ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ መንታ መንገድ ላይ ቆሟል

09፡00 ላይ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም የጀመረው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በኤሌክትሪክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሆኖም የዓዲግራቱ ጨዋታ በዝናብ ምክንያት በመቋረጡ አንደኛው ወራጅ ቡድን ሳይታወቅ ቀርቷል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ መቐለ ላይ ከገጠመው የ1-0 ሽንፈት ሲሴይ ሀሰንን እና ዘካርያስ ቱጂን በተስፋዬ መላኩ እና ስንታየው ዋለጬ ተክቶ ወደ ሜዳ ገብቷል። በሲዳማ ቡና በኩልም ሁለት ለወጦች ሲደረጉ መከላከያን 1-0 ካሸነፈው ቡድን አንፃር ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ በፍቅሩ ወዴሳ ሲቀየር አብይ በየነ ደግሞ በትርታዬ ደመቀ ምትክ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ተካቷል።

ጨዋታውን ጫን ብለው የጀመሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የነበራቸው ቢሆንም በሲዳማ ሜዳ ላይ እምብዛም መረጋጋት አልቻሉም። ኃይሌ እሸቱ ከሳጥን ውጪ ያደረጋት ኢላማዋን ያልጠበቀች የመጀመሪያ ሙከራም የታየችው 9ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ቀስ በቀስ የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ መቆጣጠር የጀመሩት ሲዳማዎች በተለመደው የመስመር ጥቃታቸው አጋጣሚዎችን መፍጠር ጀምረዋል። ቡድኑ ምንም እንኳን መሀል ለመሀል የሚሰነዝራቸው ጥቃቶች አቅም ቢያጡም አዲስ ግደይ በተሰለፈበት የግራ መስመር በመነሳት ኤሌክትሪኮችን ጫና ውስጥ እየከተቱ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርገዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ 16ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ከግራ በመነሳት ከወንድሜነህ አይናለም ተቀብሎ በመግባት የሞከረው እና ተከላካዮች የተደረቡበት እንዲሁም በ19 እና 20ኛው ደቂቃዎች አዲስአለም ደበበ እና ዐብይ በየነ ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ተጠቃሾች ነበሩ። 


በኃይሌ እሸቱ ተከላካይ መስመር በሚረብሹ ሩጫዎች ላይ ተመስርተው ኳሶችን ወደ ፊት ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋሉ የነበሩት ኤሌክትሪኮች በኳስ ቁጥጥራቸው ካሉሻ አልሀሰንን ነፃ ለማድረግ ተቸግረው ቢቆዩም በዲዲዬ ለብሪ የመስመር እንቅስቃሴ እየታገዙ ዳግም የበላይነቱን መያዝ ችለዋል። 28ኛው ደቂቃ ላይ ኄኖክ ካሳሁን ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ያደረጋት ሙከራም ለጥቂት ነበር በግቡ አናት የወጣችው። ዲዲዬ ለብሪን ከግራ ወደ ቀኝ መስመር ከቀየሩት በኃላ የሲዳማ ቡናን የተከላካይ መስመር ጥቅጥቅነት መበተን የቻሉት ኤሌክትሪኮች ካሉሻ አልሀሰንን ከኳስ ውጪ ነፃነት እንዲያገኝ በር ተከፍቶላቸውል። 33ኛው ደቂቃ ላይም ጀርባውን ለሲዳማ ግብ ሰጥቶ ከሳጥን ውጪ የተቀበለውን ኳስ በመያዝ እና ዞሮ ተከላካዮችን በማታለል ከገፋ በኋላ ካሉሻ አልሀሰን የአመቱን 14ኛ ጎሉን በድንቅ አጨራረስ አስቆጥሯል። 
ግቡን ካገኙ በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት ኤሌክትሪኮች ከእረፍት በፊት ሌሎች ሁለት ያለቃላቸው ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። እነዚህም 36ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ መላኩ ከመስመር ወደ ውስጥ ያሳለፈውን ኳስ ካሉሻ በእግሮቹ ስር አሾልኮ ሲተውለት ዲዲዬ ሞክሮ ፍቅሩ ወዴሳ የያዘበት እንዲሁም ከአንድ ደቂቃ በኋላ ስንታየው ዋለጩ ከግራ መስመር የሰጠውን ኳስ ኃይሌ እሸቱ ጨርፎት ኳስ ፍቅሩን አልፋ ግብ ልትሆን ስትቃረብ ተከላካዮች ከመስመር ላይ ያወጡበት አጋጣሚዎች ነበሩ። ተቆጣጥረውት የነበረው አጠቃላይ የጨዋታው ግለት ከእጃቸው እየወጣ የመጡት ሲዳማዎች ከወንድሜነህ ዓይናለም ፣ አዲስአለም ደበበ እና ዮሴፍ ዮሀንስ የሶስትዮሽ አማካይ መስመር ወደ ሁለቱ ኮሪደሮች ከሚልኳቸው ኳሶች ወደ ውስጥ ለመግባት ያደረጓቸው ጥረቶች ወደ መጨረሻ የግብ ዕድልነት ሳይቀየሩ ነበር ቡድኖቹ ወደ እረፍት ያመሩት።


