በብሩክ ገነነ እና ሳሙኤል የሺዋስ
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም በጀርመኗ ሙኒክ ከተማ በጠራዉ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በየሀገራቱ ዉስጥ የሚደረገዉ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ የተሻለ ፕሮፌሽናል መልክ እንዲኖረዉ ያግዛል በሚል ያዘጋጀዉን የክለቦች ምዝገባ አሠራር (Club Licensing) ለመጀመርያ ጊዜ ያስተዋዉቃል። በስብሰባዉ የተገኙ የ209ኙ አባል ፌደሬሽን ተወካዮችም በጉዳዩ ዙሪያ ከተወያዩ በኋላ የፊፋን ሐሳብ በመቀበል በየአህጉራቱ የሚገኙ ኮንፌዴሬሽኖች ይህን አሰራር ተቀብለዉ እንዲተገብሩ ዉሳኔ በማሳለፍ ጉባኤዉን አጠናቀቁ። የአዉሮፓ እግር ኳስ ማህበር (UEFA) አዲሱን አሰራር በመተግበር የመጀመሪያዉ ሲሆን በሌሎች ኮንፌዴሬሽኖችም ይህ የክለቦች ምዝገባ አገልግሎት ላይ ዉሏል።
ሃገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ እግርኳስ ማህበር (CAF) አሠራሩን ለመተግበር ከ2011 ጀምሮ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ይህንን ሂደት ለማቀላጠፍም ራሱን የቻለ ኮሚቴ ሰይሟል። ካፍ የአባል ሃገራቱ ክለቦች ለምዝገባ የሚያበቃቸውን መስፈርት እንዲያሟሉ የተለያዩ ቀነ ገደቦችን በተደጋጋሚ ቢያስቀምጥም በክለቦችና አባል ፌዴሬሽኖች ጥያቄ ጊዜዉን ሲያራዘም ቆይቷል። በመጨረሻም እስከ ታህሳስ 31፣ 2016 ዓ.ም. ድረስ በተዘጋጀዉ የክለቦች ምዝገባ ህግ ላይ የተቀመጡትን መስፈርቶች በማሟላት ከሀገሩ ፌዴሬሽን ፈቃድ (License) ለማግኘት ያልቻለ ክለብ ከ2017 ጀምሮ በሚደረጉ የአፍሪካ ክለብ ዉድድሮች ላይ ተሳታፊ እንደማይሆን በማስታወቁ በ2017ቱ የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ የነበሩ ክለቦች በሙሉ በአሠራሩ ተመዝግበው እውቅና እንዲሰጣቸው አድርጓል። በመቀጠል ደግሞ ካፍ በአባል ሃገራቱ የውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ቡድኖች በሙሉ ክለብ ለመባል የሚያስችላቸውን ዝቅተኛውን መስፈርት በማሟላት ፈቃድ አውጥተው የሚጫወቱበትን አስገዳጅ ስርዓት እንደሚዘረጋ ይጠበቃል።
የዛሬው የሶከር-ህግ አምዳችን ትኩረትም በዚህ የክለቦች ምዝገባ አሰራር ምንነት፣ እንዲሁም በክለቦቻችንና በአጠቃላይ በሃገራችን እግር ኳስ እድገት ላይ የሚኖረውን አስተዋፅኦ ላይ ይሆናል።
የክለቦች ምዝገባ መመሪያ (Club Licensing Regulation) ምንድን ነው?
Lየክለቦች ምዝገባ መመሪያ በዙሪኩ 57ተኛው የፊፋ ጠቅላላ ጉባዔ በመርህ ደረጃ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን የፊፋ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 29, 2007 ዓ.ም. የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ አካል በማድረግ አፅድቆታል፤ ከ2008 ጀምሮም እየተሰራበት ይገኛል። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ለአባል ፌዴሬሽኖቹ ባሰራጨው ፅሁፍ ላይ ይህንን መመሪያ “የተለያዩ የእግር ኳሱ አካላት ስፖርታዊ እሴቶችን፣ የፋይናንስ ግልፀኝነት፣ የክለቦች ንብረትነት እና አስተዳደር፣ የክለብ ውድድሮች ጥንካሬ እና ተቀባይነትን የመሳሰሉ የጋራ መርሆችን የሚያጎለብተው የክለቦች ምዝገባ አሠራርን የሚያስተዳድር ዋና መመሪያ ነው፤” ሲል ይገልፀዋል።
ይህ ጥራዝ (Document) ክለቦች በሀገርአቀፍ እና ዓለምአቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ የሚያስችላቸውን ፈቃድ ለማግኘት ማሟላት የሚገባቸውን ዝቅተኛ መስፈርቶች ያስቀምጣል። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር የፊፋ የክለቦች ምዝገባ መመሪያ (FIFA Club Licensing Regulations) ተብሎ የሚጠራውን ዋንኛ መተዳደሪያ ደንብ ያዘጋጀ ሲሆን የየአህጉራቱ ኮንፌዴሬሽኖች ደግሞ በዚህ ዓለምአቀፍ ዶክመንት ተመርኩዘው የራሳቸውን መመሪያ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ጨምሮ የየሃገራቱ ማህበራት ደግሞ ይህን መመሪያ በሀገርአቀፍ ደረጃ እንዲሰራበት ለማድረግ በሚያመች መልኩ በማሻሻል ተግባራዊ ያደርጉታል።
ዝቅተኛ መስፈርቶቹ ምንድን ናቸው?
