የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስመራጭ ኮሚቴ ከቀናት በኋላ ዛሬ ያደረገው ስብሰባ ምርጫው አስቀድሞ በወጣለት ቀን እንዲደረግ ከሰምምነት በመድረስ ተጠናቋል።
የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዘዳንት እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ከመስከረም 30 ጀምሮ ይደረጋል ቢባልም በተለያዩ አሰልቺ ምክንያቶች የተነሳ ሳይደረግ ከአንዴም ሦስቴ ሲገፋ ቆይቶ በመጨረሻም የካቲት 24 ላይ እንደሚደረግ አስመራጭ ኮሚቴው በዛሬው ስብሰባው ወስኗል።
በጁፒተር ሆቴል የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን መኮንንን ጨምሮ ከቤንሻንጉል ክልል እና ደቡብ ክልል ተወካዮች በስተቀር አብዛኛው የኮሚቴው አባላት የተገኙበት ስብሰባ ከዚህ ቀደም ከተደረጉ የአስመራጭ ኮሚቴ ስብሰባዎች እጅግ በሰከነ ሁኔታ በመግባባት የተጠናቀቀ ሆኖ አልፏል ። የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን መኮንን በመሩት ስብሰባ በግል ፍቃዳቸው ያለ አስመራጭ ኮሚቴው ይሁንታ ወደ ፊፋ የሚልኩት ተደጋጋሚ ደብዳቤዎች ስህተት እንደሆኑ በመቀበል በቀጣይ ከእንደነዚህ ያሉ ድርጊቶች በመቆጠብ የምርጫው ሂደት እንዳይስተጓጓል ከኮሚቴው አባላት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልፀዋል ።
አስመራጭ ኮሚቴው በዛሬው ስብሰባ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል ምርጫው የሚካሄድበትን ቀን አስቀደሞ በወጣለት መርሀግብር የካቲት 24 በአፋር ከተማ ሰመራ እንደሚደረግ የወሰነ ሲሆን ከየካቲት 15 ጀምሮ በምርጫው ላይ ተሳታፊ ለሆኑ አካላት በሙሉ ጥሪ እንዲደረግ እንዲሁም ፊፋም ሆነ ካፍ በምርጫው ዕለት ታዛቢ እንዲልኩ በደብዳቤ ጥሪ እንዲደርሳቸው ወስነው ወጥተዋል ።
በአሰልቺ ሁኔታ እና በውዝግቦች ታጅቦ እዚህ በደረሰው የምርጫ ሂደት የዛሬው ስብሰባ ላይ በአስመራጭ ኮሚቴዎቹ መካከል ምንም አይነት የአቋም ልዩነትም ሆነ ከዚህ ቀደም የመከራከርያ እርስ ሆነው ይቀርቡ የነበሩ የኮሚቴ አባላቱ እና የተመራጭ እጩ አባላት ተገቢነት ዙርያ የተነሱ ጥያቄዎች ሁሉ በዛሬው ስብሰባ ላይ አንዴም አልተነሱም። ሆኖም መጀመርያውንም ይህ ሁሉ ከፍተኛ ገንዘብ እና ጊዜ እስካሁን መባከኑ ለምድነው የሚል ጥያቄ እና ሀላፊነቱን የሚወስደው አካል ማን እንደሆነ አለመታወቁ ነገሩን አስገራሚ አድርጎታል።