ኡመድ ስለዘንድሮ አቋሙ እና ስለስሞሃ ይናገራል

በኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ የነበረውን የተሳካ ግዜ አጠናቅቆ ወደ አሌክሳንደሪያው ክለብ ስሞሃ ያመራው ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ኡመድ ኡኩሪ በ2017/18 ግብፅ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ተቀዛቅዞ ታይቷል፡፡ እስከ 21ኛው ሳምንት ድረስም ያስቆጠረውን መጠን ሶስት ሲሆን በክለቡ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ግን በመደበኝነት እየገባ ይገኛል፡፡ አጥቂው ኡመድ ስለስሞሃ የስድስት ወር ቆይታው፣ የግብፅ ፕሪምየር ሊግ፣ ስለተቀዛቀዘው አቋሙ እና መሰል ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡


የግብፅ ፕሪምየር ሊግ አጋማሽን አልፎ 22ኛ ሳምንት ላይ ይገኛል፡፡ ክለብህ ስሞሃም በአራተኛ ደረጃነት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ያለፉትን ስድስት ወራት የቡድኑን የሊግ ጉዞ እንዴት አየኸው?

ጥሩ ነው ማለት እችላለው፡፡ አጀማመራችን ላይ ከሜዳ ውጪ ነጥቦችን እንሰበስባለን በሜዳችን በተቃራኒው እንጥልን ነበር፡፡ ቡድኑ ላይ የአጨዋወት አለመረጋጋት ነበር እንዲሁም 3 የምንሆን ተጫዋቾች ለክለቡ አዲስ እንደመሆናችን ከቡድኑ ጋር በፍጥነት ለመወሃድ እና ለመቀናጀት ግዜ ፈጅቶብናል፡፡ ከሜዳችን ውጪ እና በሜዳችን ላይ ያለን የአጨዋወት ስልት መለያየትም እንደምንፈልገው ነጥብ እንዳንሰበስብ አድርጎን ነበር፡፡ ውድድር የጀመረነው በፍራንቼስክ ስትራካ ስር ነበር፡፡ ከአውሮፓ እንደምጣቱ በአብዛኛው በጥቂት ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረንስ የሚችል ቡድን ለመገንባት ነበር ፍላጎቱ፡፡ ይህ ደግሞ ቡድኑ ከለመደው አጨዋወት የወጣ መሆኑ ነገሮችን አስቸጋሪ አድርጎበታል፡፡ አዲሱ አሰልጣኝ ታላት የሱፍ ከመጣ በኃላ ግን ሁኔታዎች መሻሻል ጀምረዋል፡፡ የቡድኑ ተጫዋቾችን በሚገባ ያውቃል የሚሰጠን ልምምድም ጥሩ ነው፡፡ ከእኔም ጋር ኢትሃድ አሌክሳንደሪያ አስርቶኝ ነበር፡፡ አሁን ላይ ወደ ጥሩ አቋም ቡድናችን ተመልሷል፡፡


ታላት የሱፍ አምና አል አሃሊ ትሪፖሊን ለካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ አብቅተዋል፡፡ ልምድ ካላቸው ግብፃዊያን አሰልጣኞች መካከልም የሚመደቡ ናቸው፡፡ የስትራካ ስንብት በኃላ የዩሱፍ መምጣት ቡድኑ ላይ የፈጠረው ዋነኛ ለውጥ ምንድነው?

ስትራካ ከተጫዋቾች ጋር በእጅጉ ቅርበት ነበረው፡፡ እዚህ ግብፅ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች የሚደጥሩት ግንኙነት ከልክ ሲያልፍ ጥሩ አለመሆኑን በስትራካ ላይ በተፈጠረው ተረድቻለው፡፡ ስትራካ ተጫዋቾችን ከልክ ባለፈ መቅረቡ አለመታዘዝን እና ልምምድ ላይ ቸልተኛ መሆንን ፈጥሯል፡፡ ታላት የሱፍ ደግሞ ቀልድ አያውቅም፡፡ እዚ የግብፁ ሞሪንሆ ነው የሚሉት፡፡ እሱ ከመጣ ጀምሮ ማንም ተጫዋች ልምምድ ላይ አይቀልድም ስራውን አርፎ ይሰራል፡፡ የሱፍ በተጫዋቾቹ የሚከበር እና የሚፈራ መሆኑ ቡድኑን ጠቅሞታል፡፡ ይህም የቡድኑ መሻሻል እና ለውጥ ላይ አዎንታዊ ጎን እንዲኖረው አድርጎታል፡፡ በሁለቱም አሰልጣኞች ስልጠና ላይ ጥሩ ናቸው፡፡ ሆኖም አስቀድሜ የጠቀስኩት የአሰልጣኞች የግል ባህሪ ውጤታችን ላይ ተፅዕኖ አምጥቷል፡፡

በግልህ አምና ስኬታማ የሆነ ግዜን ነበር በኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ያሳለፍከው፡፡ በስሃም ይህንን እንደምትደግም ሲጠበቅ ነበር ሆኖም ይህ ሊሆን አልቻለም፡፡ ዘንድሮው ያስቆጠርካቸው ግቦችም አንሰዋል፡፡ የአቋም መቀዛቀዙ ከየት የመጣ ነው?

