ብሄራዊ ሊጉ እና የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች የዝውውር እንቅስቃሴ

ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና በአጠቃላይ 6 ተጫዋቾችን ከብሄራዊ ሊጉ ክለቦች አስፈርሟል፡፡ ሀብታሙ ጥላሁን ፣ ምስጋናው ወ/ዮሃንስ እና እሸቱ እንድሪስ ከደቡብ ፖሊስ የፈረሙ ሲሆን እያሱ ታምሩ ከሃላባ ከነማ ፣ ቶማስ እሸቱ ከናሽናል ሴሜንት እንዲሁም ሳዲቅ ሼቾ ከሼር ኢትዮጵያ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡

የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዱ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ተጫዋቾቹ ከ3 እስከ 4 አመት ውል የተፈራረሙ ሲሆን ከወቅታዊው ገበያ በእጅጉ ያነሰ ክፍያ ይከፈላቸዋል ብለዋል፡፡

ሀዋሳ ከነማ

ከማጠቃለያ ውድድሩ ተጫዋች ለመመልመል ድሬዳዋ የነበሩት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ 2 ተጫዋቾችን ለማስፈረም ተስማምተዋል፡፡ ሁለቱም ተጫዋቾች ከጅማ ከነማ ሲሆኑ የቡድኑ አምበል መላኩ ወልዴ እና ተከላካዩ ኃይማኖት ወርቁ ለሀዋሳ ከነማ ለመፈረም የተስማሙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከብሄራዊ ሊጉ ክለቦች ለማስፈረም የተስማማው አንድ ግብ ጠባቂ ብቻ ነው፡፡ ፈረሰኞቹ የአርሲ ነገሌውን ግብ ጠባቂ ፍሬዘር ጌታሁን ለማስፈረም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ክለቡ እንዳስታወቀው ፍሬዘር የተስማማው በቃል ደረጃ ብቻ ነው፡፡

 

መከላከያ

ግዙፉ የአርሲ ነገሌ አጥቂ ካርሎስ ዳምጠው ለመከላከያ ለመፈረም ተስማምቷል፡፡ አጥቂው በ2 አመት ውስጥ 500ሺህ ብር (በወር 20ሺህ ብር) ሊከፈለው ተስማምቷል፡፡ ተጫዋቹ ዛሬ ወይም ነገ ለክለቡ ፊርማውን ያኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

መከላከያ ከአርሲ ነገሌው አጥቂ በተጨማሪ 3 ተጫዋቾችን በድሬዳዋው ውድድር ላይ ከተሳተፉ ክለቦች አስፈርሟል፡፡

ለመከላከያ ለመፈረም የተስማማው ካርሎስ ዳምጠው
ለመከላከያ ለመፈረም የተስማማው ካርሎስ ዳምጠው

 

ወላይታ ድቻ

ወሳኝ ተጫዋቾቹን በሌሎች ክለቦች የተነጠቀው ወላይታ ድቻ 2 ተጫዋቾችን ለማስፈረም ተስማምቷል፡፡ የሶዶው ክለብ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች አማካዩ አማኑኤል ተሾመ ከአዲስ አበባ ከነማ እና ተከላካዩ ቶማስ ስምረት ከሱሉልታ ከነማ ናቸው፡፡

ደደቢት

እንደቀድሞው በትልልቅ ስሞች ዝውውር ላይ ተሳታፊ ያልሆነው ደደቢት ከብሄራዊ ሊጉ ውድድር 6 ተጫዋቾችን ማስፈረሙ ተነግሯል፡፡ የወልዋሎው አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ቅጥር እና የተጠናቀቁት ዝውውሮች ክለቡ ነገ በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዳሽን ቢራ

ዳሽን አውስዱን ተከላካይ ያሬድ ባዬ እና የሼር ኢትዮጵያው ኪዳኔ ተስፋዬ ለማስፈረም መስማማማቱን ከክለቡ ህዝብ ግንኙነት አንተነህ መሃሪ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ዳሽን ቢራ የድሬዳዋ ከነማው ተጫዋች ይሁን እንደሻውን ለማስፈም በቃል ደረጃ ከስምምነት ላይ ቢደርስም ክለቡ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ካለፈ በድሬዳዋ ይቆያል ተብሏል፡፡ ክለቡ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ዛሬ በደብረዘይት የሚጀምር ሲሆን ሁለቱ ተጫዋቾች እንዲገኙም ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ዳሽን ቢራ 2 የውጭ ዜጋ ተጫዋቾችን ለሙከራ መጥራቱን ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ንግድ ባንክ

በተጫዋቾች ዝውውር ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኘው ንግድ ባንኮች ለማስፈረም ያሰቡትን ተጫዋች ማግኘት አልቻሉም፡፡ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም 2 ተጫዋቾችን ቢመለከቱም በክለባቸው ቀሪ ኮንትራት ያላቸው በመሆኑ ዝውውሩ ሳይሳካ መቅረቱን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

 

ሙገር ሲሚንቶ

የሙገር ሲሚንቶው አሰልጣኝ ግርማ ኃ/ዮሃንስ ከብሄራዊ ሊጉ የሚፈልጋቸው ተጫዋቾችን ተመልክተዋል፡፡ ከከልቡ ባገኘነው መረጃ መሰረት በመጪዎቹ ቀናት ከተጫዋቾቹ ጋር ድርድር ይጀምራሉ፡፡

ሙገር ሲሚንቶ በቀጣዩ የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊግ እንዲቀጥል ምንም አይነት ደብዳቤ እንዳልደረሳቸውም ክለቡ አስታውቋል፡፡


 

*ምንጭ ካልተጠቀሰ በቀር በዚህ ድረ-ገፅ ላይ የሚወጡ ፅሁፎች የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ፅሁፉን ሲጠቀሙ ምንጭ በመጥቀስ ለስራችን ዋጋ ይስጡ


 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *