በ22ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ መቐለ ከተማ ወላይታ ድቻን 2-0 በመርታት ከመሪው ያለውን ልዩነት ማጥበብ ችሏል።
መቐለ ከተማ ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ደደቢትን ከረታበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በዳንኤል አድሀኖም ምትክ አቼምፖንግ አሞስን የተጠቀመ ሲሆን በተመሳሳይ ከ21ኛው ሳምንት የአንድ ተጨዋች ለውጥ ብቻ ያደረገው ወላይታ ድቻ ፋሲል ከተማን ካሸነፈበት ስብስብ በእሸቱ መና ቦታ ለወንደሰን ቦጋለ የመሰለፍ ዕድል ሰጥቷል።
ከጨዋታው መጀመር በፊት በአመቱ መጀመርያ ላይ ተመስርተው በከተማው ጥሩ የተዳጋዎች ስፖርት መነቃቃት የፈጠሩት ብሩህ ተስፋ ኣካዳሚ እና ፓሽን አካዳሚ ደጋፊዎችን ያዝናና ጨዋታ አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም መቐለ ከተማ ግብ ጠባቂው ፍሊፖ ኦቮኖ ከደደቢት ጋር ባሳየው ብቃት የሳምንቱ ኮኮብ ተብሎ ተሸልሟል።
በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ በመከላከል አደረጃጀት እና በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስዱም በጃኮ አራፋት ላይ ጥገኛ የሆነ እና ተገማች የሆነ የማጥቃት ሂደት በመምረጣቸው ሳቢያ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው በመቐለ ቁጥጥር ውስጥ በቀላሉ ሲገባ ተስተውሏል። ገና ከጅምሩ ኃይል የበዛበት ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል አመለ ሚልክያስ እና ጃኮ አረፋት በግዜ ተቀይረው እንዲወጡ ያስገደደ ነበር። ከ10 ደቂቃ በኋላ የነበረው እንቅስቃሴ በወላይታ ድቻ የሜዳ ክፍል ላይ አመዝኖ የተካሄደ ሲሆን መቐለዎች በርካታ የጎል እድል ቢያገኙም በወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ወንድወሰን ጥረት ግብ ከመሆን ተርፈዋል። በተለይም ኑሁ ፉሴይኒ በረጅሙ መትቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት እና ኑሁ ፉሴይኒ ከቀኝ መስመር ኣሻምቶ አማኑኤል ያመከናት ኳስ መቐለን መሪ ማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። ከባላሜዳዎቹ መቐለዎች በተሻለ ሁኔታ የወላይታ ድቻ የመስመር ተከላካዮች ወደ ፊት በመሄድ በአማካይ መስመር ላይ የቁጥር ብልጫ ቢወስዱም የማጥቃት እንቅስቃሴው ከመሃል ሜዳ አለማለፉ ጥረታቸው ፍሬ ኣልባ እንዲሆን አድርጎታል። መቐለ ከተማዎች በአንፃሩ ኑሁ ፉሴይኒ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር አድልተው ጫና በመፍጠር በ26ኛው ደቂቃ ጋናዊው ኑሁ ፉሴይኒ ያሻገረውን ኳስ ሌላው ጋናዊ አቼምፖንግ አመስ በግንባሩ በመግጨት መቐለ ከተማን ቀዳሚ አድርጓል።
