ትላንት አንድ ጨዋታ የተስተናገደበት የሊጉ 15ኛ ሳምንት ዛሬ በጎንደር ፣ በይርጋለም ፣ በአዳማ እና በድሬደዋ አራት ጨዋታዎች ይደረጉበታል። የዛሬው ቅድመ ዳሰሳችንም እነዚሁኑ ጨዋታዎች የተመለከተ ይሆናል።
ፋሲል ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ
ሁለቱ ክለቦች ያሳለፍነውን ጥር ወር በተለያየ ሁኔታ ነበር ያሳለፉት። ወሩ ፋሲል ከተማ ያለመሸነፍ ሪከርዱን ከማጣት ባለፈ ተደጋጋሚ ሽንፈት ያስተናገደበት ሲሆን በአንፃሩ አርባምንጭ ከተማ ከአምስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኃላ ዳግም ነጥብ መሰብሰብ የጀመረበት ነበር። አምና 26ኛው ሳምንት ላይ አርባምንጭን አስተናግደው 2-0 መርታት የቻሉት ፋሲል ከተማዎች ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኃላ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ድል ማድረግ ቢችሉም ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና መሸነፋቸው የሚታወስ ነው። መነቃቃት የሚታይበት አርባምንጭ ከተማ ደግሞ አዳማ ከተማን እና ድሬደዋ ከተማን ሜዳው ላይ በመርታቱ እንዲሁም ከሀዋሳ አንድ ነጥብ ይዞ በመመለሱ ከሰንጠረዡ ግርጌ ወደ 12ኛነት ከፍ ብሏል። ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን በመሀል ዳኝነት የተመደበበት ይህ ጨዋታ ምንም ተስተካካይ ጨዋታ ለሌላቸው ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው ዙር ማሳረጊያ እንደመሆኑ መጠን ፋሲልም ሆነ አርባምንጭ አሸንፈው ነጥባቸውን ከፍ ለማድረግ እንደሚፋለሙ ይጠበቃል።
የፋሲል ከተማዎቹ ተከላካዮች አይናለም ኃይለ እና ያሬድ ባየህ አሁንም ያላገገሙ ሲሆን አርባምንጭ ከተማም ጉዳት ላይ የሚገኙትን ወንድሜነህ ዘሪሁን እና ወንደሰን ሚልኪያስን የማይጠቀም ይሆናል።
ሜዳው ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች ለኳስ ቁጥጥር የተሻለ ቦታ የሚሰጠው ፋሲል ከተማ አማካይ ክፍል ላይ ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል። ፋሲሎች በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ እንዳደረጉት ሁሉ የመስመር አጥቂዎቻቸውን ወደ ኃላ ስበው ለ 4-2-3-1 የቀረበ ቅርፅ እንደሚይዙ ቢታመንም አርባምንጭም በተመሳሳይ አምስት አማካዮችን የሚጠቀም በመሆኑ እና በጨዋታውም ጥንቃቄ አዘል የሆነ አቀራረብ ሊኖረው ስለሚችል ፋሲሎች እንደ ኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ በተለይ በመሀል እና በመስመር ተከላካዮች መሀል በተደጋጋሚ ሰብረው የሚገቡባቸውን አጋጣሚዎች ላንመለከት እንችላለን። አርባምንጭ ከተማ ደግሞ ከሚቀሙ ኳሶች መነሻነት ለብቸኛው አጥቂ ተመስገን ካስትሮ የመጨረሻ ዕድሎችን ለመፍጠር ዕንደሚያቅድ መገመት ይቻላል። እዚህ ላይ አርባምንጮች ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ባለፉት ጨዋታዎች በተለይ በተጨዋቾች የግል ስህተት ምክንያት ክፍተት እየፈጠረ ጎሎችን ሲያስተናግድ የታየው የባለሜዳዎቹ የኃላ ክፍል ነው። የከድር ሀይረዲን እና ሰይድ ሁሴን ጥምረት ከተመስገን ካስትሮ ጋር የሚኖረውም ፍልሚያ አንዱ የጨዋታው ተጠባቂ ነጥብ ነው። ሌላው አማካይ መስመር ላይ ዳግም እየተመለከትነው ያለነው የአማኑኤል ጎበና እና ምንተስኖት አበራ ጥምረት ከፋሲል ከተማዎቹ ዳዊት እስጢፋኖስ እና ሔኖክ ገምቴሳ ጋር የሚገናኙባቸው አጋጣሚዎች ናቸው። በእነዚህ አራት አማካዮች መሀል የሚኖረው የሜዳ ላይ ፉክክር ለቀሪዎቹ የቡድኖቻቸው ከወገብ በላይ ያሉ ተሰላፊዎች ኳሶችን በነፃነት በማድረስ በኩል እጅግ ወሳኝ ይሆናል።
ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ፌደራል ዳኛ ወልዴ ንዳው በመሀል ዳኝነት የሚመራው ይህ ጨዋታ ለሲዳማ ቡና የሊጉ የመጀመሪያው ዙር ማብቂያ ሲሆን ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ የአመቱ አስራሶስተኛ ጨዋታው ይሆናል። የአመቱን አጋማሽ ከሜዳው ውጪ ሶስት ነጥብ ሳያሳካ ያገባደደው ሲዳማ ቡና ሜዳው ላይ በሶስት አጋጣሚዎች ማጣጣም የቻለውን ድል ዛሬም ለመድገም ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። ሲዳማዎች መከላከያን እና መቐለን ከገጠሙባቸው ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማሳካታቸውም ከዚህኛው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ እንዲያገኙ የሚያስገድዳቸው ይሆናል። አምና 10ኛው ሳምንት ላይ ከሲዳማ የአቻ ውጤት ይዞ የተመለሰው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለመጨረሻ ጊዜ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ነጥብ ማግኘት የቻለው ከሀዋሳ ከተማ ያለግብ ባጠናቀቀው ጨዋታ ብቻ ነው። ይህን ተከትሎም ክለቡ በመጨረሻ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ሶስተኛው ሳምንት ላይ ወደ አርባምንጭ ተጉዞ ሳይጠበቅ አሸንፎ የተመለሰበትን ውጤት ዛሬም መድገም ከቻለ እየጨለመ ባለው የሊጉ ጉዞው ላይ የተወሰነ ተስፋን የሚፈነጥቅ ይሆናል።
ሲዳማ ቡና ጉዳት ላይ የሚገኙትን ፍፁም ተፈሪን እና ፍቅሩ ወዴሳን አገልግሎት አያገኝም። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩልም ቢኒያም አሰፋ ፣ ሞገስ ታደሰ እና ዐወት ገ/ሚካኤል በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሲሆኑ የሀይሌ እሸቱ መሰለፍም እርግጥ አልሆነም። ከዚህ ውጪ ግብ ጠባቂው ሱለይማን አቡ በክለቡ ጋር የነበረውን ውዝግብ በመፍታቱ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሁንም ሙሉ የቡድኑ የሜዳ ላይ መዋቅር መስተካከል ያለበት ሆኖ ውድድሩን ቀጥሏል። ከመጀመሪያው ጀምሮ አብሮት የዘለቀው የመከላከል ድክመቱ አሁንም አብሮት ያለ ሲሆን መሀል ሜዳ ላይ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ሀላፊነቱን በሚገባ ሲወጣ የቆየው ካሉሻ አልሀሰን ከዲዲዬ ለብሪ ጋር ፊት መስመር ላይ እንዲጣመር መሆኑ ተጨማሪ ችግር ሲፈጥርበት ታይቷል። በዛሬው ጨዋታም ቢሆኑ ቡድኑ ይዞት ይገባል ተብሎ ከሚጠበቀው ጥንቃቄ አዘል አቀራረብ አንፃር ግብ ሊያስቆጥር የሚችልበት አማታጭ ወደ ሁለቱ ተጨዋቾች በሚላኩ ኳሶች ላይ የተመሰረተ ነው። ኤሌክትሪክ ምንአልባት ሲዳማ እንደ መከላከያው ጨዋታ በማጥቃት ሂደት ላይ ሲሆን መሀል ሜዳ ላይ ሁለት