ፕሪምየር ሊግ | የ29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

29ኛ ሳምንት ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ስድስት ጨዋታዎች ይስተናገዱበታል። እነዚህን ጨዋታዎችም እንደተለመደው በቅድመ ዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል።

በደረጃ ሰንጠረዡ አናት በእኩል ነጥብ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባ ጅፋር ከሜዳቸው ውጪ በመውጣት ሁለት ጨዋታዎች በቀረው የሻምፒዮንነት ጉዟቸውን የሚወስኑ ጨዋታዎች ያደርጋሉ

አዳማ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በተከታታይ ሳምንታት ባስመዘገበው ውጤት ከፉክክሩ ውጪ የሆነው አዳማ ከተማ ሜዳው ላይ ያለውን ጠንካራ ሪከርድ ለማስቀጠል ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በመሪነቱ ለመቀጠል በኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ መሪነት አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ ይገናኛሉ። የአዳማ በውጤት መንሸራተት የጨዋታውን ተጠባቂነት ቢቀንስሰውም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሚቸገርባቸው ሜዳዎች መካከል አንዱ በመሆኑ ጠንካራ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል። የመጨረሻ ሳምንታት ላይ ብርታቱን በማሳየት የሚታወቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በደደቢት እና ወላይታ ድቻ ላይ ሰባት ግቦችን በማስቆጠር ምንም ግብ ሳያስተናግድ ለዚህ ጨዋታ ሲደርስ አዳማ ከተማ ደግሞ ከአርባምንጭ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ ከተገናኘባቸው ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ አሳክቶ ነው ለዛሬው ጨዋታ የደረሰው።

አዳማ ከተማ ከጉዳት እና ቅጣት ዜናዎች ነፃ ሆኖ ለዚህ ጨዋታ ሲደርስ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ሳላዲን ሰይድ ፣ ሪቻርድ አፒያ እና አማራ ማሌ አሁንም ጉዳት ላይ ይገኛሉ።

የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ግንኙነት ለአዳማ ከተማ እና ከንዓን ማርክነህ የሚረሱ አይደሉም። እንደቡድን በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ብልጫን መውሰድ ችለው የነበሩት አዳማዎች በዛ ጨዋታ ላይ ከከንዓንን ልዩ ብቃት በሚገባ የተጠቀሙበት ነበር። በጨዋታው የነበራቸው በራስ መተማመን እና በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ፍጥነት በተሞላበት መልኩ ይሰነዝሩ የነበሩት ጥቃት ለዛሬው ጨዋታ ግብአት እንደሚሆናቸው ይታሰባል። ከንዓን ማርክነህ ያኔ ካልነበረው ናትናኤል ዘለቀ ጋር እንዲሁም በረከት ደስታ እና ሱራፌል ዳኛቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚገናኙባቸው ጊዜያትም ወሳኝነታቸው ከፍ ያለ ነው።

አሁንም በየጨዋታው ግብ የሚያስቆጥርለት ሁነኛ አጥቂ ያሌለው ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ቡድን ግቦችን ከሁሉም አማራጮች ለማግኘት የሚያደርገው ርብርብ ስኬታማ እያደረገው ይገኛል። ቡድኑ በኋላ መስመር ተሰላፊዎቹ አማካይነት የቆሙ ኳሶችን ወደ ውጤት የሚቀይርበት መንገድ ዛሬም አዳማን እንደሚፈትኑ መናገር ይቻላል። የአማካይ ክፍሉን እርጋታ ካላበሳው ናትናኤል ዘለቀ ድንቅ ብቃት በተጨማሪ የበሀይሉ አሰፋ እና ኦዝቫልዶ ታቫሬዝ ፈጠን እንዲሁም ከቡድኑ አጠቃላይ ጉልበት ጋር አብሮ የሚሄድ ጥቃት ከአዳማ ጠንካራ ተከላካይ መስመር ጋር ሲገናኝ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለውም ተጠባቂ ነጥብ ነው።