ከላይ እንደተገለፀው ክለቦች በሃገርአቀፍ ወይም በኢንተርናሽናል ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ እና እንደ አንድ ተቋም ለመስራት እና ለመንቀሳቀስ ይችሉ ዘንድ እውቅና ያስፈልጋቸዋል። ይህም የሚሰጠው አንድ ክለብ ማሟላት አለበት ተብለው የሚታሰቡ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሳካት ሲችል ነው። ቅድመ ሁኔታዎቹ በ5 ዋና ዋና ዘርፎች ውስጥ የሚጠቃለሉ ሲሆኑ እነዚህም ስፖርታዊ፣ የመሰረተ ልማት፣ የሰው ሃይል እና አስተዳደራዊ፣ ህጋዊ እና የፋይናንስ መስፈርቶች ናቸው።
ክለቦች ከላይ የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ማሟላታቸው በሚገመገምበት ወቅት በሶስት የተከፈሉ A B እና C በሚል የሚጠሩ እርከኖች በጥቅም ላይ ይውላሉ። በA ረድፍ ስር ያሉ ቅድመ ሁኔታዎች የግድ መሟላት ያለባቸው ናቸው። B በአንዳንድ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ሲሆኑ፤ የC ክፍል ውስጥ ያሉ ቅድመ ሁኔታዎች ግን እንዲተገበሩ ግዴታ የሌለባቸው ነገር ግን የሚበረታቱ፤ ወደፊትም ግዴታ ሊሆኑ የሚችሉ “ጥሩ ልምዶች” ናቸው።
1) ስፖርታዊ ቅድመ ሁኔታዎች
አንድ ክለብ ውጤታማነትን አላማው አድርጎ እንደ መነሳቱ በፕሮፌሽናል ተጫዋቾች መዋቀሩ የግድ ይሆናል። በተለይም በሀገራችን ከፕሮፌሽናልነት ጋር ለረጅም አመታት የሚነገሩ የተዛቡ አመለካከቶች አሉ። ኢትዮጵያዊ ተጫዋቾች ከሀገር እስካልወጡ ድረስ ፕሮፌሽናል አይደሉም የሚሉ አካላት እንደዚህ ላሉት አመለካከቶች መነሻ ናቸው። ነገር ግን የፕሮፌሽናልነት ዓለማቀፋዊ ትርጓሜ በተለይም በእግር ኳሱ ዓለም ለስፖርቱ ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ የሚጫወት እና ለአገልግሎቱም ክፍያ የሚያገኝ ነው።
ክለቦች በመዋቅራቸው ስር የታዳጊ እና የሴቶች ቡድንን መያዝ ያስፈልጋቸዋል። ለተጫዋቾቻቸውም ዘመናዊ እና ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎትም መስጠት አለባቸው።
ይህ ክፍል ክለቦች ደረጃቸውን የጠበቁ የወጣቶች አካዳሚ እና የወጣት ተጫዋቾች ማብቂያ ፕሮግራሞች ሊኖራቸው እንደሚገባ ይገልፃል። ይህ ማለት ክለቦች ከ15-21 ዓመት እና ከ10-14 ዓመት ባሉ የእድሜ ክልሎች ውስጥ ቢያንስ አንድ የተሟላ የወጣት ቡድን ይኖራቸዋል ማለት ነው። ክለቦች የወጣት ተጫዋቾቻቸውን እግርኳሳዊ የሆኑ እና ያልሆኑ ትምህርቶች እና የህክምና ወጪዎችን የመሸፈን ግዴታ አለባቸው። ይህ አሠራር ለዋና ቡድኑ የሚመጥኑ ተጫዋቾችን ማፍራት ከማስቻሉ በተጨማሪ ክለቦቹ ያሠለጠኗቸው ከ23 ዓመት በታች ያሉ ተጫዋቾች ባህር ማዶ ወዳሉ ክለቦች የሚዘዋወሩ ከሆነ ከዝውውር ሂሳቡ ድርሻ እንደሚኖራቸው በዚህ መመሪያ ተቀምጧል።
2) መሰረተ ልማት
አንድ ክለብ ውድድር ለማድረግ የሚያስችለው ደረጃውን የጠበቀ ስቴዲየም ባለቤት መሆን አለበት። ስቴዲየሙ ተመልካቾችን እና የሚዲያ አባላትን በበቂ ሁኔታ ማስተናገድ የሚችል አሰራር ሊኖረው ይገባል። ተጫዋቾቹም ልምምድ መስራት የሚያስችላቸው ደረጃውን የጠበቅ የማሰልጠኛ ቦታ ያስፈልጋቸዋል።
