዕለቱ የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ታጅበው ከሜዳ ሊወጡ ችለዋል። ይህ በተደጋጋሚ የሚፈጠሩት ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጭ የሆኑ ድርጊቶች የክለቡ አመራሮች ቆም ብለው ሊያስቡበት እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
ድሬዳዋ ፖሊስ 1-1 ሻሸመኔ ከተማ
(በዳንኤል መስፍን)
08:00 ላይ የተጀመረው ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ ማራኪ እንቅሰስቃሴ የተመለከትንበት ሲሆን በአሰልጣኝ ያሬድ አበጀ የሚመሩት ሻሸመኔ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በፍጥነት ወደ ጎል በመድረስ በሚደረግ ሽግግር የተሻሉ ቢሆንም ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ባለሜዳዎቹ ፖሊሶች ነበሩ። በ22ኛው ደቂቃ ዘርአይ ገ/ሦላሴ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ አድርጓል።
ሻሸመኔዎች ጎሉ ከተስተናገደባቸው በኋላም በነበራቸው የመጫወት ፍላጎት እና ጥሩ እንቅስቃሴ ተጠቅመው በ37ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ ይድነቃቸው ብርሃኑ በግሩም ሁኔታ ባስቆጠራት ጎል አቻ መሆን ችለዋል። በ44ኛው ደቂቃ ላይ እራሱ ይድነቃቸው ብርሃኑ ነፃ የማግባት አጋጣሚን ከቡድን አጋሮቹ ጋር አብሮ ተጫውቶ ጎል ሊሆን የሚችለውን ኳስ በግሉ ለመጠቀም በማሰብ ያመከናት ኳስ ሻሸመኔዎችን ቀዳሚ ማድረግ የምትችል መልካም አጋጣሚ ነበር።
ከእረፍት መልስ ሻሸመኔዎች የአቻ ውጤቱን ለመጠበቅ በሚመስል መልኩ ወደፊት አጥቅቶ ከመጫወት ይልቅ ማፈግፈጋቸው ለድሬዳዋ ፖሊሶች የማጥቃት እድል ቢሰጣቸውም የአማካይ ክፍሉ ደካማ መሆኑ ለአጥቂዎች በተገቢው መልኩ የጎል እድል ሳይፈጠርላቸው ቀርቷል። በመስመር አጥቂዎቻቸው የሚፈጥሩት የማጥቃት እንቅስቃሴ ከአንድ የጎል የማግባት እድል ከመፍጠር የዘለለ ጉዞ አልነበረውም ። 81ኛው ደቂቃ ላይ እዩኤል ተስፋዬ ከመስመር የተሻገረለትን በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት የወጣው ኳስ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። ሻሸመኔዎች በመልሶ ማጥቃት አልፎ አልፎ ወደ ድሬደዋ ፖሊስ የግብ ክልል ቢደርሱም ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የተሳካ የጎል ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ጨዋታውም በስፍራው የተገኘው የድሬዳዋ ስፖርት አፍቃሪን ያዝናና ነበር።
ሌሎች መርሀ ግብሮች
(በአምሀ ተስፋዬ)
ወደ ቤንጅ ማጂ ያመራው ደቡብ ፖሊስ የ1-0 ሽንፈት አስተናግዶ ከመሪው ዲላ ጋር የነበረውን የነጥብ ልዩነት የማጥበብ እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በ17ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት መሰለ ወልደሰማያት ወደ ግብነት ለውጦ ቤንችማጂ ቡናን ድል አስጨብጧል፡፡
ካፋ ቡና ነገሌ ከተማን አስተናግዶ ወደ 3-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ካለፈው ሳምንት ሽንፈቱ አገግሟል። ኦኔ ኦጅሎ ሁለት ግቦች ሲያስቆጥር ትዕዛዙ ወንድሙ ቀሪዋን ጎል አስቆጥሯል።
ወደ ወራቤ ያመራው ሀምበሪቾ በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ስልጤ ወራቤን 1-0 አሸንፏል። ከዕረፍት መልስ በ65ኛው ደቂቃ ላይ የስልጤ ወራቤ ተጨዋች በፈጠረው ስህተት በራሱ ላይ ባስቆጠረው ግብ ነው ሀምበሪቾ 3 ነጥብ መሰብሰብ የቻለው። ከጨዋታው በኃላ የእለቱ 2ኛ ዳኛ በነበሩት ፌደራል ዳኛ ቢቄላ ሁንዴሳ ላይ ጉዳት ደርሶ ለህክምና ወደ ሆስፒታል መሄዳቸው ሶከር ኢትዮጵያ ከስፍራው ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።
ሀላባ ላይ ሊደረግ የነበረው የሀላበ ከተማ እና ቡታጅራ ከተማ ጨዋታ በሀላባ ሴራ በአል ምክንያት ወደ ማክሰኞ ሲሸጋገር በወልቂጤ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና መካከል ሊደረግ የነበረው ጨዋታ በፀጥታ ችግር ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።