በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ የወላይታ ድቻ ተጋጣሚ የሆነው የዛንዚባሩ ዚማሞቶ የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ ከሰአት በሀዋሳ አለምአቀፍ ስታድየም ሰርቷል፡፡
የዚማሞቶ ቡድን 32 ልዑካንን በመያዝ ከትላንት በስቲያ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ትላንት ቀን ላይ ሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል ማረፊያውን በማድረግ ዛሬ ሁለተኛ እና የመጨረሻ ልምምዱን 10:00 ላይ ሰርቷል። የዛንዚባር የመከላከያ ቡድን የሆነው ዚማሞቶ በመጨረሻ ልምምዱ የአካል ብቃት ፣ የመልሶ ማጥቃት እና ተደራጅቶ የመስራት ስራን ሲሰሩ ተመልክተናል።
28 ክለቦችን በሚያሳትፈው እና በሁለት ምድብ ተከፍሎ በሚደረገው የዛንዚባር ሊግ ምድብ ለ የሚገኘው ዚማሞቶ እና የወላይታ ድቻ የመልስ ጨዋታ ነገ በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየም ሲካሄድ ጨዋታውን የሚመሩት የጅቡቲ ዳኞች እና ሲሸልሳዊ ኮሚሽነር ትላንት ምሽት ሀዋሳ በመግባት ማረፊያቸውን በሌዊ ሆቴል አድርገዋል፡፡
የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ እና የዚማሞቶው ዋና አሰልጣኝ ሙሶማ አብዱልሀኒ ስለነገው ጨዋታ የሰጡትን አስተያየት በቀጣይ ይዘንላችሁ የምንቀርብ ይሆናል፡፡