የክለብ ስቴዲየም ለተመልካች ምቹ፣ ሳቢ እና ደህንነቱ አስተማማኝ መሆን አለበት። የህክምና ቦታዎች፣ ሱቆች እና ደረጃቸውን የጠበቁ መፀዳጃ ቦታዎችም መሟላት አለባቸው። የስቴዲየሙ መገኛ ለትራንስፖርት አመቺ መሆኑም የግድ ነው። ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ምቹ እና በበቂ ሁኔታ የተደራጀ ስታዲየም ደጋፊዎች የተሟላ እና አዝናኝ የጨዋታ ቀን እንዲያሳልፉ ይረዳል።
አንድ ስቴዲየም በጥራቱ መሰረት በተለያዩ እርከኖች ይከፋላል። ተመልካች የመያዝ አቅሙ ፣ የመገኛው አመቺነት ፣ የመብራት (ባውዛ) ጥራት እና የህክምና መስጫ ቦታዎች መለኪያ መስፈርቶቹ ናቸው።
ወደ ሀገራችን ሁኔታ ስንመጣ ክለቦች በአብዛኛው የተዘረዘሩትን መስፈርቶች በበቂ ሁኔታ ያሟላሉ ወይ ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። ፌደሬሽኑስ ክለቦችን ወደ ውድድር ከማካተቱ በፊት መስፈርቶቹን የመመልከት እና ያለመመልከቱ ነገር ሌላው አሻሚ ጉዳይ ነው። ዘመናዊ እና ህግን መሰረት ያደረገ አሰራር ብቸኛው የስኬት መንገድ ነው። የሚመለከተው አካልም የደንቦቹን ተፈፃሚነት የማረጋገጥ ግዴታ አለበት።
3. የሰው ሐይል እና አስተዳደራዊ መስፈርቶች
በመሠረታዊነት የአንድ በትክክል ፕሮፌሽናል የሆነ ክለብ ፋይናንስ፣ ማርኬቲንግ፣ መዝናኛ፣ ሚድያ፣ ህግ፣ ሰው ሐይል አስተዳደርን የመሳሰሉ ክፍሎቹ ፕሮፌሽናል በሆኑ እና በየዘርፉ ዕውቀት ባላቸው ሰዎች መመራት አለበት። ይህ መስፈርትም ክለቦች በቂ እውቀት ያላቸው ሰራተኞችን ቀጥተኛ በሆነ ቅጥር ወይንም በአማካሪነት ማሰራት እንዳለባቸው ይገልፃል።
4. ህጋዊ መስፈርቶች
የህጋዊ መስፈርቶች አላማ በአንድ ውድድር የሚሳተፉ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ክለቦች በአንድ አካል ንብረትነት፣ አስተዳደር ወይንም ተፅዕኖ ስር እንዳይሆኑ በማድረግ ውድድሩ ከአሠራር ችግሮች የነፃ እንሆን ማስቻል ነው። በዚህ መመሪያ መሰረትም አንድ ግለሰብ፣ ድርጅት ወይንም የመንግስት አካል ከአንድ በላይ ክለቦችን በባለቤትነት አልያም በአስተዳዳሪነት ሊያንቀሳቅስ አይችልም። ወደ ሐገራችን ስንመጣ ደግሞ ለምሳሌ የክልል መንግስታት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ክለቦችን በቀጥተኛ ባለንብረትነት ወይንም አስተዳዳሪነት መምራት እንደማይችሉ ህጉ ያስቀምጣል።
ከዚህ በተጨማሪ ክለቦች ግልፅ የሆነ የንብረትነት እና አስተዳደር አደረጃጀት ሊኖራቸው እንደሚገባ እንዲሁም እግርኳስ ነክ የሆኑ ክሶች በመደበኛ ፍርድ ቤት እንዳይታዩ የሚከለክለውን ጨምሮ የሚሳተፉበት ውድድር ህጎችን የማክበር ግዴታ አለባቸው።
5. የፋይናንስ መስፈርቶች
ይህ ክፍል ክለቦች ግልፅ እና ተቀባይነት ያለው የፋይናንስ አሠራር መዘርጋት ይገባቸዋል ሲል ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀምጣል። የፋይናንስ አስተዳደርን ዘመናዊ በማድረግና ወጪና ገቢን በአግባቡ መዝግቦ በመያዝ ክለቦች የፋይናንስ መረጋጋትን (Financial Stability) ማምጣት ከመቻላቸውም በላይ ገንዘብ ለጋሾቻቸውን እና የክለቡ ባለቤቶችን ከትችት ማዳን ይችላሉ።
በክፍል 2 ፅሁፋችን የክለቦች ምዝገባ እና ፈቃድ አሠጣጥ አሰራር ውስጥ የተካተቱ መስፈርቶች አስፈላጊነትና፤ አሰራሩም ክለቦች፣ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎችን ጨምሮ በእግርኳሱ ላሉ ባለድርሻ አካላት የሚኖረውን ጥቅም በጥልቀት የምንመለከት ይሆናል።