የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እግርኳስ ፌደሬሽን የ2010 ዓም ጠቅላላ ጉባዔ እና የማሟያ ምርጫውን ለማከናወን ከ15 ቀናት በፊት ቀን ቆርጦ የነበረ ቢሆንም ከአአ ወጣቶች እና ስፖርት የማህበራት ማደራጃ በተላከ ደብዳቤ ጠቅላላ ጉባኤው እንዳይከናወን፣ ቀኑ እንዲራዘም እና የተፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱ መጠየቁ ይታወሳል።
ፌደሬሽኑ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ የፕሬዝዳንት እና የሁለት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሟሟያ ምርጫ ለማድረግ እንዳሰበ እና የእጩዎቹን ስም ዝርዝር ማውጣቱ የሚታወስ ሲሆን ከእጩዎቹ ስም ዝርዝር መውጣት በኋላ ሁለት ክፍለ ከተሞች ቅሬታ በማስገባታቸው ነገሮች መጓተታቸው ይታወቃል። የፌደሬሽኑ ጊዜያዊ ዋና ሰብሳቢ አቶ በለጠ ዘውዴ ዛሬ ለሶከር ኢትዮጵያ በገለፁት መሰረት ችግሮቹ እና አለመግባባቶቹ መፈታታቸውን ያስረዱ ሲሆን ችግሮች አሉ በተባሉበት ነገሮች ላይ ሁሉ ፌደሬሽኑ ከሚመለከታቸው አካላቶች ጋር በመነጋገር አለመግባባቶችን በጥሩ ሁኔታ እንደፈታ ገልፀዋል።
በቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔውን ጳግሜ 3 በኢትዮጵያ ሆቴል ለማከናወን ዛሬ የፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ተሰብስቦ መወሰኑን እና የሟሟያ ምርጫውንም በዛኑ እለት ለማከናወን መታሰቡን አቶ በለጠ ጨምረው አስረድተዋል።
በተያያዘ ዜና የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለ13ኛ ጊዜ የሚያከናውነው የአዲስ አበባ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) በመስከረም ወር መጨረሻ በደመቀ ሁኔታ ለማከናወን ፌደሬሽኑ እንቅስቃሴዎችን መጀመሩን እና የምስራቅ አፍሪካ ተጋባዥ ክለቦችን ለማምጣት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።