የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ ጠዋት ተጀምረዋል፡፡ ጠዋት በተደረጉ ጨዋታዎች ሆሳእና ከነማ እና ሀላባ ከነማ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ያለፉ ሲሆን በከሰአቱ መርሃ ግብር ጅማ አባ ቡና ፌዴራል ፖሊስን አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍፃሜው አልፏል፡፡
በመደበኛው 90 ደቂቃ ክፍለ ጊዜ 1-1 በተጠናቀቀው ጨዋታ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ጅማ አባ ቡናዎች ናቸው፡፡ በ48ኛው ደቂቃ እዮብ መስፍን ለጅማ አባ ቡና ግብ አስቆጥሮ እስከ ጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ድረስ 1-0 መምራት ችለው ነበር፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ የ1 ደቂቃ እድሜ ሲቀረው አንተነህ ዘውዴ ፌዴራል ፖሊስን አቻ የምታደርግ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው ወደ መለያ ምቶች እንዲያመራ አድርጓል፡፡
አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡት የመለያ ምቶች ጅማ አባ ቡና ሁሉንም ወደ ግብነት ሲቀይሩ ከፌዴራል ፖሊስ በኩል የመጀመርያውን የመለያ ምት የመታው ደሳለኝ ብሩጅ ስቷል፡፡ የመለያ ምቱም በጅማ አባ ቡና 5-4 በአጠቃላይ 6-5 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ የመጨረሻዋን የማሸነፍያ የመለያ ምት ከመረብ ያሳረፈው በጨዋው ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የተስተዋለው አንጋፋው ቢንያም ኃይሌ ‹‹ዋሴ›› ነው፡፡
ከጨዋታው በኋላ የጅማ አባ ቡናው አሰልጣኝ ደረጄ ጨዋታውን ማሸነፍ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ጨዋውን እንደመቆጣጠራችን እና በርካታ የግብ እድሎችን እንደመፍጠራችን ጨዋው በ90 ደቂቃ ማለቅ ነበረበት፡፡ ያም ሆኖ በመለያ ምቶች አሸንፈን ወጥተናል፡፡ ጨዋታው ውጥረት የተሞላበት ከመሆኑ በተጨማሪ የገጠምነውም ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ በቀጣይ ጨዋታ ድክመቶቻችንን አርመን አላማችንን ለማሳካት ትረት እናደርጋለን፡፡ ›› ብለዋል፡፡
ጅማ አባ ቡና በግማሽ ፍፃሜው ድሬዳዋ ከነማን ሲገጥም ይህንን ጨዋታ ካሸነፈ በሌላኛው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ የሚያልፈውን ቡድን ተከትሎ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያለፈ የመጀመርያው የጅማ ክለብ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም በፕሪሚየር ሊጉ የተሳተፈ 44ኛው ክለብ ይሆናል፡፡
የፎቶ መግለጫ – በፎቶው ላይ ልጅ ይዞ የሚታየው የጅማ አባ ቡናው ግብ ጠባቂ ተስፋዬ በቃና ነው፡፡ ይህ በፎቶው ላይ የሚታየው ልጅ ወላጆቹን በመኪና አደጋ ያጣ ህፃን ነው፡፡ ተስፋዬም ይህንን ህፃን ልጅ በሃላፊነት ወስዶ እያሳደገው ይገኛል፡፡ ይህ ህፃን በጅማ አባ ቡና ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች በጣም ተወዳጅ ሲሆን ከአሳዳጊው ጋር አብሮ ድሬዳዋ መጥቷል፡፡ ቡድኑ ጨዋታ በሚደርግበት ሰአትም ከተጠባባቂ ተጫዋቾች ጋር ወንበር ላይ ተቀምጦ የአባቱን እንቅስቃሴ ይከታተላል፡፡ የቡድኑ አባላትም ‹‹ ገዳችን ›› ነው ይሉታል፡፡ የተስፋዬ ሰናይ ተግባር ሊበረታታ እና ሊመሰገን የሚገባው ነው፡፡