የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንታዊ እና የስራ አስፈፃሚ ምርጫ ለሦስተኛ ጊዜ ተራዝሞ የካቲት 24 በአፋር ሰመራ ከተማ ይደረጋል ተብሎ ቀነ ቀጠሮ እንደተያዘለት ይታወቃል።
ከጅምሩ እያወዛገበ እና እያጨቃጨቀ አሁን ላይ የደረሰው ምርጫው ላይ አሁን እየተሰማ ያለው ጉዳይ ደግሞ ይበልጥ የምርጫውን አሰልቺ ሂደት የሚያንፀባርቅ ነው። ፊፋ ከዘጠኝ ቀን በፊት ምርጫውን አስመልክቶ በቀጣይ ሊደረግ ስለሚገባው ጉዳይ መልዕክት አዘል ደብዳቤ የላከ ሲሆን የደብዳቤው ሀሳብም ” ምርጫውን በካፍ እና በፊፋ የምርጫ ኮድ እንዲሁም በሀገራችሁ የምርጫ መተዳደርያ ደንብ መሰረት አካሂዱ” የሚል እና የዋና ፀሀፊዋ ፋትማ ሳሞራ ፊርማ ያረፈበት ነበር።
ሆኖም የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን ለዘጠኝ ቀናት ያህል ያስቆጠረውን ደብዳቤ ለህዝቡ እና ለሚዲያው ሳያሳውቅ መቅረቱ እያነጋገረ ይገኛል። እስከ ዛሬ ይህ ደብዳቤ ሳይገለፅ ለምን ማስቀመጥ አስፈለገ? የሚለውን ጥያቄ ይዘን ላቀረብነው ጥያቄ ” እስካሁን ለህዝቡም ሆነ ለሚዲያ ይፋ ያላደርግነው አብዛኛዎቹ የፌዴሬሽኑ አባላት ለቻን ውድድር እና ካፍ ኮንግረስ ወደ ሞሮኮ በመሄዳቸው ነው። በዛሬ እና በነገው እለት ለሚዲያው እናሳውቃለን” የሚል ምላሽ ነው ያገኘነው።
ወደ የካቲት 24 ቢገፋም በእለቱ ለመካሄዱ ምንም ዋስትና ያላገኘው የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ በአሰልቺነቱና በሴራ ንድፈ ሀሳብ ጉዞው ቀጥሎበታል።