ባህር ዳር ከተማ በ2010 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በመወዳደር የምድብ ሀ የበላይ በመሆን በቀጣይ አመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ መሆኑን ከምድቡ ሶስት ጨዋታዎች እየቀሩት ማረጋገጡ ይታወሳል። በ27ኛ ሳምንት የምድብ ሀ የከፍተኛ ሊግ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ ኢትዮጵያ መድንን 2ለ1 በመርታት ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ አላማን ያሳካው ቡድኑ ማለፉን ካረጋገጠ በኃላ አዳዲስ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ እየቀላቀለ እንዲሁም የነባር ተጨዋቾችን ውል እያደሰ ይገኛል።
በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው የሚመሩት የጣና ሞገዶቹ ከዚህ ቀደም የስምንት ነባር ተጨዋቾችን ውል ማደሱ የሚታወስ ሲሆን አሁን ተጨማሪ የአምስት ወሳኝ ተጨዋቾችን ውል ማደሱ ታውቋል።
የመጀመሪያው ውሉን ያደሰ ተጨዋች ወሰኑ ዓሊ ነው። የቀድሞው የመድን አጥቂ ከመስመር እየተነሳ ለቡድኑ ወሳኝ የግብ ማግባት እድሎችን ሲፈጥር የነበረ ተጨዋች ነው። ብዙውን ጊዜ በቀኝ እንደ ሁኔታው ደግሞ በግራ መስመር ሲጫወት ዓመቱን ያሳለፈው ይህ የመስመር አጥቂ በቀጣይ ቦታውን ለማስጠበቅ ከአዳዲሶቹ ፈራሚዎች ማራኪ ወርቁ እና እንዳለ ደባልቄ ፈተና እንደሚጠብቀው ይገመታል።
ቡድኑ ሌላው ለአንድ አመት ውሉን እንዲያድስ ያደረገው ተጨዋች ግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎ ነው። ተጨዋቹ በምድቡ ከነበሩ 16 የመጀመርያ ተሰላፊ ግብ ጠባቂዎች መካከል ከሽረ እንዳሥላሴው ሙሴ ዮሃንስ (18) እና ከገጣፎው አንተነህ ሃብቴ (18) በመቀጠል አነስተኛ ግብ (21) የተቆጠረበት ተጨዋች ነው።
ሌላው ውሉን ያደሰው ተጨዋች ከኢትዮጵያ ቡና ወደ ባህር ዳር መጀመሪያ በውሰት ቀጥሎም በቋሚነት የፈረመው ሳለዓምላክ ተገኝ ሲሆን እሱም እንደ ሌሎቹ ተጨዋቾች ለአንድ አመት መፈረሙ ተረጋግጧል። በመጀመሪያ ዙር የከፍተኛ ሊግ ጨዋታ ቡድኑን በቋሚ 11 ውስጥ በመግበት ሲጠቅም የነበረው ሳለዓምላክ በሁለተኛው ዙር ውድድር አብዛኞቹን ጨዋታዎች በተጠባባቂነት አልፎ አልፎ ደግሞ ተቀይሮ እየገባ ሲጫወት ታይቷል።
በተጨማሪ ቡድኑ የተከላካዩን ሄኖክ አቻምየለህን እና በብዙ የጣናው ሞገድ ደጋፊዎች ተወዳጅ የሆነው ዳግም ሙሉጌታን ውል ማደሱ ተነግሯል። ሁለቱም ተጨዋቾች አመቱን እየተቀየሩ እየገቡ ቡድናቸውን ያገለገሉ ሲሆን በተለይ ዳግም ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ለአጥቂዎች በማቀበል የግብ እድሎችን ሲፈጥር የነበረ ተጨዋች ነው።
ባህር ዳር ከዚህ ቀደም የአሰልጣኙ ጳውሎስ ጌታቸው ውል ከማደሱ በተጨማሪ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ፣ ዳንኤል ኃይሉ፣ ደረጄ መንግስቱ፣ ፍቃዱ ወርቁ፣ ግርማ ዲሳሳ፣ ተስፋሁን ሸጋው፣ ወንድሜነህ ደረጄ እና አቤል ወዱን ውል ማደሱ ይታወሳል።