ከመጀመርያው ጎል መቆጠር በኋላ መቐለ ከተማዎች ከዚህ በፊት በሚታወቁበት በረጃጅም ክዋሶች የተመሰረት አጨዋወትን በጥቂቱም ቢሆን በመተው ከኋላ ተመስርተው ለመጫወት ሲሞክሩ ቢታዩም ኳሶቹ ቀጣይነት ሳይኖራቸው ይጨናገፉ ነበር። ሆኖም የወላይታ ድቻው ተከላካይ ውብሸት በትኩረት ማጣት እና በውሳኔ አሰጣጥ ችግር 2 የጎል እድሎች መፍጠር ችለው ነበር። በተለይም በ39ኛው ደቂቃ ላይ ቢስማርክ እና ፉሴይኒ በጥሩ ቅብብል ሄደው ቢስማርክ መትቶ ወደ ውጭ የወጣችው ኳስ የምትጠቀስ ነበረች። ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ በተጎዳው ጃኮ አራፋት ምትክ ታድዮስ ወልዴ ተቀይሮ ከገባ በኋላ በአማካይ ክፍሉ ላይ የቁጥር ብልጫ በመውሰድ መጠነኛ መነቃቃት ቢያሳዩም ፀጋዬ ባልቻ ከረጅም ርቀት ካደረጋት ሙከራ ውጭ ሌላ የጎል እድል መፍጠር አልቻሉም።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ በመቐለ ከተማ ሙሉ ብልጫ የቀጠለ እና ሙከራዎች የታጀበ ነበር። በ47ኛው ደቂቃ ላይ አምበሉ ሚካኤል ደስታ ከመሃል ሜዳ አጋማሽ በረጅሙ የጣለውን ኳስ ፉሴይኒ ማግኘት ሳይችል ወንድወሰን ሊቆጣጠራት ችሏል። በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰውና የመጀመርያውን ጎል አመቻችቶ ያቀበለው ፉሴይኒ በ49ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር በኩል የተላከችለትን ኳስ አክርሮ በመምታት የመቐለን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።
ከጎሉ በኋላም መቐለ ተጨማሪ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ እድሎችን መፍጠር የቻለ ሲሆን ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ በመንቀሳቀስ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ሪትም የገባው ጋቶች ፓኖም ከድቻ የአማካይ እና የተከላካይ መስመር መካከል በመገኘት መልካም አጋጣሚዎችን ሲፈጥር ተስተውሏል። በተለይም ለአማኑኤል አሳልፎለት አጥቂው መትቶ ወንድወሰን ያዳነበት ሙከራ በዚህ መንገድ የተገኘ ነበር። ወላይታ ድቻዎች ቸርነት ጉግሳን ቀይረው ካስገቡ በኋላ ተዳክሞ የነበረው የቡድኑ ማጥቃት እንቅስቃሴ በመጠኑም ቢሆን ተሻሽሎ በ ሁለት አጋጣሚዎች ያለቀላቸው የጎል እድሎች መፍጠር ችለዋል። በተለይም ወጣቱ እዮብ አለማየሁ ሳጥን ውስጥ አክርሮ የመታውና ኦቮኖ ተስፈንጥሮ የመለሰው ለጦና ንቦች አስቆጭ ሙከራ ነበረች። ከዚህ በተጨማሪም እዮብ አለማየሁ የግብ ጠባቂው መውጣትን ተመልክቶ ከርቀት ያደርጋት ሙከራ እና በዛብህ መለዮ በተመሳሳይ ከርቀት የሞከረው ኳስ ተጠቃሾች ነበሩ።
ጨዋታው በመቐለ ከተማ 2-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ መቐለ ነጥቡን ወደ 35 ከፍ በማድረግ ሁለተኛ ደረጃ ላየ መቀመጥ ሲችል ወላይታ ድቻ በ27 ነጥቦች በነበረበት 9ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ዮሃንስ ሳህሌ – መቐለ ከተማ
መጀመርያ እነሱ ኳሱን ተቆጣጥረውት ነበር። ከዛ እኛም ወደ ጫና መፍጠር በመግባት አንድ ጎል ካስቆጠርን በኋላ ወደ ጨዋታው በደምብ ተመልሰናል። ውጤቱ ይገባናል፤ ከሁሉም በላይ ግን ይሄ ክብር ያለው ደጋፊን ማመስገን እፈልጋለው።
ዘነበ ፍስሃ – ወላይታ ድቻ
ጨዋታው ጥሩ ነበር ከሞላ ጎደል። መቐለ ጥሩ ነበሩ፤ ዛሬ ማሸነፍ ይገባቸዋል። እኛ ጥሩ አልነበርንም። ለቀጣይ በተከላካይ መስመር ያለብንን ክፍተት እናርማለን። መቐለዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።