በካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሊጫወት የነበረው አል ሰላም ዋኡ ወደ አዲስ አበባ እንደማይመጣ ተረጋግጧል፡፡ ክለቡ ከሐሙስ ጅመሮ በሚቀያየር ሰዓት እንደሚመጣ ቢነገርም ይህ ባለመሆኑ በህጉ መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አንደኛው ዙር አላፊ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሃላፊዎች ዛሬ ጠዋት ከ3 ሰዓት ጀምሮ የአል ሰላምን መምጣት ሲጠባበቁ የቆዩ ሲሆን ፌድሬሽኑ ከኬንያዊው የጨዋታ ኮሚሽነር ጋር በመሆን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አሳውቋል፡፡ አል ሰላም ዋኡ በተደጋጋሚ ለተላከለት መልዕክትም ምላሽ ሳይሰጥ በመቅረቱ የቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ቅዳሜ ሲደረግ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተወካዮች ብቻ ተገኝተዋል፡፡ ሆኖም ዛሬ 10፡00 ሊደረግ የነበረው ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተያዘለት ሰዓት ይቀጥላል፡፡ በህጉ መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳ ላይ ብቻውን የሚገኝ በመሆኑ እንዲሁም ተጋጣሚው በሰዓቱ ባለመገኘቱ ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያልፍ ይሆናል፡፡
ሌላኛው የደቡብ ሱዳን ክለብ የሆነው አል ሂላል ጁባ ከሜዳው ውጪ ቱኒዚያ ላይ ላለበት ጨዋታ በግዜው መድረስ ባለመቻሉ ከውድድር ውጪ ሲሆን በተመሳሳይ መንገድ አል ሰላም ዋኡ ይህ እጣ የሚደርሰው ይሆናል፡፡ በ2016 በወጣው እና በፀደቀው የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት ሁለቱ ክለቦች የገንዘብ ቅጣት እና እገዳ የሚጠብቃቸው ይሆናል፡፡
ሁለቱም ክለቦች ጨዋታዎቻቸው እንዲራዘሙላቸው ለካፍ ጥያቄ አቅርበው ውድቅ ተደርጎባቸዋል፡፡ በደንቡ መሰረት አንድ ክለብ የጨዋታ ቀን ለውጥ መጠየቅ የሚችለው ከ20 ቀናት በፊት ነው፡፡ በቅድመ ማጣሪያ ዙር ጨዋታዎች ላይ እራሱን ከውድድር የሚያገል ቡድን 5ሺ የአሜሪካ ዶላር የሚቀጣ ሲሆን ለሁለት ተከታታይ ግዜያት በአፍሪካ ክለቦች ውድድር ላይ እንዳይወዳደር ይታገዳል፡፡ የአንድ ሃገር እግርኳስ ፌድሬሽን/ማህበር ክለቦቹ በአፍሪካ የክለቦች ውድድሮች ላይ እንደሚሳተፉ አረጋግጦ በውድድሮች ላይ የማይካፈሉ ከሆነ ለሚያገጥመው ኪሳራ በካፍ ዲስፕሊን ኮሚቴ ይጠያቃል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አንደኛው ዙር በቀጥታ ማለፉን ለማረጋገጥ ሰዓታትን ብቻ መጠበቅ አለበት፡፡ በአንደኛው ዙር ክለቡ ከዩጋንዳው ኬሲሲኤ እና የማዳጋስካሩ ስናፕስ ስፖርት አሸናፊ ጋር ይጫወታል፡፡ አንታናናሪቮ ላይ ሁለቱ ክለቦች ቅዳሜ ተጫውተው ስናፕስ በፌኖሶአ ራቶሎጃናሃሪ እና ፋራንሲስ ራፋራላሂ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች በሜዳው 2-1 ኬሲሲኤን አሸንፏል፡፡ የኬሲሲኤን ወሳኝ ከሜዳ ውጪ ግብ ዴሪክ ንስምባቢ ከመረብ አዋህዷል፡፡