ወላይታ ድቻ ከ ጅማ አባ ጅፋር

በፌደራል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው መሪነት የሚደረገው ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች እጅግ አሳኝ ነው። በውድድር አመቱ በሊጉም ሆነ በአህጉራዊ ውድድር ከፍተኛ መነቃቃት አሳይቶ የነበረው ወላይታ ድቻ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከገጠመው ከባድ ሽንፈት በኋላ የወራጅ ቀጠናውን ተቀላቅሏል። ዛሬ ደግሞ በሌላው የሊጉ መሪ ተመሳሳይ ሽንፈት ከገጠመው የቡድኑ በቀጣይ አመት በሊጉ የመቆየት ጉዳይ አጠራጣሪ ይሆናል። ከጅማ ወጪ ሶስት ጨዋታዎችን አድርጎ ሙሉ ነጥቦችን የሰበሰበው አባ ጅፋር ደግሞ አራተኛ ተከታታይ ድሉን አሳክቶ እና በርካታ ግቦችን አስቆጥሮ ሳምንት ብዙ ባገባ በሚለው ህግ የተነጠቀውን መሪነት መልሶ ለማግኘት ይፋለማል። ውጤቱ ለሁለቱም ቡድኖች ካለው አስፈላጊነት አንፃርም ጨዋታው እልህ አስጨራሽ ትግል እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

ወላይታ ድቻ ተስፉ ኤልያስ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሲሆንበት ውብሸት አለማየሁ ደግሞ በተቃራኒው ከጉዳት ይመለሳል። ቢኒያም ሲራጅ እና እንዳለ ደባልቄ በጅማ አባ ጅፋር በኩል ለጨዋታው የማይደርሱ ሲሆን ወሳኙ አማካይ አሚኑ ነስሩም በጉዳት ዝርዝር ውስጥ ተካቷል።

ወላይታ ድቻ በውጤት ብቻ ሳይሆን በተጨዋቾች የግል ብቃት እንዲሁም በነበረው ጠናካራ እና የተናበበ የቡድን ስራ ጭምር ነው የወረደው። ላለፉት ሳምንታት የታየው የቡድኑ እጅግ የሳሳ የማጥቃት አቅም ከጅማ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ጋር ሲገናኝ ደግሞ መፈተኑ የማይቀር ነው። ድቻ በወልዋሎ እና ጊዮርጊስ ላይ የፈጠራቸው የግብ ዕድሎች አናሳነት ከአማካይ ክፍሉ የማጥቃት ፍጥነት መቀነስ ጋር አብረው የሚሄዱ ናቸው። ዛሬም ቡድኑ ከበዛብህ መለዮ እና አብዱልሰመድ አሊ የአማካይ ክፍል ጥምረት ያጣቸውን የመጨረሻ ኳሶች የሚጠብቅ ሲሆን የመስመር አማካዮቹም ለፊት አጥቂው ጃኮ አራፋት ክፍተቶችን ከመፍጠር ባለፈ እራሳቸውም የማስቆጠር ሀላፊነት እንደሚኖርባቸው ይታመናል።

የአሚኑ ነስሩ መጎዳት ለጅማ አባ ጅፋር ትልቅ ፈተና ነው። ተጨዋቹ ከይሁን እንዳሻው ጋር የፈጠርው የአማካይ ክፍል ጥምረት በወጥነቱ በሊጉ ተወዳዳሪ ያለው አይደለም። አሚኑ ነስሩ ደግሞ ለተከላካይ መስመሩ ቀርቦ በመጫወት ተጋጣሚ መሀል ለመሀብ ለመሰንዘር የሚሞክራቸውን ጥቃቶች በማቋረጥ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው። አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ይህን ወሳኝ ተጨዋቻቸው አለመኖር የሚፈጥረውን ክፍተት በምን መልኩ ይሸፍኑታል የሚለው ነጥብ ተጠባቂ ነው። ከዚህ ውጪ በማጥቃቱ በኩል የሌሎቹ አማካዮች አሮን አሞሀ እና ዮናስ ገረመው የመስመር እንቅስቃሴ ለወላይታ ድቻ ከባድ ፈተና የመሆን አቅም ሲኖረው አውራሪዎቹ ኦኪኪ አፎላቢ እና ተመስገን ገ/ኪዳን የተናበበ ጥቃትም ለጅማ አባጅፋር ጥንካሬን የሚያላብስ ነው።

ጎንደር እና መቐለ ላይ የሚደረጉት ሌሎች ሁለት ጨዋታዎች በ27ኛው ሳምንት በጣሏቸው ነጥቦች ከፉክክሩ ራቅ ያሉት ክለቦችን ዳግም ዕድል የመስጠት አቅም ይኖራቸዋል።

ፋሲል ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና

ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋራው ኢትዮጵያ ቡና በዛ ጨዋታ ላይ የጣላቸው ሁለት ነጥቦች ዋጋ በምንም የሚተኩ አይደሉም። ከበላዩ ያሉት ሁለቱ ክለቦች ከሜዳቸው ውጪ ከበድ ያሉ ጨዋታዎችን እንደማድረጋቸውም ቡና ከድሬ ሙሉ ነጥብ ቢያገኝ ኖሮ ምንም ጫና ከሌለበት ፋሲል ከተማ ጋር መገናኘቱ ተጠቃሚ ያደርገው ነበር። በመጀመሪያው ዙር መጨረሻ እና በሁለተኛው ዙር መግቢያ ላይ የሰበሰባቸው ነጥቦች ረድተውት በሊጉ መቆየቱን በጊዜ ያረጋገጠው ፋሲል ከተማ ሲዳማን ከሁለት ሳምንት በፊት ጎንደር ላይ ከረታበት ጨዋታ ውጪ በስድስት ጨዋታዎች ግብ ካለማስቆጠር በኤሌልትሪክ 4-1 እስከመሸነፍ ድረስ የዘለቀ ደካማ የውድድር ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። ኢንተናሽናል ዳኛ ቴውድሮስ ምትኩ በሚመራው በዚህ ጨዋታ ላይም ቡድኑ የተለየ መነሳሳትን ይዞ ወደ ሜዳ ለመግባት እንደሚቸገር መገመት አይከብድም። ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ በርካታ ግቦችን ለማግኘት ያለመ እና ሙሉ ለሙሉ ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አቀራረብ ይዞ እንደሚገባ ይጠበቃል።

የፋሲል ከተማው አማካይ ኤፍኤም አለሙ እና አይናለም ኃይለ በጉዳት አምሳሉ ጥላሁን ደግሞ በኤሌክትሪኩ ጨዋታ ከተጠባባቂ ወንበር ላይ በተመለከተው ቀይ ካርድ በቅጣት የማይሰለፉ ሲሆን በአንፃሩ ያሬድ ባየህ ወደ ሜዳ ይመለሳል፡፡ የኢትዮጵያ ቡናዎቹ ቶማስ ስምረቱ እና አቡበከር ነስሩ አሁንም ከጉዳት አልተመለሱም።

መቐለ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ከሲዳማ በሽንፈት የተመለሰው መቐለ ከተማ በሂሳብ ስሌት ከዋንጫ ፉክክሩ ባይወጣም በሌሎቹ ቡድኖች ውጤት ላይ የተመሰረተው የሻምፒዮንነት ተስፋው የተመናመነ ሆኗል። ከዚህም ባሻገር ውጤቱን አጥብቆ ከሚፈልገው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የሚገናኝ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ አስገራሚ ግስጋሴ ያሳየበት የመጀመሪያ አመት የሊግ ጉዞው በዋንጫ ላይታጀብ የሚችልበትን ዕድል ይበልጥ ያጠበዋል። በኢትዮጵያ ዋንጫ ከመቐለ ጋር ተመጣጣኝ ፉክክር አድርጎ በመለያ ምቶች ማሸነፍ የቻለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ከዚህ ጨዋታ አንድም ነጥብ ቢሆን ይዞ ለመመለስ የሚታገል ይሆናል። የወላይታ ድቻ ከባድ ጨዋታ እንዲሁም የድሬዳዋ እና አርባምንጭ እርስ በእርስ መገናኘት ደግሞ ኤሌክትሪክ ለዚህ ጨዋታ የሚኖረውን ትኩረት ይበልጥ ከፍ የሚያደርጉ አጋጣሚዎች ናቸው።

በጨዋታው መቐለ ከተማ ፍቃዱ ደነቀ እና ቢስማርክ ኦፖንግን በጉዳት የሚያጣ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ግን ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ሆኖ ለጨዋታው ይቀርባል።

