በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 30ኛ ሳምንት ትላንት የተቋረጠው የወልዋሎ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በድሬዳዋ 2-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 3ኛው ወራጅ ቡድን መሆኑ ተረጋግጧል።
ኤሌክትሪክ ትላንት አዳማ ላይ ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ 2-1 ማሸነፍ ቢችልም በሊጉ ለመቆየት የድሬዳዋ ነጥብ መጣልን ሲጠብቅ ነበር። ሆኖም ድሬዳዋ በማሸነፉ በተመሳሳይ ነጥቦች በግብ ልዩነት ተበልጦ ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ወርዶ የማያውቀው ኤሌክትሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከሊጉ ወርዷል።
በ1953 የተመሰረተው ኤሌክትሪክ በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ከሚጠቀሱ ታላላቅ ክለቦች አንዱ የነበረ ሲሆን በ1985፣1990 እና 1993 የኢትዮጵያ ቻምፒዮን መሆን የቻለ ቡድን ነው። በ1990 ሊጉ በአዲስ መልክ ሲጀመር ከነበሩት 3 ክለቦች አንዱ የነበረውና ቻምፒዮን መሆን የቻለው ኤሌክትሪክ በ90ዎቹ ከአውራ የሊጉ ቡድኖች አንዱ የነበረ ቢሆንም ከሚሌኒየሙ ወዲህ ባሉት ዓመታት የቀድሞ ሞገሱ ተገፎ በተደጋጋሚ ላለመውረድ ሲጫወትና በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ሲተርፍ ቆይቶ ዘንድሮ በ35 ነጥቦች ለመውረድ ተገዷል።
ፎቶ – በሊጉ 30ኛ ሳምንት የተጫወተው ቡድን