መቐለ ከተማ የሶስት ተጫዋቾችን ዝውውር ማጠናቀቁ ታውቋል። ዮናስ ገረመው፣ ሳሙኤል ሳሊሶ እና ቢያድግልኝ ኤልያስ ለክለቡ የፈረሙ ተጫዋቾች ናቸው።
የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ቢያድግልኝ ኤልያስ በ2005 ከሲዳማ ቡና ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካመራ በኋላ በፈረሰኞቹ ቤት ለ4 የውድድር ዘመን ቆይቶ ወደ አርባምንጭ በማቅናት የግማሽ ዓመት ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ጅማ አባ ቡና ቀጥሎም የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ባሳለፈበት ወልዲያ ተጫውቷል። ተጫዋቹ በመቐለ የፍቃዱ ደነቀ እና አሌክስ ተሰማን ጥምረት ሰብሮ የመሰለፍ ፈተና ይጠብቀዋል።
ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ድንቅ የውድድር ዓመት ያሳለፈውና ከክለቡ ጋር ቻምፒዮን የሆነው ዮናስ ገረመው ወደ መቐለ ከተማ የተዛወረ ሌላው ተጫዋች ነው። ዮናስ ሀላባ ከተማን ለቆ በ2006 ኢትዮጵያ ቡና ካመራ በኋላ በ2008 በድሬዳዋ ከተማ፣ በ2009 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆይታ አድርጓል። በጅማም ከአንድ ዓመት በላይ ሳይዘልቅ ወደ መቐለ አምርቷል። በውድድር ዓመቱ በፈጣሪ አማካይ እጦት የተቸገረው መቐለ ከተጫዋቹ ፊርማ ተጠቃሚ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ሳሙኤል ሳሊሶ ሌላው የመቐለ ፈራሚ ነው። በመሀል አማካይ እና የመስመር አጥቂነት መጫወት የሚችለው ሳሙኤል ሼር ኢትዮጵያን ለቆ ወደ መከላከያ ካመራበት 2007 ጀምሮ ያለፉትን 4 የውድድር ዘመናትን በጦሩ ቤት የቆየ ሲሆን በመቐለ ከቀድሞ አሰልጣኙ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር የመገናኘት እድል አግኝቷል።
መቐለ ከተጠቀሱት ተጫዋቾች በተጨማሪ ጋብሬል አህመድን ባለፈው ሳምንት ማስፈረሙ የሚታወስ ነው።