በካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኬሲሲኤን አዲስ አበባ ላይ አስተናግዶ ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች ለጋዜጠኞች ስለጨዋታው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ማኑኤል ቫዝ ፒንቶ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ስለጨዋታው
በመጀመሪያ ደጋፊዎቻችን ላሳዩት ድጋፍ ማመስገን እፈልጋለው፡፡ ጨዋታው ሁለት የተለያዩ ክፍሎች ነበሩት፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ በቀኝ መስመር አጋድለን እድሎችን ለመፍጠር ሞክረናል፡፡ ሆኖም ኳስን ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልሉ ማድረስ ይገባን ነበር። ይህም ሊሆን አልቻለም፡፡ የኬሲሲኤንም የአጨዋወት ብቃት እናውቃለን ፤ በብዛት በመልሶ ማጥቃት ነው የሚጫወቱት፡፡ ሁለት እና ሶስት የሚሆኑ ፈጣን ተጫዋቾቻቸው ከፊት መስመር ላይ ይገኙ ነበር፡፡ ይህም ለእኛ ቡድን አስቸጋሪ ነበር ምክንያቱም ለማሸነፍ ፍላጎት ስለነበር ከኃላ መስመር ክፍተቶችን ፈጥረናል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽም ጥሩ ጅማሮ ነበረን፡፡ ኳስን ተቆጣጥረናል እንዲሁም ግብ ማስቆጠር የምንችልባቸውን እድሎች ፈጥረናል፡፡ ተጋጣሚያችን አሁንም መልሶ ማጥቃትን ነበር የሚጠቀምው፡፡
ወደ ምድብ የማለፍ እድል
ካምፓላ የሚኖረው ላይ ተመሳሳይ ነው የሚሆነው፡፡ እዛም የማግባት እድሎችን ልናገኝ እንችላለን፡፡ ዛሬ እቅዳችን የነበረው ማሸነፍ እና ግብ አለማስተናገድ ነበር፡፡ በሜዳ ላይ ግብ አለማስተናገድ ወሳኝ ነው፡፡ ከሜዳችን ውጪ ግብ ካስቆጠረን ለተጋጣሚያችን አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ኬሲሲኤ ካምፓላ ላይ ያለው ቅርፅ የተለየ ነው፡፡
ማይክ ሙቴይቢ – ኬሲሲኤ
በጨዋታው እና ባገኘው ውጤት ደስተኛ ነኝ፡፡ ከዚህም የተሻለ ውጤት ማግኘት እንችል ነበር፡፡ ጨዋታው ገና አላለቀም፡፡ የመልስ ጨዋታ ስላለን በጥንቃቄ እንዝጋጃለን፡፡ እኔ እንደማስበው ያለግብ አቻ መጠናቀቁ ትንሽ ነገሮችን አስቸጋሪ ሊያረግ ይችላል፡፡ ሁሉም ነገር በመልሱ ጨዋታ መልስ የሚያገኝ ይሆናል፡፡