ተጨዋቾችን የሚያስቀርበን አጋጣሚ ከደገመው ተጠቃሚ ሆኖ ከሚነጠቁ ኳሶች እነ ካሉሻን በቅብብል ማግኘት የሚችልበት አማራጭ አለ። ሲዳማ ከሶስቱ አማካዮቹ አንዱን ወደ ሶስቱ የፊት አጥቂዎች ቀርቦ እንዲጫወት የሚያደርግበት አኳኋን በሳጥን ውስጥ በርካታ ግብ ሊያስቆጥሩ የሚችሉ ተጨዋቾችን ሲያስገኝለት ቢታይም አማካይ ክፍላቸው በጥሩ ውህደት ደረጃ ላይ ከሚገኙ ክለቦች ጋር ግን በእጅጉ ችግር ላይ ሊጥለው እንደሚችል ይታመናል። ሆኖም የአዲስ ግደይ ፣ ባዬ ገዛሀኝ እና ሀብታሙ ገዛሀኝ ጥምረት ወደ ቀኝ መስመር አጥቂነት ሚና እየቀረበ ከሚጫወተው ትርታዬ ደመቀ የሚነሱ ኳሶችን ወደ ግብነት መቀየር ከቻለ ይህን ስጋት ማስቀረት ይቻላል። በጥቅሉ ግን ጨዋታው ኤሌክትሪክ ጥንቃቄን በመምረጥ ወደኃላ ተስቦ የሚገኙ እድሎችን ወደ እነ ዲዲዬ ለብሪ በማድረስ ሲዳማ ደግሞ በተለይ በቀኝ መስመር ባደላ እና ሶስቱን የፊት አጥቂዎቹን ታሳቢ ባደረገ የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚጠመድበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
አዳማ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር
አዳማ በኦሮሚያ ደርቢ በሳምንቱ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን ጨዋታ ታስተናግዳለች። ፌደራል ዳኛ ተካልኝ ለማ እንደሚመራው የሚጠበቀው ይህ ጨዋታ በእኩል 21 ነጥቦች በግብ ልዩነት አራት እና አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ጅማ አባ ጅፋርን እና አዳማ ከተማን የሚያገናኝ መሆኑ ከደርቢነቱ ባለፈ የቡድኖቹ ወቅታዊ አቋም የጨዋታውን አስፈላጊነት ከፍ አድርጎታል። ባለሜዳዎቹ አዳማዎች ከሜዳቸው ውጪ በአርባምንጭ ከደረሰባቸው ሽንፈት ውጪ አዲስ አበባ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን እንዲሁም በሜዳቸው ኢትዮጵያ ቡናን እና ወልዋሎ ዓ.ዩን በመርታታቸው ያገኟቸው ዘጠኝ ነጥቦች ከተቀዛቀዘ አጀማመር በኃላ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ መልሷቸዋል። ከታህሳስ ወር ጀምሮ ራሱን በሚገባ ያሻሻለው ጅማ አባጅፋርም በቅዱስ ጊዮርጊስ ከገጠመው ሽንፈት ውጪ አስገራሚ ጉዞ እያደረገ ይገኛል። በእነዚህ ጊዜያት አባጅፋር ካሳካቸው አምስት ድሎች ውስጥ አርባምንጭን እና ደደቢትን ከሜዳው ውጪ ማሸነፉ ደግሞ ዛሬ በሜዳው ከማይደፈረው አዳማ ከተማ ጋር የሚደረገውን ጨዋታ ይበልጥ አጓጊ ያደርገዋል። የዛሬው ጨዋታ አሸናፊውን ቡድን ይበልጥ ወደ ሊጉ መሪዎች የሚያስጠጋው በመሆኑ ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበትም ይጠበቃል።
አዳማ ከተማ ሚካኤል ጆርጅ ፣ ሱራፌል ዳኛቸውን እና ሙጂብ ቃሲምን በጉዳት ሳቢያ በጨዋታው ላይ የማይጠቀም ሲሆን የጅማ አባ ጅፋሮቹ ኦኪኪ አፎላቢ እና መላኩ ወልዴም ከጉዳት አልተመለሱም። በተጨማሪም በጅማ በኩል ሔኖክ ኡዱኛ ቅጣት ላይ የሚገኝ ሲሆን ረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ከነበሩ ተጨዋቾች መሀል ደግሞ ጌቱ ረፌራ በተጠባባቂነት ጨዋታውን ሊጀምር የሚችልበት ዕድል እንዳለ ሲሰማ ዝናቡ በፋአ እና አሸናፊ ሽብሩ ግን አሁንም አላገገሙም።
ጅማ አባ ጅፋር ከሜዳው ውጪ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የሚቀርብበት አግባብ እንዲሁም አዳማ ከተማም ሜዳው ላይ ወደ ፊት ገፍቶ የሚጫወት ቡድን መሆኑ ጨዋታው ቢያንስ ግቦች እስኪቆጠሩ ድረስ ማጥቃትን መሰረት ያደረገ ጥሩ ፉክክር እንደሚያስተናግድ ያመላክታል። የአዳማ ከተማ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር የተከላካይ መስመራቸውን ወደ መሀል ሜዳ አስጠግተው ለሚጫወቱ ቡድኖች ፈተኝ ያደረገው ቢሆንም ከጅማ አባጅፋር ተመሳሳይ ክፍተት ያገኛል ተብሎ ግን አይጠበቅም። የአባጅፋር የተከላካይ መስመር ካለው ጥንካሬ በተጨማሪ የአማካይ ክፍሉም የመከላከል ተሳትፎ ከፍ ያለ ነው። በመሆኑም የአዳማ አማካዮች ቡድኑ ኳስ በሚቆጣጠርበት ወቅት በተቃራኒ ሜዳ ላይ በሚደረጉ ቅብብሎች ተጋጣሚያቸውን ማስከፈት ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ሂደት ውስጥም የቡድኑ ጥቃት ዋና መሰረት የሆነው የመስመር አማካይ በረከት ደስታ ሚና ከፍተኛ ይሆናል። በተለይም ተጨዋቹ ከግራ መስመር በሚነሳበት አጋጣሚ ሔኖክ አዱኛን በቅጣት ከማያገኘው የአባ ጅፋር የቀኝ መስመር ጋር የሚገናኝበት ቅፅበት ወሳኝ ይሆናል። ከበረከት በተጨማሪም አዳማዎች መሀል ሜዳ ላይ ከከንአን ማርክነህ የሚነሱ ኳሶች ወደ ፊት አጥቂው ዳዋ ሁቴሳ የሚደርሱበትን የቅብብል ፍሰት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ሂደት ውስጥም ከንአን ማርክነህ ከይሁን እንዳሻው ጋር የሚኖረው ፍልሚያ ሌላው ተጠባቂ ነጥብ ይሆናል። የጅማ አባጅፋር የማጥቃት ሂደትም ቢሆን የሚገናኘው ከጠንካራ የተከላካይ መስመር ጋር ነው። በኢስማኤል ሳንጋሪ ጥሩ ሽፋን የሚሰጠው የአዳማ የኃላ መስመር ያለ ሙጂብ ቃሲምም በጥንካሬው መዝለቅ እንደሚችል የወልዋሎው ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ አሳይቷል። በተመሳሳይ ያለ ኦኪኪ አፎላቢ በአስፈሪነቱ የገፋበት የአባጅፋሮቹ ዮናስ ገረመው ፣ ሔኖክ ኢሳያስ እና ተመስገን ገ/ኪዳን የማጥቃት ጥምረትም እንደ ደደቢቱ ጨዋታ ሁሉ መሀል ሜዳ ላይ ከሚፈጠር ብልጫ በመነሳት በፍጥነት የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር የማስጨነቅ መንገድ በዛሬው ጨዋታ ላይ ውጤት ለማግኘት መደገም ይኖርበታል።
ድሬደዋ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ
ደካማ የውድድር ጊዜ እያሳለፉ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች በታችኛው የደረጃ ሰንጠተዡ ክፍል ላይ ይገኛሉ። ከወራጅ ቀጠናው መውጣት የተሳነው ድሬደዋ ከተማ አዲስ አበባ ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ ጠንከር ብሎ ቢታይም ሳምንት ወደ አርባምንጭ ተጉዞ ሽንፈት አስተናግዷል። ቡድኑ ከሁለቱ ጨዋታዎች በፊትም በኢትዮጵያ ቡና ሜዳው ላይ መሸነፉ የሚታወስ ሲሆን በሶስቱ ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለውም አንድ ግብ ብቻ ነበር። በ14ኛው ሳምንት ሜዳው ላይ ሀዋሳን ማሸነፍ የቻለው ወልዋሎም ቢሆን ማሸነፉ ከተጋጣሚው የተሻለ ቢያደርገውም ከዚያ አስቀድሞ በተለይ ከሜዳው ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ሶስት ግቦች እየተቆጠሩበት ሲሸነፍ መቆየቱ ለዚህኛው ጨዋታ ስጋትን የሚጭርበት ነው። ፌደራል ዳኛ አክሊሉ ድጋፌ የሚመራው ይህ ጨዋታ ለወልዋሎ የመጨረሻው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በመሆኑ ማሸነፍ እና ተስተካካይ ጨዋታ ካላቸው ተከታዮቹ ርቆ መቀመጥ ለቀጣይ ጉዞው ወሳኝ ይሆናል። ከዚህ ሌላ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ድሬደዋ ከተማም ከሁለተኛው ሳምንት በኃላ መልሶ ማግኘት ወዳልቻለው አሸናፊነት ተመልሶ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት አስፈላጊ የሆነ የመጨረሻው የሜዳ ላይ ጨዋታው ነው።
በድሬደዋ ከተማ በኩል የረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኙት ሳምሶን አሰፋ ፣ ዘነበ ከበደ እና ሀብታሙ ወልዴ ሌላ የጉዳት ዜና ያልተሰማ ሲሆን ወልዋሎ ዓ.ዩ ግን ከኤፍሬም ጌታቸው ፣ እዮብ ወ/ማርያም እና ሙሉአለም ጥላሁን በተጨማሪ ፕሪንስ ሰቨሪንሆም በጉዳት ምክንያት እንደሚያጣ ተነግሯል።
ድሬደዋ ከተማ አጨዋወቱ ለማጥቃት ቦታ መስጠት ከጀመረበት የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ስንብት በኃላም ቢሆን ግብ የማስቆጠር ችግሩ እንደቀጠለ ነው። ግብ ከማስቆጠርም በላይ ቡድኑ በተደራጀ አጨዋወት የተጋጣሚ የመከላከል ዞን ውስጥ የሚገባባቸው አጋጣሚዎችም ጥቂት ናቸው። ድሬዳዋ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ሰሞንኛ ግብ አስቆጣሪው ኩዋሜ አትራምን ከፊት ለብቻው በማድረግ እና የአማካይ ክፍል ቁጥር በመጨመር ከወትሮው በተለየ መሀል ሜዳ ላይ ተጠናክሮ ለመቅረብ ሞክሯል። ይህ አካሄድ በቅዱስ ጊዮርጊሱም ሆነ በአርባምንጩ ጨዋታ ቡድኑ እንደልቡ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠርን ቀላል ባያደርግለትም በጊዜ ሂደት በሚፈለገው መጠን መዋሀድ ከቻለ ግን የተሻለ ውጤት ሊያስገዝኝለት እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ነበር። በዛሬው የወልዋሎ ጨዋታም ቡድኑ ተመሳሳይ አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል። ወልዋሎ ውጤታማ በነበረበት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ የሙሉአለም ጥላሁን ከድር ሳሊህ እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ከፊት የነበረው ጥምረት ወሳኝ ነበር። ሆኖም የሙሉአለም እና ፕሪንስ አለመኖር የሚፈጥረው ክፍተት በቀላሉ የሚተካ አይመስልም። ከዚህ ሌላ ቡድኑ ለማጥቃት በሚገደድባቸው ደቂቃዎች ላይ ሙሉ አቅሙን ሲጠቀም ከኃላ የሚተወው ክፍተትም ዋነው ደካማ ጎኑ ሆኖ ታይቷል። በዚህም ጨዋታ ተመሳሳይ ክፍተት ከተገኘ የወልዋሎ የተከላካይ መስመር ከኩዋሜ አትራም እንቅስቃሴ ጋር የሚገናኝበት ሁኔታ ወሳኙ የጨዋታው አጋጣሚ ይሆናል። የወልዋሎ አጥቦ የመጨዋት ልምድ ያለው የአማካይ ክፍል የማጥቃት ሂደት ከኢማኑኤል ላርያ ጀርባ ለመገኘት እንዲሁም በዘላለም ኢሳያስ የሚመራው የባለሜዳዎቹ የአማካይ ክፍልም እንዲሁ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ስኬታማ ቅብብልን በማድረግ የግብ ዕድሎችን ሊፈጥር የሚችልበት አማራጭ ለሁለቱም ክለቦች አሸናፊነት ወሳኝ የሚሆነው የመሀል ሜዳ ፍልሚያ ነው።