በኢትዮዽያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ 11ኛ ሳምንት ሽረ ላይ መካሄድ የነበረበት የሽረ እንዳስላሴ እና ባህርዳር ከተማ ጨዋታ በፌዴሬሽኑ ሊግ ኮሚቴ ውሳኔ መሰረት ጥር 20 (እሁድ) ለገጣፎ ላይ በ08:00 ላይ ሊደረግ መርሀ ግብር ቢወጣለትም በከተማው በተደረገው የግማሽ ማራቶን ውድድር ምክንያት የፀጥታ አካላት በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ በሚል ምክንያት መካሄድ ሳይችል መቅረቱ ይታወሳል።
ፌዴሬሽኑ ይህን ጨዋታ እንዲካሄድ ሌላ የመርሀ ግብር ለውጥ አድርጎ አዲስ አበባ ላይ ጥር 22 (ዛሬ) በ07:00 በኦሜድላ ሜዳ እንዲደረግ በወሰነው መሰረት የሁለቱም ቡድን ተጫዋቾች ፣ አመራሮች ፣ ደጋፊዎች ፣ የህክምና ቡድን እና የጨዋታውን አመራሮች እንዲሁም በቂ የፀጥታ ኃይል በሜዳው ተገኝቶ ነበር። ጨዋታው እንደሚካሄድ በማሰብም የሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች ወደ ሜዳ ገብተው ልምምዳቸውን ጨርሰው ዳኞችም ለመጫወት ብቁ መሆናቸውን ቲሴራቸውን ተመልክተው እያረጋገጡ ባለበት ቅፅበት የፀጥታ አካላት ከበላይ አካል በተሰጠ ትዕዛዝ መሰረት ጨዋታው እንዳይደረግ የሚል ውሳኔ አሳልፈው ጨዋታው ሳይጀመር እንዲቋረጥ ተደርጓል።
የባህርዳር ከተማ ክለብ አመራሮች በውሳኔው እጅግ አዝነው ሜዳውን ለቀው የወጡ ሲሆን ቅሬታቸውንም ለጨዋታው ኮሚሽነር አቅርበዋል። ረጅም ርቀት አቋርጠው ክለባቸውን ለመደገፍ የመጡ ጥቂት የማይባሉ የባህርዳር ከተማ ደጋፊዎች ከአንዴም ሁለቴ ጨዋታው በመቋረጡ ከፍተኛ እንግልት እንደደረሰባቸው ተናግረው ፌዴሬሽኑ ውድደሮችን የመምራት አቅሙ ላይ ችግሮች እንዳለበት ገልፀዋል።
በሽረ እንዳስላሴ በኩል ደግሞ አስቀድመው ጨዋታው ከጥር 22 በኋላ በአአ ስታዲየም መካሄድ እንዳለበት በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ፌዴሬሽኑ በእንቢተኝነት ውሳኔ በመወሰኑ ጨዋታው ለመቋረጥ በቅቷል ብለዋል።
ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ጨዋታው መቼ እንደሚደረግ አላሳወቀም፡፡