ቅዱስ ጊዮርጊስ ጌታነህ ከበደን ማስፈረሙን በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ አስታውቋል።
በ2009 ከደቡብ አፍሪካው ቢድቬትስ ዊትስ የ3 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ደደቢት ተመልሶ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት በክለቡ ያሳለፈው ጌታነህ ከበደ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለሁለት ዓመት ለመጫወት ፊርማውን ማኖሩን ክለቡ ገልጸል።
በሚሌንየሙ መጀመርያ በደቡብ ፖሊስ ከእግርኳስ ቤተሰብ ጋር የተዋወቀው ጌታነህ በ2001 የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ከተመረጠ በኋላ ወደ ደደቢት አምርቶ በአምበልነት የሊግ ዋንጫ እስካነሳበት 2005 ድረስ ቆይቷል። በ2006 ወደ ቢድቬትስ ዊትስ አምርቶ ለሶስት ዓመታት በደቡብ አፍሪካ ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ደደቢት መመሀሱ ይታወሳል። በፕሪምየር ሊጉ ለ3 ጊዜያት ያህልም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል።
ከአቤል ያለው እና ኄኖክ አዱኛ በመቀጠል የክለቡ ሦስተኛ ፈራሚ የሆነው ጌታነህ የክለቡ ደጋፊዎች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲያመራ ምክንያት መሆናቸውን ገልጿል። ጌታነህ ባለፈው ዓመት በተጫዋቾቹ ጉዳት ሲቸገር የቆየው የፈረሰኞቹ የአጥቂ መስመርን እንደሚያጠናክር ታምኖበታል።