ብሄራዊ ሊግ ፡ አውስኮድ ከምድቡ አንደኛ ሆኖ ወደ ሩብ ፍፃሜው ተቀላቅሏል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ፍፃሜያቸውን አድርገዋል፡፡ በ24 ክለቦች የተጀመረው ውድድርም 16 ቡድኖችን ጥሎ 8 ቡድኖችን አስቀርቷል፡፡

የምድብ 4 ጨዋታዎች ጠዋት 2፡00 ላይ ተደርገዋል፡፡ አስቀድሞ ማለፉን ካረጋገጠው ሆሳእና ከነማ በመቀጠል የተሻለ የማለፍ ተስፋ ይዞ ደቡብ ፖሊስን የገጠመው አውስኮድ 3-2 በማሸነፍ የምድቡ መሪ ሆኖ ወደ ሩብ ፍፃሜ ተቀላቅሏል፡፡ የባህርዳሩ ክለብ ድል ያደረገባቸውን ግቦች ሙሉቀን ታሪኩ(2) እና ዜናው ፈረደ አስቆጥረዋል፡፡ አውስኮድ በተካታታይ ግብ ሳቆጠርበት የቆየ ሲሆን ዛሬ ለመጀመርያ ጊዜ ግቦች አስተናግዷል፡፡

የአውስኮድ ደጋፊዎችም ቡድናቸውን ሳያቋርጡ በማበረታታት የድሬዳዋ ድምቀት መሆናቸውን ቀጥለዋል፡፡ ዛሬም ቡድናቸውን ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያበረታቱበት መንገድ የበርካቶችን አድናቆት አስገኝቶላቸዋል፡፡image-2246b91edb30f1cd10d9c6f80bcba43fcb86564019e0c769f566114492e868d5-V

ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት የአውስኮዱ አሰልጣኝ ደግያደርጋል ይግዛው (ደጉ) ከዚህ በኋላ የሚያቆማቸው እንደሌለ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ በጥሩ ጨዋታ 3-0 መርተን ነበር፡፡ ነገር ግን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተጫዋቾቼ ላይ የነበረው የጉጉት መንፈስ ትኩረት እንድናጣና 2 ግቦች እንዲቆጠርብን አድርጎናል፡፡ ነገር ግን በቡድኔ አቋም ደስተኛ ነኝ፡፡ የደቡብ ፖሊስን ጥንካሬም ሳላደንቅ አላልፍም፡፡ ከዚህ በኋላ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች የሚያቆመን ሃይል አይኖርም›› ብለዋል፡፡

ከዚህም ምድብ አስቀድሞ ማለፉን ያረጋገጠው ሆሳእና ከነማ ባልተጠበቀ ሁኔታ በወሎ ኮምቦልቻ 4-1 ተሸንፏል፡፡ አንደኛ ደረጃ ይዞ የማጠናቀቅ እድሉንም አበላሽቷል፡፡ ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት የሆሳእና ከነማው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ 2ኛ ሆነው ቢያጠናቅቁም ጅማ ከነማን በሩብ ፍፃሜው ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ በዛሬው ጨዋታ በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾቼ በጉዳት እና ቅጣት ምክንያት ከቋሚ አሰላለፉ ውጪ ሆነው ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መጥፎ የመጀመርያ አጋማሽ አሳልፈናል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ለውጥ አድርገን ጨዋታውን ለመለወጥ ጥረት አድርገናል፡፡ በሩብ ፍፃሜው ከጅማ ከነማ ጋር መጫወታችን አስደስቶኛል፡፡ ምክንያቱም ሀላባ ከነማ ከዞናችን የመጣ ቡድን እንደመሆኑ ይፈትነን ነበር፡፡ ጅማ ከነማን አውቃቸዋለሁ፡፡ እንደምናሸንፋቸውም እርግጠኛ ነኝ፡፡ የተጫዋቾች ጉዳት ግን ለሩብ ፍፃሜው ጨዋታ ያሰጋናል፡፡ ወሳኝ አጥቂዎቻችን ለጨዋታው የመድረስ እድላቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ ያም ሆኖ ባሉን ተጫዋቾች ጅማን ለማሸነፍ ዝግጅት እናደርጋለን፡፡ ›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ መድን ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርትን 3-0 ቢያሸንፍም ከምድቡ ከመሰናበት አልዳነም፡፡ ዞኑን በከፍተኛ ነጥብ አጠናቆ የመጣው መድን 8 ነጥብ ሲሰበስብ የከማል አህመድ ውሃ ስፖርት ካለምንም ነጥብ ድሬዳዋን ተሰናብቷል፡፡ ውሃ ስፖርት አንድ ነጥብ ሳያስመዘግብ የተሰናበተ ብቸኛው ቡድን መሆንም ሆኗል፡፡

 

የሩብ ፍፃሜ ተጋጣሚዎች የሚከተሉት ናቸው

ድሬዳዋ ከነማ ከ አዲስ አበባ ከነማ

ጅማ አባ ቡና ከ ፌዴራል ፖሊስ

አውስኮድ ከ ሀላባ ከነማ

ጅማ ከነማ ከ ሆሳእና ከነማ

———–

ፎቶ – ከላይ አበንደኛ ሆኖ ምድቡን ያጠናቀቀው አውስኮድ ከታች ድሬዳዋን ያደመቁት የአውስኮድ ደጋፊዎች

————

የየምድቦቹን የደረጃ ሰንጠረዥ ፣ ውጤቶች ፣ ቀጣይ ጨዋታዎች እና ከፍተኛ ግብ አግቢዎች ደረጃ ለማወቅ ሜኑ ላይ Competitions ላይ ከሚመጡት አማራጮች Ethiopian National League ቀጥሎም Tables ይጫኑ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *