በ17ኛው ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮዽያ ቡና ከኢትዮ ኤሌትሪክ ያደረጉት ጨዋታ ቡና በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ባፕቲስቴ ፋዬ ባስቆጠረው ጎል ሦስት ነጥብ ማግኘቱ የሚታወቅ ነው። ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ኢትዮዽያ ቡናዎች ‹‹በኢትዮ ኤሌትሪክ በኩል ሄኖክ ካሳሁን አምስት ቢጫ እያለበት በእኛ ጨዋታ ላይ የ18ቱ ተጨዋቾች ስም ዝርዝር ውስጥ ገብቷል፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮዽያ እግርኳስ የውድድር መተዳደርያ ደንብ መሰረት ተገቢ አይደለም፡፡›› በማለት ክስ አስይዘው ነበር፡፡
ክሱን ሲመለከት የቆየው የፌዴሬሽኑ የዲሲፒሊን ኮሚቴ ዛሬ ጉዳዮን ከመረመረ በኋላ ሄኖክ ካሳሁን አምስት ቢጫ እያለበት በኢትዮዽያ ቡና ጨዋታ ላይ በቅጣት ምክንያት ማረፍ ሲገባው ይህን ባለማድረጉ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ንፁህ ጎል በፎርፌ ለኢትዮዽያ ቡና እንዲሰጥ ተወስኗል።
በውሳኔው መሰረት በጨዋታው 1-0 በማሸነፍ ሦስት ነጥብ እና 1 ጎል ያገኘው ኢትዮጵያ ቡና ተጨማሪ ሁለት ግቦችን አክሎ የግብ ልዩነቱን ወደ 8 ከፍ በማድረግ 3ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር በሁለት የጎል ልዩነት በመብለጥ 2ኛ ደረጃውን አጠናክሯል፡፡ ላለመውረድ እየታገለ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ በ17 ነጥብ እና 12 የግብ እዳ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ተቀምጧል።