ሉሲዎቹ ከአልጄሪያ ጨዋታ መልስ ዛሬ ልምምዳቸውን ሰርተዋል

ለ2018 የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ የመጨረሻ የማጣሪያ ዙር የመጀመርያ ጨዋታው አልጀርስ ላይ በአልጄሪያ 3-1 በሆነ ውጤት ሽንፈት አስተናግዶ የተመለሰው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከ15 ሰአት በረራ በኋላ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብቷል።

በመጪው እሁድ የመልሱን ጨዋታ የሚያደርጉት ሉሲዎቹ ዛሬ 10:00 ላይ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ በኢትዮዽያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ በዝናባማ አየር ልምምዳቸውን ሰርተዋል። በጉዳት ምክንያት ከመጀመርያው ጨዋታ ውጪ የነበረችው ተከላካይዋ መስከረም ካንኮም ወደ ሙሉ ጤንነቷ በመመለስ ልምምድ ጀምራለች። በተያያዘ ዜና የአልጄሪያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከሰአት 33 የልዑካን ቡድን በመያዝ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን ማረፊያቸውን በካፒታል ሆቴል አድርገው ነገ የመጨረሻ ልምምዳቸውን በአአ ስታድየም የሚሰሩ ይሆናል።


አዲሱ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ወደ ሩሲያ አለም ዋንጫ ከማቅናታቸው በፊት ማምሻውን ባረፉበት ሆቴል በመገኝት  የማበረታቻ ንግግር አድርገውላቸዋል።

የጨዋታው ዳኞች ከቱኒዚያ ሁለት ከግብፅ፣ ኮሚሽነር ከሱዳን የሆኑበት ይህ ጨዋታ የፊታችን እሁድ 10:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የሚካሄድ ይሆናል።