የመጨረሻ ሳምንቱ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚያስተናግዳቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ክለቦችን ወደ ከፍተኛ ሊግ ይሸኛል። ወልዲያን ተከትለው ከሀገሪቱ ዋና ሊግ ለመውረድ የተቃረቡት አራት ክለቦች የመጡበትን መንገድ እና ዕጣ ፈንታቸውን ለየብቻ ተመልክተናል።
በሊጉ ተሳታፊ ከሆኑ 16 ክለቦች መካከል ግማሹ በመውረድ ስጋት ሆነው የቆዩ ሲሆን በቅርብ ሳምንታት የተወሰኑት ለከርሞው በሊጉ እንደሚቆዩ አረጋግጠዋል። ከ7ኛ እስከ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ደደቢት፣ ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ሲሆኑ የነጥብ ስብስባቸው ሙሉ ለሙሉ ነፃ አድርጓቸዋል። በመቀጠል 10ኛ እና 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት መከላከያ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ ደግሞ 35 ነጥብ ላይ ቢገኙም የኢትዮ ኤሌክትሪክ የግብ ዕዳ መብዛት ከመውረድ እንደሚተርፉ ዋስትና ሆኗቸዋል። ከዚህ በታች የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማ ፣ ወላይታ ድቻ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ ከተማ ደግሞ ዛሬ ከ9፡00 ጀምሮ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች መጨረሻቸው ይታወቃል።
ድሬዳዋ ከተማ
15 ተጨዋቾችን በማስፈረም ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጋር የያዝነውን የውድድር አመት የጀመረው ድሬዳዋ ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን በመርታት አመቱን ቢጀምርም ቀጣዩ ድሉ የመጣው የመጀመሪይው ዙር ሲገባደድ ነበር። በመሀል የደረሱበት ሽንፈቶች ተደማምረውም ከወልዲያ ብቻ የተሻለ ብዙ ጨዋታዎችን የማሸነፍ ቁጥር ያለው ድሬን የወራጅ ቀጠናው ቋሚ ተፋላሚ አድርገውታል። ክለቡ በመቀጠል አሰልጣኝ ስምኦን አባይን በኃላፊነት ከሾመ በኋላ የአጨዋወት ለውጥ ለማድረግ ጊዜ ቢወስድበትም በሁለተኛው ዙር የተሻለ ጊዜን አሳልፏል። በተለይም ወልዲያ ፣ ወላይታ ድቻ ፣ መከላከያ እና መቐለ ከተማን ሜዳው ላይ ያስተናገደባቸውን ጨዋታዎች ድል በማድረግ በሜዳው ያለውን ጥንካሬ ማሳየቱ ብዙዎች በቶሎ ከስጋት እንደሚላቀቅ እንዲገምቱ አድርጎ ነበር። ነገር ግን ከ26ኛው ስምንት በኋላ አንድ ሽንፈት እና ሶስት የአቻ ውጤቶችን አስመዝግቦ በ32 ነጥቦች እና በሶስት የግብ ዕዳ 12ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ሆኗል።
ከሜዳው ውጪ አንድም ጊዜ አሸንፎ የማያውቀው ድሬዳዋ ከተማ ዛሬ ወደ ዓዲግራት አምርቶ በአንድ ደረጃ ከሚበልጠው ወልዋሎ ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘትን ይፈልጋል። ይህን ማድረግ ከቻለ በ35 ነጥብ ሊጉን ሊጨርሱ ከሚችሉ ቡድኖች መካከል የተሻለ የግብ ልዩነት ሊኖረው የሚችልበት ዕድል ስለሚኖር የመትረፍ አጋጣሚው ሰፊ ይሆናል። አቻ መውጣት እና ሽንፈት ግን ከበታቹ ያሉት ቡድኖችን ውጤት ተከትሎ ብርቱካናማዎቹን ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚሸኝ ይሆናል።
ድሬዳዋ ከተማ የሊጉ ህልውናውን የሚወስንበትን ይህን ጨዋታ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ሆኖ ያከናውናል። ወሳኙን የወልዋሎ ዓ.ዩ እና ድሬዳዋ ከተማን ጨዋታ ፌደራል ዳኛ ወልዴ ንዳው በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።
ወላይታ ድቻ
የወላይታ ድቻ የውድድር አመት ለሶስት የተከፈለ ነበር። ከቡድኑ የፕሪምየር ሊግ ታሪክ ጋር አብረው ከዘለቁት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጋር ሆኖ ከመጀመሪያዎቹ ስምንት ሳምንታት መካከል አምስት ሽንፈት ገጥሞት የሊጉ ግርጌ ላይ እስከመቀመጥ የደረሰበት ጊዜ የመጀመሪያው ሆኖ ይታወሳል። በመቀጠል ቡድኑ አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰህን ቀጥሮ በሜዳው የማይቀመስ ከሜዳው ውጪ ደግሞ የሚቸገር ቡድን ሆኖ መታየት ጀመረ። በነዚህ ጊዜያት ሜዳው ላይ 8 ግቦችን አስቆጥሮ እና አንድ ጊዜ ብቻ መረቡ ተደፍሮ አምስት ጨዋታዎችን ድል በማድረግ በእጅጉ አንሰራራ። ይህ ውጤት ቡድኑ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ካደረገው ጉዞ ጋር ተዳምሮ ወላይታ ድቻን በከፍታ ላይ አስቀምጦት ነበር። የኋላ ኋላ ግን ወላይታ ድቻ መጀመሪያ ገጥሞት ወደነበረው ውጤት ማጣት እንዲመለስ ግድ ሆኗል። ከ22ኛው ሳምንት በኃላም ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎችን ጨምሮ በአስር ጨዋታዎች ከአቻ ውጤቶች የተገኙ አምስት ነጥቦችን ሰብስቦ በሌሎቹ በሙሉ በመሸነፍ ዳግም በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ተገኝቷል።
ወላይታ ድቻ 32 ነጥቦችን ይዞ 13ኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠው። ክለቡ ዛሬ ከ83 ቀናት በፊት የመጨረሻ ድሉን ባገኘበት ሰበታ ስታድየም ከወልዲያ የሚያደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ በግብ ልዩነት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ተሽሎ በሊጉ የመቆየት ዕድል ሲሰጠው አቻ መውጣት እና መሸነፍ ግን የሚያድነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ ከተማ ሽንፈት ከገጠማቸው ብቻ ይሆናል።
ወላይታ ድቻ ዛሬ ከወልዲያ ጋር ሰበታ ላይ በኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው መሪነት በሚያደርገው ጨዋታ ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ቆይቶ ቢመለስም ዳግም ጉዳት የገጠመው ፀጋዬ ብርሀኑ እና የመስመር ተከላካዩ ተስፍ ኤልያስ በጉዳት አያሰልፍም።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ
በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን አሳክቶ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ብዙ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ከቅርብ ተፎካካሪዎቹ የተሻለ ቢሆንም ዘንድሮም እንዳለፉት አመታት የወራጅ ቀጣናው ደንበኛ መሆኑ ግን አልቀረም። በአሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩ እና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስር ሆኖ 13 ሽንፈቶችን ያስተናገደበት ይህ የውድድር አመት የጎል ጎተራ ሆኖ የከረመበትም ነበር። ለእንደ ካሉሻ አልሀሰን አይነት ተጨዋቾቹ ምስጋና ይግባና ቡድኑ 30 ግቦችን በማስቆጠር በአምስት ክለቦች ብቻ ብዙ በማግባት ቢበለጥም ያስተናገዳቸው 46 ግቦች ግን መውረዱን ካረጋገጠው ወልዲያ ሁሉ በታች ያደርገዋል። በወልዋሎ ዓ.ዩ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ደደቢት እና መከላከያ የደረሱበት የ3-1 ሽንፈቶች ከዚህም ሲያልፍ በጅማ አባ ጅፋር 4-0 በአዳማ ከተማ ደግሞ 6-1 የተረታባቸው ጨዋታዎች 16 የግብ ዕዳ ይዞ ዘንድሮ የመትረፉን ነገር ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ወደ 33 ነጥብ ከፍ ብሎ የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን የሚችልበትን አጋጣሚም ሳምንት መቐለ ላይ በ89ኛ ደቂቃዋ የጋቶች ፓኖም ጎል ተነጥቆ ከሊጉ የ1990 ጅማሮ በኋላ ወደ ታች የመውረድ ብሎም የመፍረስ አደጋን ከፊቱ እንዲጋፈጥ ግድ ሆኗል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዛሬ አዳማ ላይ ሲዳማ ቡናን የሚገጥምበትን ጨዋታ በድል ማጠናቀቅ ብቸኛው የሚተርፍበት አማራጭ ነው። ነገር ግን ይህ ሁኔታ ዕውን እንዲሆን ወላይታ ድቻ ወይንም ድሬዳዋ ከተማ መሸነፍ ይኖርባቸዋል።
ፌደራል ዳኛ ሃይለየሱስ ባዘዘው በሚመራው የኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጨረሻ ጨዋታ ውሉ የተጠናቀቀው ሰይዱ አብዱልፈታ ብቻ ከቡድኑ ጋር የማይኖር ይሆናል።
አርባምንጭ ከተማ
አርባምንጭ በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ፣ በአሰልጣኝ እዮብ ማለ በመጨረሻም በአሰልጣኝ ማትዮስ ለማ ስር የውድድር አመቱን አሳልፏል። ከ6ኛው ሳምንት ጀምሮ የገጠመው ተከታታይ የአምስት ጨዋታዎች ሽንፈት የቡድኑ አስከፊ ጊዜ ሆኖ ሳለ በቀሪዎቹ የውድድር ጊዜያትም ወጣ ገባ የሆነ አቋም ሲያሳይ ቆይቷል። በሁለተኛው የውድድር አጋማሽ እስከ 24ኛው ሳምንት ያሳየው ባህሪ ግን በአስገራሚነቱ ይነሳል። በዚህ ወቅት ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ ሜዳው ላይ ያስተናገዳቸውን አራት ቡድኖች ሲያሸንፍ 11 ግቦችን ከመረብ በማገናኘት ጭምር ነበር። ነገር ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ ከሜዳው ወጥቶ በአምስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ሲያሳካ ግብ ማስቆጠር ግን አንዴም አልሆነለትም። ባለፉት አራት ሳምንታት ደግሞ የአቻ ውጤትን የሙጥኝ ብሎ ከ15ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ሳይችል በከፍተኛ የመውረድ ስጋት ውስጥ ሆኖ ለ30ኛው ሳምንት ደርሷል።
30 ነጥቦች የያዘው አርባምንጭ ከተማ ዛሬ ፋሲል ከተማን ማሸነፍ በሊጉ ለመቆየት ያለው ብቸኛው አማራጩ ነው። የክለቡን ዕድል ጠባብ ያደረገው ግን ከማሸነፍ ባለፈ የድሬዳዋ ከተማ ፣ ወላይታ ድቻ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ሽንፈትም የሚጠብቅ መሆኑ ነው።
አርባምንጭ ውሉ ያበቃውን ጋናዊ የመሀል ተከላካይ አሌክስ አሙዙን የማይጠቀም ሲሆን ፋሲል ከተማን የሚያስተናግድበትን የ30ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታ ፌደራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ ይመራዋል።