የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 12ኛ ሳምንት እሁድ በተደረጉ 5 ጨዋታዎች ሲጀመር ኢኮስኮ እና ቡራዩ ወደ መሪዎቹ ራሳቸውን ያስጠጉበት ፣ አአ ከተማ ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገደበት ፣ አውስኮድ ወደ ድል የተመለሰበት ውጤቶች ተመዝግበዋል።
ቡራዩ ላይ ቡራዩ ከተማ አአ ከተማን አስተናግዶ 2-1 በማሸነፍ ወደ መሪዎቹ ሲጠጋ የምድቡ መሪ አዲስ አበባ ከተማ ለሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታ ሽንፈት አጋጥሞታል። በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ሁለቱ ቡድኖች በእንቅሳቃሴ ተቀዛቅዘው ታይተዋል፡፡ በመስመር በኩል አመዝነው የተጫወቱት አዲስ አበባ ከተማዎች በ10ኛው ምንያምር ጴጥሮስ ያሻገረውን ኳስ ፍቃዱ ዓለሙ በመግጨት በሞከረው ኳስ የሙከራ ቅድሚያውን ይዘዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ በድጋሚ ምንያምር ጴጥሮስ ከቀኝ መስመር ያሻገረው ኳስ ፍቃዱ ዓለሙ ወደ ግብ መሬት ለመሬት አክርሮ መትቶ የቡራዩ ከተማው አሸብር ደምሴ ቢያድነውም አቤል ዘውዱ የተመለሰውን ኳስ ወደ ግብነት ለውጦት ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡
በኳስ ቀጥጥር ላይ አመዝነው ሲጫወቱ የነበሩት ቡራዩ ከተማዎች ለግብ የቀረበ ሙከራ ለማደረግ 25 ደቂቃ ፈጅቶባቸዋል። በአንፃሩ በረጃጅም እና የመስመር ላይ ተሻጋሪ ኳሶች ላይ አመዝነው የተጫወቱት አዲስ አበባዎች በ30ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ዓለሙ ነፃ ሆኖ ያገኛትን ኳስ ሳይጠቀምባት ቀረ አረነሰጂ መሪነታቸውን ማጠናከር የሚችሉበት እድል ነበር።
በ35ኛው ደጀኔ በቀለ እና ዳዊት ታደሰ ተቀባብለው ወደ ውስጥ የገቡትን ኳስ ዳዊት ታደሰ የአዲስ አበባ ተከላካዮችን አልፎ ወደ ግብነት ለውጦታል፡፡ ከጎሉ በኋላ አአ ከተማዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሞከሩ ሲሆን በ40ኛው ደቂቃ በፍቃዱ ዓለሙ ያገኙትን ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ በ45ኛው ደቂቃ አብዲ ሁሴን ነፃ የግበ ዕድል አግኝቶ ያመከነው ኳስም ቡራዩ ከተማን መሪ ማድረግ የሚችል ዕድል ነበር፡፡
ኃይል የተቀላቀለበት እና ከፍተኛ የአሸናፊነት ፉክክር በታየበት ጨዋታ በ67ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር አቡበከር ደሳለኝ ያሻማውን ቅጣት ምት ጀሚል ከማል በግንባሩ በመግጨት ቡራዩን ከተመሪነት ወደ አሸናፊነት ያሸጋገረች ጎል አስቆጥሯል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ያፈገፈጉት ቡራዩ ከተማዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ ያደረጉት መከላከል ተሳክቶላቸው ሶስት ነጥብ አሳክተው ተመልሰዋል። የዕለቱ ጨዋታ የዳኙት ወጣቱ ፌዴራል ዳኛ ባህሩ ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር በመልካም ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ማድረጋቸው አድናቆት የሚቸረው ነው።
ኢትዮጵያ መድን እገዳ ከተነሳለት በኋላ የመጀመሪያውን ጨዋታ ከባህርዳር ከተማ ጋር አድርጎ 2-2 ተለያይቷል። ባህርዳር ላይ በተደረገው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ መድን በሀብታሙ መንገሻ ግብ መሪ መሆን ቢችልም ከዕረፍት መልስ ባህርዳር ከተማ በወንድሜነህ ደረጀ ጎል አቻ ሆኗል። በ78ኛው ደቂቃ ሚካኤል ደምሴ ኢትዮጵያ መድንን በድጋሚ መሪ ማድረግ ቢችልም በ85ኘው ደቂቃ እንዳለ ከበደ ባህርዳር ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አስችሏል።
ወደ ነቀምት ያመራው ኢኮሥኮ 2-1 አሸንፎ በመመለስ በመልካም ወቅታዊ አቋሙ ገፍቶበታል። የኢኮስኮ ሁለቱንም ግቦች ያስቆጠረው አበበ ታደሰ ነው። ወደ አዲስ አበባ የመጣው አማሬ ውሀ ስራ ደግሞ የካ ክፍለ ከተማን ገጥሞ 1-0 ማሸነፍ ሲችል ፌዴራል ፖሊስ ከ ወሎ ኮምቦልቻ ያለምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡
የምድቡ አንድ መርሀ ግብር ዛሬ ሱሉልታ ያያ ቪሌጅ ላይ ሲካሄድ ሱሉልታ ከተማ ሽረ እንዳስላሴን ያስተናግዳል። ደሴ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ እንዲሁም ለገጣፎ ለገዳዲ ከአክሱም ከተማ ወደ ሌላ ጊዜ የተሸጋገሩ ጨዋታዎች ናቸው።