ከዕረፍት ተመልሰው ጨዋታው ሊጀመር የፌደራል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው ፊሽካ እየተጠበቀ ባለበት ሰዐት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የዓዲግራቱ ጨዋታ ዘግይቶ በመጀመሩ ሰዐቱ መስተካከል አለበት በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ምንም እንኳን ዳኞቹ ይህን ጨዋታ በሰዐቱ ማስጀመራቸውን በማስረዳት ማዘግየት እንደማይችሉ ቢገልፁም ከኮምሽነሩ ጋር ጉዳዩን እስኪወያዩበት ደቂቃው ተስተካክሎ ከዓዲግራቱ ሁለተኛ አጋማሽ ጋር በተስተካከለ ደቂቃ እንዲጀመር ሆኗል። የመጀመሪያው አጋማሽ በጀመረበት መልኩ አሁንም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ተጋጣሚያቸውን ወደ ራሱ ሜዳ ገፍተው መንቀሳቀስ ችለዋል። ኃይሌ እሸቱም አሁንም ሰፊ የሜዳ ክልል ሸፍኖ መጫወቱን የቀጠለ ሲሆን በ51ኛው እና 55ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር የሚችልባቸውን ዕድሎች ቢያገኝም በሚያስቆጭ መልኩ አምክኗቸዋል። 
በመቀጠል 56ኛው ደቂቃ ላይ ዐብይ በየነ በግራ መስመር ሰብሮ በመግባት ወደ ውስጥ ባሳለፈው እና ማንም ባልተጠቀመበት ኳስ ምላሽ መስጠት የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች የተፈጠረባቸውን ጫና በመቀልበስ በኤሌክትሪክ ሜዳ ላይ ደቂቃዎችን ማሳለፍ ጀምረዋል። በርግጥ 68ኛው ደቂቃ ላይ ካሉሻ አልሀሳን ከቀኝ መስመር ካሳለፈለት ኳስ ዲዲዬ ለብሪ ሁለተኛው ቋሚ ላይ ተገኝቶ ለማስቆጠት ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም የጨዋታው ሚዛን ወደ ሲዳማዎች እያዘነበለ ነበር። 71ኛው ደቂቃ ላይ ወንድሜነህ አያናለም በሚታወቅበት የርቀት ሙከራው ከሳጥን ውጪ ያደረጋት ሙከራም በሱሊማና አቡ ልዩ ጥረት ነበር ለጥቂት ግብ ከመሆን የዳነችው። የሲዳማዎችን የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ተከትሎ ወደ ግብ ክልላቸው ያፈገፋጉት ኤሌክትሪኮች መጠነኛ መነቃቃት ያሳዩት ከታፈሰ ተስፋዬ መግባት በኋላ ነበር። ታፈሰ የሲዳማ ቡና ተከላካዮችን በማስጨነቁ በኩል በተዳከመው ኃይሌ እሸቱ ምትክ ነበር የገባው።

በጨዋታው ላይ ሚናው እየጎላ የመጣው ዲዲዬ ለብሪ 75ኛው ደቂቃ ላይ በግራ በኩል በአስደናቂ ሁኔታ የሲዳማን ተከላካዮች አልፎ ወደ ውስጥ በመግባት ለማቀበል የሞከረው ኳስ በተከላካዮች ቢከሽፍበትም ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ግን ያገኘውን ዕድል አላመከነም። አጥቂው ከመሀል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ ይዞ ገብቶ ከሞከረ እና ፍቅሩ ካዳነበት በኋላ በድጋሜ መቶ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ከፍ አድርጓል። ሆኖም የሁለት ጎል መሪነቱ የዘለቀው ለሶስት ደቂቃዎች ነበር። 81ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተጀመረውን ኳስ የኤሌክትሪክ ተከላካዮችን በማዘናጋት አዲስ ግደይ ወጥቶ በፍጥነት በመቀበል ወደ ውስጥ ሲያሻማ የቡድኑ አምበል አበበ ጥላሁን ሁለተኛው ቋሚ ጋር በማግኘት ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ልዩነቱን መልሶ ወደ አንድ አጥብቦታል። በቀሩት ደቂቃዎች ሲዳማዎች ወደፊት በማጥቃት እና የቆሙ ኳሶችን በመጠቀም ውጤቱን አጥብቆ የሚፈልገውን ተጋጣሚያቸውን አስጨንቀዋል። ሆኖም ጨዋታው ሌላ ግብ ሳይታይበት በኤሌክትሪክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። 

ነጥቡን 35 ያደረሰው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወራጅ ቀጠናው የወጣ ሲሆን 63ኛው ደቂቃ ላይ በከባድ ዝናብ ምክንያት የተቋረጠው የወልዋሎ ዓ.ዩ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ ወይንም ወልዋሎ ካሸነፈ በሊጉ መቆየቱን ያረጋግጣል። 


የአሰልጣኞች አስተያየት
ም/አሰልጣኝ ቦጋለ ዘውዴ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የመጨረሻው ጨዋታችን ስለነበር የግድ ማሸነፍ ነበረብን። እናም አሸንፈናል። ሆኖም የሌላ ጨዋታ ውጤት ለመጠበቅ ተገደናል ፤ የኛ ማሸነፍ ብቻውን በቂ አይሆንም። ነገር ግን ማሸነፋችን በራሱ አንድ ትልቅ ነገር ነው ብዬ አስባለሁ። ቡድናችን የይድረስ ይድረስ ሳይሆን በሚገባ መሰረት ይዞ መገንባት አለበት። የሚያተርፈውም የራስ ጠንካራ ስራ ብቻ ነው። ዘንድሮ ቡድኑ ይትረፍ እንጂ ይህ ነገር የሚደገም አይመስለኝም።

አሰልጣኝ ዘርዐይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

በዛሬው ጨዋታ ቡድናችን ደክሞ ታይቷል። የማጥቃት ሀይላችን ተዳክሟል። ኳስ ይዘን ለመጫወት ብንሞክርም ሀይል አልነበረንም። ይህ ድካም የመጣው ደግሞ ፌዴሬሽኑ በሚያወጣቸው መርሀግብሮች ነው። ጨዋታው አዲስ አበባ ላይ ይከናወን የነበረ በመሆኑ እዛው ጭቃ ሜዳ ላይ ልምምዳችንን አድርገናል። ከዛ ዛሬ ጠዋት ተጉዘን መጥተን ነው ይህን ጨዋታ ያደረግነው። ቡድኔ በፊት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አላደረገም ዛሬ ፤ በጣም ደስተኛ አይደለሁም። ሊታሰብበት ይገባል ፕሮግራም መቀያየር ቡድኖችን ይጎዳል።