ጨዋታዎች ሲጀመሩ ከቡድኑ ጋር መላመድ ስለነበረብኝ ግቦችን ለማስቆጠር አልቻልኩም ነበር፡፡ ሆኖም እራሴን እስኪገርመኝ ድረስ የማገኛቸውን የግብ እድሎች አመክናለው፡፡ የማገኛቸው እድሎች ግብ መሆን የሚችሉ በመሆናቸው ወይ አግዳሚ እና ቋሚ ይገጭብኛል ወይ ግብ ጠባቂ ይመልሰዋል፡፡ ይህ የአጨራረስ ድክመት ትንሽ ግብ እንዳላስቆጥር ጎትቶኝ ነበር፡፡ ሌላው የቡድናችን አጨዋወት በተለይ በማጥቃት ሽግግሩ ላይ እኔን ያሳተፈ አለመሆኑ ነው፡፡ በኤል ሃርቢ ማጥቃቱ መሰረት የሚያደርገው እኔን ነበር ይህም ብዙ ግብ እንዳስቆጥር ረድቶኛል፡፡ እድለኛ አይደለሁም ማለት ይቻላል ከአሃሊ፣ ኤስማኤሊ፣ ናስር እና ራጋብ ጋር ስንጫወት ግብ ማስቆጠር እየተገባኝ ሳላስቆጥር ቀርቻለው፡፡ እስካሁን 22 ጨዋታዎችን በቋሚነት ተሰልፌ ተጫውቻለው፡፡ ግብ በመጀመሪያ ጨዋታዬን ነበር ያስቆጠርኩት ግን ደግሞ ለማስቆጠር ወራትን መጠበቅ አስፈልጎኛል፡፡ ጉጉት ነበር ይህም እኔን አልጠቀመኝም፡፡ ወደ ጨዋታው ትኩረት አድርጌ በመንቀሳቀስ ያለፉትን አራት ሳምንታት በተሻለ መጫወት ጀምሪያለው፡፡


የ2017/18 የውድድር ዘመንን ሂደት እንዴት ተመለከትከው?

ዘንድሮው ውድድር ፉክክር የበዛበት እና ጠንካራ ተጋጣሚዎች የመጡበት ነው፡፡ ጨዋታዎችን በ3 እና 4 ቀናት ልዩነት ስለምናደርግ ድካም ይኖራል ይህም ይበልጥ ሁሉንም ጨዋታዎችን ፈታኝ ያደርጋቸዋል፡፡


የስሞሃ ደረጃ በቻምፒየንስ ሊግ ወይም ኮንፌድሬሽን ዋንጫ በቀጣይ አመት ለመሳተፍ የቀረበ ነው፡፡ እቅዳችሁ ምንድነው?

እስከአራት እንወጣለን ብለን ነው ያቀድነው፡፡ ክለቡ ከፍተኛ በጀት ከሚያወጡ ክለቦች መካከል ነው፡፡ በኤል ጋይሽ ስንሸነፍ ሃላፊዎቹ መጥተው አነጋግረውን ነበር፡፡ እስከአራተኛ ደረጃ ያለውን ይዘን ማጠናቀቅ እንደሚገባን እና አምስተኛ ሆኖ መጨረስ እራሱ ተቀባይነት የለሌው መሆኑን አስገንዝበውናል፡፡ ከፔትሮጀት ከተጫወትን በኃላ ዛማሌክን፣ ኢስማኤሊ የምንገጥመው በሜዳች ነው፡፡ ዋዲ ደግላ ወራጅ ቀጠና ውስጥ በመገኘቱ ከባድ እንደሚሆን ገምተን ጨዋታውን ማሸነፍ ችለናል፡፡ ኤንፒ ጥሩ መነቃቃት ላይ ይገኛል ቢሆንም በቀጣዮቹ ጨዋታዎች ድል ማድረግ አያቅተንም፡፡ ይህም እቅዳችንን ለማሳካት ይረዳናል፡፡


ውድድሩ ፉክክር እና ፈተና የበዛበት ቢሆንም ለቻምፒዮንነት ግን አል አሃሊ አሁንም ለብቻው እየተጓዘ ይገኛል…

አዎ አሃሊ ጠንካራ ክለብ ነው፡፡ ጠንካራ የሚያደርጉት ብዙ ጉዳዮችን ቢኖሩም የተጋጣሚ ክለቦች በስነ-ልቦና ተበልጠው አሃሊን ለመግጠም መምጣታቸው ሁሌም ተሸናፊ እንዲሆኑ እና አሃሊ ሊጉን ያለተቀናቃኝ እንዲያሸንፍ እያደረጉት ነው፡፡ ተጋጣሚ ክለቦች እራሳቸው በስነ-ልቦና አውርደው እንዲሁም ለመከላካል ብቻ ስለሚጫወቱ አሃሊ ለማሸነፍ እምብዛም አይከብደውም፡፡ ደፍረው የሚጫወቱ ክለቦች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ እኔ ያየሁት አል መስሪ ብቻ ነው፡፡ ሁሌም አሃሊን ይፈትናል፡፡ አሰልጣኙ ሆሳም ሀሰን መሆኑ ተዳምሮ መስሪ ለአሃሊ ከባድ ተጋጣሚ ነው ሁሌም፡፡ ኢትሃድ እያለው ሆሳም ነበር አሰልጣኛችን አሃሊን ገጥመን 4-1 አሸንፈናቸዋል፡፡


በሊጉ አሰልጣኞች የሚቀያየሩት በፍጥነት ነው፡፡ ለዚህም ማሳየው ብዙ ነው ለምሳሌ ያህል አንተ ያለህበት ስሞሃ እራሱ በውድድር አመቱ ሁለተኛውን አሰልጣኝ ነው የቀጠረው፡፡ የአሰልጣኞች መቀያየር የፈጠረብህ ተፅዕኖ አለ?

አለ ማለት ይከብደኛል፡፡ ብዙ ግዜ ግብፅ ውስጥ አሰልጣኞች ሹም ሽር ከውጤት ጋር ይያያዛል፡፡ ሶስት ጨዋታ በተከታታይ የተሸነፈ አሰልጣኝ በአንድ ወር ውስጥ ሊባረር ይችላል፡፡ ውጤት መሰረታዊ ነው እዚህ ማምጣት ካልቻልክ በፍጥነት ትነሳለህ፡፡ ለእኔ ተፅዕኖ የለውም ምክንያም የሚሄዱት አሰልጣኝም ሆነ አዲስ የሚመጣው በአጨዋወት ፍልስፍና እምብዛም የተለያዩ አለመሆናቸው ነው፡፡ ታክቲክ እና ስልጠና ላይ ልዩነቶች ይኖራሉ ቢሆንም ግን በአመዛኙ በመልሶ ማጥቃት እና መከላካልን የሚመርጡ አሰልጣኞች የሚበዙበት ሃገር መሆኑ ተፅዕኖውን ይቀንሰዋል፡፡ በኢትሃድ (ታላት የሱፍ/ሆሳም ሀሰን)፣ ኤል ሃርቢ (ሻውኪ ጋሪብ/ሞክታር ሞክታር) እና  ስሞሃ (ፌሬንቼስክ ስትራካ/ታላት የሱፍ)  እስካሁን ሁለት ሁለት አሰልጣኞች ናቸው ያሰለጠኑኝ፡፡ የመሰለፍ እድል ባልተሰጠኝ ኤንፒ ውስጥ በአንድ ዓመት ውስጥ አራት አሰልጣኝ ነው የቀየርነው፡፡

የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች በዚህ ዓመት ላይ አይኖሩም፡፡ የማጣሪያ ጨዋታዎች መዘዋወራቸውን ተከትሎ ብሄራዊ ቡድኑ ከጨዋታዎች ይርቃል ተብሎ የሚጠበቀው ከዚህ በፊት ሲሰራበት በነበረው መንገድ፡፡ ምን ሃሳብ አለ በዚህ ላይ?

አዎ ልክ ነህ ጨዋታዎች ተዛውረዋል፡፡ ከሴራ ሊዮን ጋር የምናደርገው ጨዋታ መለወጡ አሁን ላይ ቡድናችን ጨዋታዎች እንዳይኖሩት ያደርገዋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ነው የአቋም መለኪያ ጨዋታ መዘጋጀት ያለበት፡፡ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ቢኖር ከሴራ ሊዮን ግጥሚያ አስቀድሞ ቡድኑን ለማሻሻል እና ለማዘጋጀት ይጠቅማል፡፡ የአቋም መለኪያ ግጥሚያዎችን ቢናደርግ እና ከጨዋታ ባይርቅ ቡድኑ ጥሩ ነው የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡


ግብፅ ከ27 አመታት በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ለዓለም ዋንጫ አልፋለች፡፡ አሁንም በአለም ዋንጫ ድባብ ውስጥ ትገኛለች እና ይህ አንተ ላይ የተለየ ስሜት ፈጥሮብሃል?

በሚገባ አለ! ወደ ዓለም ዋንጫው ያለፉበት ጨዋታ የተካሄደው እኔ በምገኘበት አሌክሳንደሪያ ነበር፡፡ ጠዋት ከስሞሃ ጋር ልምምድ ሰርተን ከሰዓት ተጫዋቾች ጨዋታውን እንዲመለከቱ እረፍት ተሰጥቶን ነበር፡፡ ካሸነፉ በኃላ ከተማው ቀውጢ ነው የሆነው፡፡ ለሊቱን በሙሉ ሲጨፍሩ እና ሲጮሁ ነው ያደሩት፡፡ ከጨዋታው ሳምንት አስቀድሞ ነው ከተማው የደመቀው፡፡ በ2012 ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ስታልፍ የነበረውን ግዜ ነው ያስታወሰኝ፡፡ እናም ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ ብታልፍ ብዬ ተመኝቼ ነበር በወቅቱ፡፡ በእርግጥ ለአፍሪካ ዋንጫ እና ዓለም ዋንጫ ማለፍ ፈፅሞ የተለያዩ ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *