በተለያዩ ምክንያቶች ሳይደረጉ በተስተካካይነት ተይዘው የቆዩ የሊጉ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ሲደረጉ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በ 11 ሰዐት ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን የሚያስተናግድ ይሆናል። የዛሬው ዳሰሳችንም ይህንን ጨዋታ የተመለከተ ነው።
Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ
ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው የዛሬው ጨዋታ ለአዳማ ከተማ የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ሲሆን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ 13ኛው መርሀ ግብር ነው። ከዚህ ባለፈ ጨዋታው የአቻ ሪከርዳቸው ከፍ ያሉ ቡድኖችንም ነው የሚያስተናግደው። እስካሁን አዳማ በሰባት እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ በስድስት ጨዋታዎች ከተጋጣሚዎቻቸው ጋር ለበርካታ ጊዜ ነጥብ በመጋራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ተሰልፈዋል።
ከተስተካካይ ጨዋታዎቹ ብዛት እና እንደወትሮው ካልሆነው አቋሙ መነሻነት ስድስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጎንደር ላይ ፋሲል ከተማን ካሸነፈበት ጨዋታ በኃላ ወደ ድል አልተመለሰም። የወላይታ ድቻው ሽንፈት እና ከድሬደዋ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋራበት ጨዋታ ወደ መሪው መጠጋት የሚችልበትን ዕድል እንዳይጠቀምበት አድርጓል። ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን አዲስ አበባ ላይ ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ሽንፈት ባይገጥመውም ማሸነፍ የቻለው ግን በሶስቱ ብቻ ነበር። በቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች አቻ ሲለያይ ከእነዚህም መሀል ሁለቱ ግብ ያልተቆጠረባቸው ጨዋታዎች ነበሩ። ተጋጣሚው አዳማ ከተማ በአንፃሩ የተሻለ አቋም ላይ ያለ ይመስላል። ቡድኑ በሳምንቱ መጨረሻ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር አቻ ቢለያይም ከዚያ አስቀድሞ አርባምንጭ ላይ ከደረሰበት ሽንፈት ውጪ ሶስት ድሎችን ማስመዝገብ ችሏል። አዳማ ከተማ ከእስከዛሬው የተሻለ በሚባል ሪከርድ ዘንድሮ ከሜዳው ውጪ ሁለት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ 3 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል። የተሸነፈው በወልዲያ እና በአርባምንጭ ብቻ ነው። በመሆኑም አምና በመጀመርያው ዙር ከሜዳው ውጪ ከሰበሰባቸው ስድስት ነጥቦች ዘንድሮ በተሻለ ሁኔታ ዘጠኝ ነጥቦችን አሳክቷል። አነጋጋሪ በሆነ ሁኔታ የሰኞውን የደደቢት እና የመከላከያ ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የመሩት ፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወ/ጊዮርጊስ በድጋሚ የተመደቡበት የዛሬው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች የመጀመሪያው ዙር ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ራሳቸውን በዋንጫው ፉክክር ውስጥ የተሻለ ደረጃ ላይ ለማስቀመጥ ለማሸነፍ የሚፋለሙበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ከወቅታዊ አቋማቸው አንፃር የጨዋታው ጥንካሬ የተጠበቀ ቢሆንም የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ታሪክ ግን ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደላ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን ከመጨረሻዎቹ ስድስት ግንኙነታቸው ውስጥ 2007 ላይ ብቻ በአንድ አጋጣሚ አሸንፎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን አዲስ አበባ ላይ በተገናኙባቸው 16 ጨዋታዎች አንዴም ሽንፈት ያልገጠመውም። በዚህም 13 ጊዜ አሸንፎ 3 ጊዜ አቻ ወጥቷል። ዛሬ ከሜዳው ውጪ በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የመጀመሪያውን ድል ለማግኘት ወደ ሜዳ የሚገባው አዳማ ከተማ በአዲስ አበባዎቹ 16 ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው ስድስት ግቦችን ብቻ ሲሆን በአንፃሩ 32 ግቦችን አስተናግዷል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ 32 ግቦች መሀል ሰባቱ የተቆጠሩት ቡድኖቹ 2004 ላይ በተገናኙበት እና ባለሜዳዎቹ 7-0 ድል ባደረጉበት ጨዋታ ነበር። ሆኖም ከሶስቱ አቻዎች ሁለቱን ባለፉት ሁለት የውድድር አመታት ያሳካው አዳማ ከተማ ባለፉት ተከታታይ አራት ጨዋታዎች በጊዮርጊስ አልተሸነፈም። በጥቅሉ እስካሁን ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 32 ጊዜ ሲገናኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ 17 ድል በማስመዝገብ የበላይ ሲሆን አዳማ ከተማ 7 ጊዜ አሸንፏል፡፡ 8 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ 43 ፣ አዳማ ከተማ 23 ጎሎች አስቆጥረዋል፡፡
ከናትኤል ዘለቀ ውጪ ረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ የሰነበቱት የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ሳላዲን ሰይድ ፣ ታደለ መንገሻ እና አሜ መሀመድ ወደ ልምምድ የተመለሱ ሲሆን ሮበርት ኦዱንካራ እና አስቻለው ታመነም ማገገመቸውን ሰምተናል። በአዳማ በኩል ደግሞ ሙጂብ ቃሲም ከጉዳት ሲመለስ ተስፋዬ በቀለ ፣ ሚካኤል ጆርጅ እና ሱራፌል ዳኛቸው ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጨዋቾች ናቸው።
Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ
ጨዋታው የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በማግኘት ላይ ተመስርቶ የሚደረግ እንደሚሆን ይጠበቃል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ይህን ለማሳካት በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ያልተለወጠው ከሙሉአለም መስፍን ፊት የምናየው የምንተስኖት አዳነ እና አብዱልከሪም ኒኪማ ጥምረት ከአዳማዎቹ ከነአን ማርክነህ እና ኢስማኤል ሳንጋሪ ጋር የሚገናኙባቸው አጋጣሚዎች ወሳኝነት ይኖራቸዋል። ለአዳማ ከተማ አደገኛ እንቅስቃሴ መነሻ የሆኑት የመስመር አማካዮቹ በረከት ደስታ እና ሲሳይ ቶሊ ከሁለቱ የመሀል አማካዮች እንዲሁም ከመስመር ተከላካዮቻቸው የሚደርሷቸውን ኳሶች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ክልል ይዘው የሚገቡበት ፍጥነት እና ለነዳዋ ሁቴሳ የሚያደርሱበት አኳኃን አዳማዎች ለሚፈጥሯቸው የግብ ዕድሎች ዋነኛ አማራጮች ናቸው። በተለይም የበረከት ደስታ በዚህ አይነቱ አጨዋወት በሁለቱም መስመሮች የተካነ መሆን ተጨዋቹ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚያደርገውን ፉክክር ተጠባቂ ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ የአዳማ ከተማ ስብስብ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመሩን ወደ መሀል ሜዳ አስጠግቶ ለሚጫወት ቡድን ተስማሚ መሆን የእንግዶቹ ሌላው ጠንካራ ጎን ነው። ከከንአን ማርክነህ የሚነሱ ረዥም ኳሶች እና የበረከት ደስታ ጥሩ የሚባሉ የመጨረሻ ኳሶች ለፈጣኖቹ አጥቂዎች ቡልቻ ሹራ እና ዳዋ ሁቴሳ የመልሶ ማጥቃት ሂደት ግብዐት የሚሆኑ ናቸው።
በአዳማ በኩል በተጋጋሚ የሚታየው በፍጥነቱ ዝግ ያለ የመከላከል ሽግግር ደግሞ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ በር የሚከፍት ነው። የተጋጣሚ የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎች በሚፈለገው ፍጥነት የመከላከል ቅርፃቸውን አለመያዝ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አማካዮች የተሻለ የቅብብል ነፃነትን የሚሰጥ ነው። ከዚህ መነሻነትም ከቅዱስ ጊዮርጊስ የአማካይ ክፍል ወደ መስመር አጥቂዎቹ የሚላኩ ኳሶች ቡድን ንፁህ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሊጠቀምባቸው የሚችልበት ዕድል አለ። ከዚህ ውጪ አቡበከር ሳኒ በፊት አጥቂነት የሚሰለፍ ከሆነ የተጨዋቹ ከኳስ ውጪ ያለ ተከላካዮችን ጫና ውስጥ የሚከት አጨዋወት ዛሬ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሊጠቅም የሚችልበት አጋጣሚ ይንምራል። በዚህም ተጨዋቹ አልፎ አልፎ ስህተቶችን ሲሰራ ከሚታየው የአዳማ ከተማ የመሀል ተከላካዮች ጥምረት ፊት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተጠባቂ ይሆናል።