ቀሪዎቹ ሁለት የዛሬ ጨዋታዎች በወራጅ ቀጠናው ያለውን ፉክክር የመለየት ዕድል ይኖራቸዋል። ከሌሎቹ ጨዋታዎች ውጤት ጋር ተዳምሮ ምናልባት ዛሬ ላላኛውን ወራጅ ቡድን የምንለይበት ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል።

ሀዋሳ ከተማ ከወልዋሎ ዓ.ዩ

በዝግ ስታድየም እንደሚደረግ የተነገረው ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች ቀጣይ እጣ ፈንታ ውሳኝ ትርጉም ይኖረዋል። በአንድ ነጥብ ልዩነት 10 እና 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች በኢተናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ የሚመራው ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉ በሊጉ የመቆየታቸውን ነገር የሚያረጋግጡ ሲሆን አቻ እና ሽንፈት ግን የመጨረሻውን ሳምንት እንዲጠብቁ ያደርጋቸዋል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ቡና ሽንፈቶችን ካስተናገደ በኃላ ከአርባምንጭ ነጥብ የተጋራው ሀዋሳ ከሊጉ ወገብ በጣሙን ሳይንሸራተት ለዚህ ቢደርስም ዳካማ የውድድር አመቱ ግን ከስጋት ነፃ አላደረገውም። በመጨረሻ ሳምንታት መሻሻልን ያሳየው ወልዋሎ ዓ.ዩ ደግሞ ቀደም ብሎ ከገባበት ያለመውረድ ጣጣ ለመውጣት ከመጨረሻው የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በፊት ሀዋሳ ላይ ውጤት ማግኘት አስፈላጊው ነው።

የመኖሪያ ፍቃዱ ተጠናቆ ወደ ሀገሩ ያቀናው ሰይላ መሀመድ እና ከአሰልጣኝ ቡድን አባላት ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ወደ አሜሪካ ያለክለቡ ፍቃዱ ያቀናው ሙሉአለም ረጋሳ ክለቡን አያገለግሉም። ከዚህ ውጪ አዲስአለም ተስፋዬ በጉዳት የማይኖር ሲሆን ደስታ ዮሀንስ ከጉዳት ሱሆሆ ሜንሳ ደግሞ ከቅጣት ይመለሳሉ፡፡ አሳሪ አልመሀዲ እና በረከት አማረ በቅጣት የማይጠቀመው ወልዋሎ ዓ.ዩ ወሳኙ የመስመር አጥቂው ፕሪንስ ሰርቨኒሆም የውል ጊዜው በመጠናቀቁ ምክንያት ክለቡን ማገልገል አይችልም።

ድሬዳዋ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ

በወራጅ ቀጠናው ውስጥ እልህ አስጨራሽ ትግል እያደረጉ የቆዩት ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ ድሬዳዋ ላይ በኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብትሀን እየተመሩ ከባዱን ፍልሚያ ያደርጋሉ። ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው ድሬዳዋ ከተማ አሁንም የማጥቃት አቅሙ ደካማ ቢሆንም ሜዳው ላይ ያሳካቸው የ 1-0 ድሎች ለዛሬው ጨዋታ ተስፋን ይሰጡታል። በተቃሪኒው ደግሞ ከሜዳው ውጪ እጅግ ደካማ ሪከርድ ያለው አርባምንጭ ከተማ እስትንፋሱን ለማቆየት የብቃቱ ጫፍ ላይ መገኘት እና ግቦችን ማስቆጠር የግድ ይለዋል። 29 ነጥብ ላይ የቀረው አርባምንጭ ከተማ ዛሬም ሽንፈት የሚገጥመው ከሆነ እና ሌሎቹ የታችኛው ሰንጠረዥ ክለቦች ድል ከቀናቸው ወልዲያን ተከትሎ ሊጉን ሊሰናበት የሚችልበት አጋጥሚ ይፈጠራል።

ድሬዳዋ ከተማ ሙሉ የቡድን ስብስቡን ይዞ ጨዋታውን የሚያስተናግድ ሲሆን አርባምንጭ ከተማ ደግሞ ውሉ ተጠናቆ ወደ ሀገሩ ጋና ያመራውን የመሀል ተከላካዩ አሌክስ አሙዙን የማያገኝ ይሆናል፡፡